top of page

ህዳር 18፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች



የብሪታንያ መንግስት ጥገኝነት ፈላጊዎችን ወደ ሩዋንዳ በመላኩ እቅዴ እገፋበታለሁ አለ፡፡


የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትሩ ጄምስ ክሌቨርሊ በአደገኛው የባህር መስመር ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞችን ለመከላከል እቅዱ አሁንም አስፈላጊነቱ የጎላ ነው ማለታቸውን ሜይል ኦን ላየን ፅፏል፡፡


ክሌቨርሊ የመንግስትን አቋም የተናገሩት ሐውስ ኦፍ ኮመንስ ለተሰኘው የአገሪቱ ፓርላማ እንደሆነ ታውቋል፡፡


ከሳምንታት በፊት የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥገኝነት ፈላጊዎቹን ወደ ሩዋንዳ የመላኩን እቅድ ህገወጥ ነው እንዳለው ዘገባው አስታውሷል፡፡


የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ መንግስት ጥገኝነት ፈላጊዎቹን ወደ ሩዋንዳ በመላክ እቅዱ አሁንም ቁርጠኛ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


እቅዱን ስራ ላይ ለማዋል መንግስት የማያደርገው ነገር እንደሌለ ለእንደራሴዎቹ ተናግረዋል፡፡



በናይጀርያ ‘’የዩናይትድ ናይጀርያ አየር መንገድ’’ አውሮፕላን በተሳሳተ ኤርፖርት ያረፈበት አጋጣሚ ምንድነው ነገሩ እያሰኘ ነው፡፡


የሀገሪቱ ሲቪል አቪየሽን መስሪያ ቤትም አጋጣሚውን እየመረመረው መሆኑን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


እንደተባለው ከሆነ አውሮፕላኑ ከሌጎስ ተነስቶ በርዕሰ ከተማዋ አቡጃ ማረፍ ይጠበቅበት ነበር፡፡


አቡጃ ማረፍ የነበረበት አውሮፕላን በ450 ኪሎ ሜትር በምትርቀዋ አሳባ ኤርፖርት ማረፉ ታውቋል፡፡


በጊዜውም ለመንገደኞቹ አቡጃ ደርሰናል የሚል ማስታወቂያ እንደተነገራቸው ታውቋል፡፡


ስህተቱ እንደታወቀ አየር መንገዱ በመጥፎ የአየር ሁኔታ አስገዳጅነት አሳባ አርፈናል ማለቱ ተሰምቷል፡፡


የሲቪል አቪየሽን መስሪያ ቤቱ መምታታቱን እየመረመረው ነው ተብሏል፡፡



ሴራሊዮን ከእሁድ እለቱ ትርምስ እያገገመች እና መልሳ እየተረጋጋች ነው ተባለ፡፡


የሀገሪቱ ርዕሰ ከተማ ፍሪታውን ከትናንት በስቲያ በተኩስ ስትናጥ ማርፈዷን ፍራስ 24 ፅፏል፡፡


በርዕሰ ከተማዋ እስር ቤት ላይ በተከፈተ ጥቃት በርካታ እስረኞች ማምለጣቸው ተጠቅሷል፡፡


የጥቃት አድራሾቹ ዓላማ ምን እንደሆነ በዝርዝር አልተጠቀሰም፡፡


ይሁንና ጉዳዩ ከመንግስት ግልበጣ ሙከራም ጋር ተያይዞ እየተነሳ ነው፡፡


ፕሬዘዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ በሰላም እና ደህንታችን ላይ የተቃጣ አደጋ ነበር ከማለት ባለፈ ዝርዝሩን አላብራሩትም፡፡


የጥቃቱ ጠንሳሾች ናቸው የተባለ ከ20 ያላነሱ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡


ሙሉ የሰዓት እላፊ ታውጆ የነበረ ሲሆን መልሶ እንዲቀጥል መደረጉን ዘገባው አስታውሷል፡፡



እስራኤል እና የፍልስጤማውያኑ የጦር ድርጅት /ሐማስ/ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እና የጥቃት መግቻውን ለተጨማሪ 2 ቀናት ለማራዘም መስማማታቸው ተሰማ፡፡


ስምምነት መደረሱን የካታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማረጋገጣቸውን NTD በድረ ገፅ ፅፏል፡፡


በተጨማሪው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እና የጥቃት መግቻ ወቅት ተፋላሚዎቹ ቀደም ብለው እንዳደረጉት ተጨማሪ ታጋቾች እና እስረኞችን ይለዋወጣሉ ተብሏል፡፡


እስከ ትናንት ሐማስ 50 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል ደግሞ 150 ፍልስጤማውያን እስረኞችን መፍታቷ ተነግሯል፡፡


ሐማስ ከ8 ሳምንታት ገደማ በፊት በእስራኤል ላይ ድንገት ደራሽ ጥቃት ባደረሰበት ወቅት ከ240 የማያንሱ ታጋቾችን ወደ ጋዛ ይዞ ማምጣቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡



የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page