‘’በኦሮሚያም ይሁን በአማራ ያሉ ታጣቂዎች ሺህ ዓመት ቢዋጉን አያሸንፉንም’’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የብልፅግና ፓርቲን 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ በአድዋ ሙዚየም ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራም ይሁን በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሀይሎች በውጊያ እንደማያሸንፉ አውቀው በንግግር ቢገቡ ይሻላችኋል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው ንግግራቸው የብልፅግና ፓርቲ አባላት ቁጥር 15.7 ሚሊዮን በላይ መድረሱን፣ ይህ በአፍሪካ ግዙፉ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው ፓርቲያቸው ወደ ስልጣን ከመጣበት ከህዳር 21 ቀን 2012 እስከ ዛሬ ድረስ ያከናወናቸውን የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ አስረድተዋል፡፡
ኢኮኖሚን በተመለከተ ሀገሪቱ ባለፉት 5 ዓመታት የበጋ ስንዴ ማምረት የጀመረችበት፣ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ የገቡበት፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች የተመረቁበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዲፕሎማሲን በተመለከተ ባደረጉት ንግግርም ኢትዮጵያ በኢህአዴግ ዘመን መንግስት ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በሚባል ደረጃ መጋጨቷን ተናግረው ባለፉት 5 ዓመታት ግን ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እየሰራች ያለችው በወዳጅነት እና በትብብር እንጂ አንድም የጥይት ልውውጥ አላደረገችም ብለዋል፡፡
ፖለቲካን በተመለከተ የብልፅግና ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ አንዲስ የፖለቲካ ልምምድ በኢትዮጵያ አስጀምረናል ብለዋል፡፡
በፊት በኢትዮጵያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መስራት አልተለመደም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልፅግና ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ግን በፊት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበረውን በጠላትነት የመተያየት ብሂል አስቀርቷል ብለዋል፡፡
ብልፅግና ከሀሳብ እንጂ ከሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማንኛውም ሰው ጋር በሀሳብ አብሮ ለመስራት ፍቃደኛ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ፓርቲያቸው 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር ኢትዮጵያ የምትረዳ እንጂ የማትረዳ የውጪ፣ ሀገራት ሊያስታርቋት የሚለምኗት ሳይሆን የምታስታርቅ ሀገር ትሆናለች ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments