በመደበኛው ገበያና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ልዩነት እየጠበበ መጥቶ 7.8 በመቶ መድረሱን ብሔራዊ ባንክ ተናገረ፡፡
ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ካካሄደች ከ3 ወራት በላይ ሆኗታል፡፡
ማሻሻያው በተተገበረባቸው በእነዚህ ጊዜያት በተለይ የፋይናንስ ዘርፉ ምን ለውጥ መጣ? በሚል በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት ተመክሮበታል፡፡
ማሻሻያው ሲደረግ ለማሳካት እንደግብ ከተቀመጡ በርካታ ጉዳዮች መካከል የፋይናንስ ዘርፍ ፓሊሲ ማሻሻያ አንዱ ነው፡፡
በዚህም ውስጥ የፋይናንስ ተደራሽነትና አካታችነትን ማረጋገጥ ይገኝበታል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያም ሌላው ነው፤ ይህም ሲደረግ ገበያ መር የሆነ የውጭ ምንዛሪ እንዲኖር ማስቻልን፣ በፋይናንስ ሴክተሩ በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲኖር ለማድረግ በማሰብ እንደተደረገ ለምክክሩ መነሻ ሚሆን ገለፃ ያደረጉት በብሔራዊ ባንክ የውጭ ኢኮኖሚ ትንተናና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሀብታሙ ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡
በገለፃቸውም ባለፉት 3 ወራት በጉልህ ከታዩ ለውጦች መካከል በመደበኛና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ እንደተቻለ አንስተው ማሻሻያው ከመደረጉ አንድ ቀን በፊት ሐምሌ 21 2016 በፊት በመደበኛና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረው ልዩነት 97 በመቶ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይሁንና ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ልዩነቱ እየጠበበ መጥቶ ከትናንት በስቲያ ዕረቡ ህዳር 18 2017 ዓ.ም የመደበኛ እና የጥቁር ገበያው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ልዩነት 7.8 በመቶ መሆኑን አቶ ሃብታሙ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ሪፎርሙ ካመጣቸው ለውጦች መካከል ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ግኝት ጨምሯል ከሪፎርሙ በፊት ባሉ 3 ወራት 793 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን ከማሻሻያው በኋላ ባሉ 3 ወራት ግን ከኤክስፖርት የተገኘው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ነው ብለዋል፡፡
በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት በባንክ የሚልኩት ገንዘብም ከ973 ሚሊዮን ዶላር ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደተሻገረም ጠቅሰዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እነዚህን ለውጦች ቢያመጣም በተለይ የፋናንስ ዘርፉ ለውጭ ሃገራት ክፍት ከመደረጉ በፊት የሃገር ውስጥ ባንኮች አቅማቸውን ማጠናከር ካልተቻለ ለመወዳደር ከባድ እንደሚሆን ከምክክሩ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል በአዋሽ ባንክ የባንክ ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሃይሉ ነግረውናል፡፡
ማሻሻያው አሳክቷቸዋል ከተባሉ ጉዳዮች ባሻገር በተለይ ሸማቹ ማህበረተሰብ ላይ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ጫና በደምብ ሊጤንና የማስተካከያ እርምጃዎች በመንግስት ሊወሰዱ ይገባል የሚል ሃሳብም በምክክሩ ተነስቷል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments