የዘመን ባንክ ዋና መስርያ ቤት ማስፋፍያ ህንፃ ንድፍ ውድድርን ‘’አለበል ደስታ አማካሪ አርክቴክቶችና መሀንዲሶች’’ አሸነፈ።
ዘመን ባንክ በቅርቡ ካስመረቀው ዋና መስሪያቤት ህንፃ ጎን ለሚያሰራው ህንፃ የንድረፍ ውድድር ሲያካሂድ ቆይቷል።
በተካሄደው ውድድርም አለበል ደስታ አማካሪ አርክቴክቶችና መሀንዲሶች አንደኛ በመውጣት አሸንፏል።
የንድፉ ደራሲ ትንሳኤ ፀጋሁን መሆኗም ተነግሯል።

አሸናፊዎቹ ቅዳሜ ምሽት በተካሄደ ስነ ስርዓት ታውቀዋል።
በውድድሩ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ‘’የማ አርክቴክቸር’’ ሲሆን ሶስተኛ የወጣው ደግሞ ‘’ኢንላብስ ቢዝነስ’’ መሆናቸው ተነግሯል።
ዘመን ባንክ ከዋና መስሪያቤቱ ጎን የሚያሰራው የማስፋፊያ ህንፃ በ2264.22 ስኩዌር ሜትር ላይ የሚያርፍ መሆኑን ሰምተናል።
የሚገነባው ህንፃ ከባንኪንግ አገልግሎት በተጨማሪ፣ ሰፊ የመኪና ማቆሚያ፣ የገበያ ማዕከላት፣ የውበት መጠበቂያ፣ የስፖርት ማዕከል፣ የምግብ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጡበት ነው ተብሏል።

የዘመን ባንክን የማስፋፊያ ግዙፍ ህንፃ ንድረፍን ያሸነፉም ሆነ ብርቱ ፉክክር ያደረጉ ሽልማት እና የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷቸዋል ።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ዘበነ በንድፍ ስራ ውድድሩ ላይ እውቀታቸውን፣ ጊዜ እና ልምዳቸው ይዘው ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደርንም እንዲሁ ሲያመሰግኑ ተሰምተዋል።
ዘመን ባንክ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የፋይናንስ ተቋማት መናኸሪያ እየሆነ በመጣው ሜክሲኮ ኮሜርስ ንግድ ስራ ኮሌጅ አካባቢ ዋና መስሪያቤት ህንፃ ማስመረቁ ይታወሳል ፡፡
የህንፃው ግንባታ በ1.2 ቢሊዮን ብር እንዲሰራ ውል ተይዞ የተነገረ ሲሆን የተለያዩ ጉዳዮች የግንባታ ወጪውን 1.5 ቢሊዮን ሊያደርሱት እንደሚችሉ በወቅቱ ተነግሯል ።
አዲስ የሚገነባው የዋና መስሪያቤት ማስፋፊያ ህንፃ የወለል ብዛቱ፣ ወጪው እና ሌሎች ጉዳዮቹ ወደፊት ይታወቃሉ።
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments