የሞሪታንያው ፕሬዘዳንት ሞሐመድ ኤልድ ጋዙአኒ በሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባትን ለማስፈን ያለመ ምክክር እንዲጀመር እየተዘጋጀሁ ነው አሉ፡፡
ፕሬዘዳንቱ ብሔራዊ ምክክር ለመጀመር መታሰቡን ያበሰሩት የአገሪቱን 64ኛ አመት የነፃነት በዓል ምክንያት በማድረግ ባሰሙት ንግግር ነው፡፡
ሞሐመድ ኡልድ ጋዙአኒ ሞታንያውያን ያለፍንበትን እና የመጣንበትን በቅጡ መመርመር ይኖርብናል ማለታቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡
ምክክሩ ዴሞክራሲ በሀገሪቱ ሥር እንዲሰድ ያግዛል ብዬ አምናለሁ ብለዋል ፕሬዘዳንቱ፡፡
በቀደሙት ዓመታት የመንግስት ተዋቃሚ የፖለቲካ ማህበራት የብሔራዊ ምክክርን አስፈላጊነት ሲጎተጉቱ መቆየታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ አዳጊዎች ማንኛውንም ማህበራዊ ድረ ገፅ እንዳይጠቀሙ ልትከለክል ነው፡፡
የአውስትራሊያ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) አዳጊዎች ማንኛውንም ማህበራዊ ድረ ገፅ እንዳይገለገሉ የሚከለክለው ህግ ማፅደቁን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ይሁንና ህጉን ሥራ ላይ ለማዋል የ1 ዓመት የሽግግር ጊዜ ይኖራል ተብሏል፡፡
ህጉን የማያከብሩ የኢንተርኔት (መረጃ መረብ) አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያዎች 50 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር መቀጮ ይቆነደዳሉ ተብሏል፡፡
የመቀጮ ገንዘቡ ከ32 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የምንዛሪ ግምት አለው፡፡
የክልከላው ነገር ከወዲሁ በስፋት ማነጋገር እንደጀመረ መረጃው አስታውሷል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬይኗ ርዕሰ ከተማ ኪየቭ የሚገኙ የመንግስት ሹሞች ውሳኔ ማስተላለፊያዎችን በሚሳየል ለመምታት ዛቱ፡፡
ፑቲን በኪየቭ የሚገኙ መንግስታዊ ውሳኔ ማስተላፊያዎችን እመታለሁ ያሉት በአዲስ ስሪቱ መካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየል እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ኪየቭን የአዲስ ስሪቱ ሚሳየል ዒላማ እናደርጋታለን ያሉት ዩክሬይን ወደ ሩሲያ ምዕራብ ስሪት ሚሳየሎችን ለመተኮሷ ምላሽ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ ቀደም ሲል የዩክሬይንን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ለማሽመድመድ የታለመ መጠነ ሰፊ ድብደባ መፈፀሟ ተጠቅሷል፡፡
የዩክሬይን ሹሞች በድብደባው አንዳችም ጉዳት አልገጠመንም እያሉ ነው፡፡
ይሁንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዩክሬይናውያን ካለ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መቅረታቸው ተሰምቷል፡፡
የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር አንድ ከፍተኛ የጦር ሹምን በሥነ - ምግባር ጥሰት ከሀላፊነት አባረራቸው፡፡
በሥነ ምግባር ጥሰት ከከፍተኛ ወታደራዊ ሹምነት የተባረሩት ሚያኦ ሁአ የተባሉ ግለሰብ እንደሆኑ አልጀዚራ ፅፏል፡፡
ግለሰቡ በአገሪቱ ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ነበሩ ተብሏል፡፡
በቻይና የሥነ - ምግባር ጥሰት ብዙው ጊዜ ከምዝበራ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
ይሁንና ሚያኦ ሁአ የተባረሩበት ምክንያት በዝርዝር አልተብራራም፡፡
ባለፉት 2 ዓመታት ገደማ 20 ያህል የወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች የበላዮች ከሀላፊነት ተባርረው እንደታሰሩ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments