top of page

ህዳር 19፣2017 - የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ጥረት አንዳንዶች በህገወጥ መንገድ መድሃኒት ወደ ሀገር ውስጥ እያስገቡ ነው ተባለ

በተለያዩ ክልሎች የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ጥረት አንዳንዶች በህገወጥ መንገድ መድሃኒት ወደ ሀገር ውስጥ እያስገቡ ነው ተባለ፡፡


እነዚህ መድሃኒቶች ፈቃድ የሌላቸው እና ታማሚዎች እንዲጠቀሙት ህጋዊ ፍቃድ ያልተሰጣቸው ናቸው ተብሏል፡፡


የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ነው ይህንን ያሉት፡፡


የምክር ቤቱ አባላት ሀገሪቱ ውስጥ የወባ ወረርሽኝ ተከስቷል ለመቆጣጠር የጤና ሚኒስቴር ምን እየሰራ ነው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡


የጤና ሚንስትሯ በበኩላቸው ‘’የተከሰተው የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል እንደ ተቋም እየሰራን ነው’’ ብለዋል፡፡

‘’የወባ በሽታው በዚህ ልክ የተስፋፋው ህብረተሰቡ ወባን ለመከላከል እያደረገ የነበረው ስራ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ነው’’ ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል፡፡


በተለይም የአጎበር አጠቃቀም ችግር የወባ በሽታ ባለባቸው አካባቢዎች ይታያል ያሉት መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) አሁንም ድረስ ያልተቀረፈ ችግር ነው ብለዋል፡፡


የፈጣን የወባ መመርመሪያ ኪቶች፣ አጎበር ስርጭት የጤና ሚንስቴር የወባ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎች እንዲሰራጭ አድርጓል ተብሏል፡፡


‘’ለወባ በሽታ የሚሆኑ መድሃኒቶች በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ እና በውስጥ ሲንቀሳቀስ ነበር’’ ያሉት ሚኒስትሯ ‘’450 ኩንታል ወይም 45 ቶን መድሃኒትም በቁጥጥር ስር ውሏል’’ ብለዋል፡፡


ከዚህ ውስጥ 9 ኩንታል የሚሆነው መድሃኒት ከመንግስት መስሪያቤቶች በህገወጥ መንገድ የወጣ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 2 ወቅቶች የወባ በሽታ ስርጭት የሚጨምርበት ነው የሚሉት ሚኒስትሯ በተለይም አሁን ያለንበት ወቅት አንደኛው ነው ብለዋል፡፡


አሁን ላይ የጤና ሚኒስቴር በመድሃኒትና የአጎበር ስርጭት በማድረግ ህብረተሰቡ እራሱን እንዲጠብቅ እያደረገ ነው የተባለ ሲሆን በተለይም የአጎበር አጠቃቀም ክፍተት የወባ በሽታ አለባቸው በሚባሉ አካባቢዎች አለ ተብሏል፡፡


ህብረተሰቡ ይህንን ክፍተቱ በፍጥነት እንዲቀርፍ ሁሉም ማህበረሰብ በጋራ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡


በረከት አካሉ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


留言


bottom of page