የሀይል ማመንጫና የማከፋፈያ ጣቢያዎች በሚገነቡበት ወቅት የሚያጋጥም የአቅርቦት እጥረት እና መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርስ ስርቆት ፈተና ሆነውብኛል ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ተናገረ፡፡
በተለይ ደግሞ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ስርቆት ከፍተኛ መሆኑን ተቋሙ ተናግሯል፡፡
ከዚህ ቀደም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ስርቆት የሚፈፀምባቸው ነዋሪ በማይበዛባቸው አካባቢዎች እንደነበር የሚናገሩት የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን #አዲስ_አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ይሄው ችግር እየታየ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች በስርቆት ምክንያት በየሁለት እና ሶስት ቀናት #የኤሌክትሪክ_አገልግሎት_መቆራረጥ እንደሚፈጠር የሚናገሩት አቶ ሞገስ ይህ የሚያሳየውም ችግሩ እየጨመረ መምጣቱን ነው ይላሉ፡፡
የወደሙትን እና የተሰረቁትን መሰረተ ልማቶች ለመተካት ተቋሙ የሚያወጣው ወጭ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ይህንን #ችግር እያስተናገድኩ ቢሆንም በ2017 በጀት አመት የ3 ወራት አፈፃፀሜ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ አሳይቷል ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት ተቋሙ ለማመንጨት እቅድ ይዞ የነበረው 5,517 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጅ ነበር፤ ያመነጨው ደግሞ 6,456 ጊጋ ዋት ሰአት ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ይህም ከእቅዱ 17 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ተናግረዋል፡፡
ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ35.6 በመቶ ጭማሬ እናዳለው ሰምተናል፡፡

ተቋሙ በሶስት ወራት አከናወንኩት ያለው 6004 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጅ ሽያጭ ጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ ለሀገር ውስጥ ደንበኞቹ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለከፍተኛ ሀይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች እና ለጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት ያደርጋል ተብሏል፡፡
በዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጅቡቲ፣ ሱዳን እና #ኬንያ የኢትዮጵያን ኤሌክትሪክ የሚገዙ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል እና አገልግሎት በተያዘው በጀት ዓመት የሚሰጡት አገልግሎት ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የ2017 በጀት ዓመት የሶስት ወራት አፈፃፀሙ ከእቅዱም ሆነ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አብላጫ ማሳየቱ የታሪፍ ጭማሬው ውጤት ይሆን? ስንል የጠየቅናቸው የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ጭማሪው ያጣው ውጤት ሳይሆን የተመረተው ኤሌክትሪክ መጨመሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Komentarji