top of page

ህዳር 18፣2017 - ማሻሻያው ተቋሙ የሚገጥመውን የመድሃኒት ግዢ መስተጓጎል ያስቀርለታል ተብሏል

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሚያጋጥመውን የበጀት እጥረት ለማስተካል ተገልጋይ ተቋማት በዱቤ የሚወስዱትን መድሃኒት ገቢ በአግባቡ እንዲመልሱ እንዲሁም ባላቸው የበጀት አቅም ብቻ መድሃኒት እንዲያዙ የሚያስችል የማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ተደረገለት፡፡

 

ማሻሻያው ተቋሙ የሚገጥመውን የመድሃኒት ግዢ መስተጓጎል ያስቀርለታል ተብሏል፡፡

 

ከመንግስት ምንም ዓይነት በጀት የማይመደበለትና በተገላባጭ ፈንድ መድኃኒቶችና የህክምና ግብዓቶችን ለመንግስት የጤና ተቋማት የሚያቀርበው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሚያገኘውን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ የአዋጅ ማሻሻያ ተደርጎለታል፡፡

 

በአብዛኛው የመንግስት የጤና ተቋማት መድሃኒቶችን በሚያቀርበው ተቋሙ ተቋማት የወሰዱትን እዳ በጊዜው ባለመመለሳቸው በአሰራሩ ላይ እንቅፋት ሲፈጥርበት እንደነበር በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡

 

 ይህንን ችግር ይቀርፋል ሌሎችም ለአሰራሩ ያግዛሉ የተባለው ሃሳቦች የተካተቱበት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትና የመድኃኒት ፈንድ ለማቋቋም የቀረበ አዋጅ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡

 

ረቂቅ አዋጁን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የጤና ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወርቅሰሙ ማሞ ናቸው፡፡  

                                                                                                                                                

በተጨማሪ በተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ከተካተቱት ውስጥ አገልግሎቱ ከወረርሽኝና በቋሚነት ከሚያቀርባቸው መድኃኒቶች በተጨማሪ ለሰው ሰራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ታሳቢ አድርጎ የመጠባበቂያ ክምችት እንዲኖረው ማድረግ ይገባዋል የሚለው ተካቶበታል፡፡

 

 የጤና ተቋማት የሚወስዱትን መድሃኒት ገቢ በአግባቡ እንዲመልሱ በተቋማቸው ባለው የበጀት መጠንም ላይ ተመስርተው እንዲያዙ ማድረግ በበጀት ምክንያት የሚመጣውን የመድኃኒት ግዥ መስተጓጎል ለማስቀረት ያግዛል ተብሏል፡፡

 

አገልግሎቱ በዱቤ ላቀረበው መድሃኒት የጤና ተቋሙ ተገቢውን ክፍያ ሳይከፍል ከስድስት ወር በላይ ከቆየ በውሉ መሠረት በቀጥታ ከባንክ ሒሳቡ ላይ ተቀንሶ ወደ አገልግሎቱ ገቢ የሚደረግበት አንቀጽ በአዋጁ መካተቱን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡

 

ይህን የተሻሻለውን አንቀጽ በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ የቀረበ ሲሆን አንቀፁ ተፈጻሚ የሚሆነው ተቋማት በሚገቡት ውል መሰረት ብቻ እንጂ በግዴታ አለመሆኑ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡                                                                      

በተሻሻለው የኢትዮጵያ የመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎትና የመድኃኒት ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ የሀገሪቱን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት አምራችና በዘርፉ ከተሰማሩ ተቋማት ጋር መስራት የሚለው አጽኖት የተሰጠበት ሲሆን በምክር ቤቱ አባላትም በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

 

ምህረት ስዩም

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


 

📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g

 

 

Comments


bottom of page