top of page

ህዳር 18፣2017 - ከኢትዮጵያ ህዝብ 68.7 በመቶው በድህነት ውስጥ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ሪፖርት አሳይቷል

ከኢትዮጵያ ህዝብ 68.7 በመቶው በድህነት ውስጥ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት(UNDP) ያወጣው ሪፖርት አሳይቷል፡፡


በዚህ UNDP ባወጣው የሀገራት የድህነት ምጣኔ ሪፖርት በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ድህነቱ የከፋ እንደሆነና 79 በመቶ እንደሚደርስ አስቀምጧል፡፡


ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከUNDP ጋር በመሆን ባደረጉት በዚህ ጥናት ከዚህ በፊት በተመድ የተቀመጠውን አንድ ሰው ደሃ ለመባል ከ2.15 ዶላር ወይም በቀን ከ250 ብር በታች የሚያገኝ መሆን አለበት የሚለውን በመቀልበስ፤ በዋናነት 3 ትልልቅ መለኪያዎችን (የትምህትርት፣ የጤናና የአኗኗር ሁኔታ) በማስቀመጥ በእነዚህ ስር ደግሞ 10 መለኪያዎችን በማከል የ112 ሀገራትን የድህነት ምጣኔ አስቀምጧል፡፡


ኢትዮጵያ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንዳለባትም አሳስቧል።

ሪፖረርቱን መሰረት አድርገን ቀጣዩ የኢትዮጵያ የቤት ስራ ምን ሊሆን ይገባል? በሚለው ጉዳይ ዙሪያ በዘርፉ ለረጅም ዓመታት የሰሩትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብና ኒውትሪሽን ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አሻግሬ ዘውዱን ጠይቀናል፡፡


ባለሙያው እንደሚሉት ከዚህ በፊት በተመድ የድህነት መለኪያ ተደርጎ የሚሰላው በቀን 250 ብር በወር 7500 ብር በላይ የሚያገኝ ሰው ደሃ አይደለም የሚለው አስተሳሰብ በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ መለኪያ ሊሆን አይችልም፤ አሁን ባለው የኑሮ ጫና በወር 10,000 ብርም የሚያገኝ ሰውም በድህነት ውስጥ እየኖረ ነው ይላሉ፡፡


በጥናቱ መሰረት የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላት ያልቻሉ 1.1 ቢሊዮን ሰዎች በአለም ዙሪያ በድህነት ውስጥ ናቸው፤ ከእነዚህም ውስጥ 40 በመቶዎቹ ወይም 455 ሚሊዮን ሰዎች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የግጭት እና ከሰሃራ በስተደቡብ የሚኖሩ ናቸው፡፡


ጥናቱን ለመከወን ከተቀመጡ 10 መለኪያዎች አንዱ አመጋገብ ነው። የህፃናት ሞት፣ የትምህርት ተደራሽነትና መጠነ መቋረጥ፣ የኤልክትሪክና የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ የመኖሪያ ቤት መሰረታዊ ነገሮችን ያሟላ መሆኑ እንዲሁም ቤተሰቦች የሚይዙት ጥሪት ይጠቀሳል፡፡


ኢትዮጵያ በእነዚህ መስፈቶች ተለክታ ከህዝቧ በከተማ 68.7 በመቶ በገጠር ደግሞ 79በመቶ ድርህነት ውስጥ እንዳለ ታይቷል።


ይህንን ጥናት ለማድረግ ተቋማቱ ተጠቀሙት በ2019 ያገኙትን መረጃ የሚጠቅሱት የስነ ምግብ ተመራማሪ ዶ/ር አሻግሬ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ያሳለፈችው ጦርነትና አሁንም ያለችበት ግጭትና መፈናቀል ደረጃዋን ከዚህም ሊያወርደው እንደሚችል ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

በጥናቱም እንደተመለከተው ግጭቶች በዚህ ከቀጠሉ ይህ 68.7 በመቶ 18.4 በመቶ ተጨምሮበት የድህነት ምጣኔውን 80 በመቶ ያደርሰዋል፡፡


በጉዳዩ ዙሪያ የፕላንና ልማት ሚኒስቴርን ሃሳብ ለማካተት ተደጋጋሚ ጥረቶች ብናደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡


ይሁንና ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያዎቹ ቀናት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን አስመልክቶ ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ ባደረጉት ገለፃ ኢትዮጵያ ባለፉት 6 ዓመታት በአማካኝ የ7.2 በመቶ እድገት ማስመዝገቧን ጠቅሰዋል።


ድህነት ቅነሳ ላይ በተሰራው ስራ ለውጥ መጥቷል፤የእናቶችና ህፃናት ሞት ቀንሷል፣በትምህርትም በተለይ የቅድመ መደበኛ ት/ት 37 በመቶ ደርሷል፣ በፆታ እኩልነት ከአለም 124ኛ ከነበረችበት 75ኛ መሆን ችላለች በማለት ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡


በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ ተደራሽነት 52 በመቶ ቢደርስም 48 በመቶ ህዝቡ የኤሌክትሪክ ብርሃን አላየም፣ ከ30 በመቶ በላዩ የንፁህ መጠጥ ውሃ እንዳላገኘ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡


በተጨማሪም በቅርቡ ኢትዮጵያ አስተናግዳው በነበረው ከረሃብ ነፃ አለም በሚል በተሰናዳው አለም አቀፍ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ድህነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ በሰራችው ስራ ለውጥ አምጥታለች፣ የሚታረሰው መሬት በ6 ዓመት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል፣ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ እንደ ስንዴና ጤፍ ያሉ ምርቶች መጣ ያሉትን ለውጥ አብራርተዋል፡፡


ወደ ሪፖርቱ ስንመለስ ኢትዮጵያ በድህነት አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ ናት የሚለው የዩኤንዲፒ የዘንድሮ ሪፖርት ከዚህ ለመውጣት ፈጥና ትላልቅ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ የዘነጋቻቸውን የአካል ጉዳተኛና ሌላውንም ማህበረሰብ በፖሊሲ ማዕቀፏ ማካተት እንደሚኖርባትም ምክረ ሃሳቡን ሰጥቷል፡፡


በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የምግብና ኒውትሪሽን ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አሻግሬ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ ። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ማስቀደም ያለባትን ብታስቀድም ያዋጣታል፤የመንግስት ቀዳሚ ትኩረት ስራ ፈጠራ ላይ፣ ምርታማነትን መጨመር ላይ፣ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ላይ በአጠቃላይ የሰዎችን የኑሮ ሁኔታ መለወጥ ላይ መሆን አለበት ሲሉ መክረዋል፡፡


ተቋሙ በአውሮፓውኑ የዘመን ቀመር በ2019 አውጥቶት በነበረው የሀገራት የድህነት ምጣኔ ሪፖርት ኢትዮጵያ ከህዝቧ 83.8 በመቶ በድህነት ውስጥ እንዳለ መጥቀሱ ይታወሳል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comentários


bottom of page