top of page

ህዳር 18፣2017 - በወንጀል ተግባር የተገኘን ንብረትንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ ቅሬታ ቀረበበት

በወንጀል ተግባር የተገኘን ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ ወደኋላ አስር ዓመት ተመልሶ ተጠያቂ የሚያደርግበት አሰራር ግልፅነት የሚጎድለው ነው የሚል ቅሬታ ቀረበበት፡፡

 

ቅሬታው የቀረበው በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ ደረጃ ላይ በተሰናዳው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

 

አዋጁ አስር ዓመት ወደኋላ ሄዶ የሚመለከትበት ምክንያት አሳማኝ አይደለም የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡

 

‘’በእኔ እምነት ሙስና በሃገራችን ስር የሰደደው ከ1997 በኋላ ይመስለኛል’’ ያሉት አንድ ጠያቂ ‘’አስር ዓመት ወደኋላ ተሄዶ ይመረምራል የሚለው የቀረበው ምክንያት መሰረት አላገኘሁትም’’ ብለዋል፡፡

 

አዋጁ አስር ዓመት የሚለው በሚገባ የሚያሳምን አይደለም የሚሉት ጠያቂው ከሆነም ለምን ወደኋላ ሄዶ ሙስና በሀገሪቱ መሰረቱን በዘረጋበት ቢታይ ብለዋል፡፡

 

‘’ደግሞም በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለምን አልሆነም?’’ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

 

በመንግስት በበኩሉ በሰጠው ምላሽ አስር ዓመት ወደኋላ መመለስ የተፈለገበት ምክንያት የመንግስት ተቋማት የደንበኞቻቸውን ሰነድ አስር ዓመት የመያዝ ግዴታ ስላለባቸው ነው፡፡ ማስረጃ እኔ የለኝም ብሎ መከራከር የሚፈልግ ተጠርጣሪ ካለ ቢያንስ ማስረጃውን ከመንግስት ማግኘት እንዲቻል ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

 

ውጭ ኖረው ሃብት ስላፈሩ ዜጎች እና በሞባይል ባንኪንግ ለአጋቾች ለሚተላለፍ ገንዘብም ተጠይቋል፤ መንግስትም ምላሽ ሰጥቷል፡፡


ያሬድ እንዳሻው

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g

 

 

Yorumlar


bottom of page