top of page

ህዳር 15፣2016 - ኢትስዊች በ2015 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት 534.5 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ተናገረ

ኢትስዊች በ2015 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት 534.5 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ተናገረ።


ትርፉ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 172 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡


ይህንንም ተከትሎ የአንድ ባለ 1000 ብር አክሲዮን የትርፍ ድርሻ (Earning per Share) ወደ 719.93 ማደጉ ተነግሯል፡፡


ትርፉ የተመዘገበው የኩባንያው ገቢ እንዲጨምር በመሰራቱ እና ጥንቃቄ የተሞላበት የወጪ አስተዳደር ተግባራዊ በመደረጉ መሆኑን የኢትስዊች የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ደስታ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ስዊች የሆነው ኢትስዊች ከሰሞኑ ባ 10ኛው ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ አድርጓል።


ኢትስዊች ጠቅላላ የተከፈለ ካፒታሉ 941.5 ሚሊዮን ብር መድረሱን ተናግሯል።


በበጀት ዓመቱ በባንክ ኢንዱስትሪው መካከል በኢትስዊች አማካኝነት በአጠቃላይ የብር መጠኑ 89,762,128,279 የሆነ በድምሩ 71,433,041 እርስ በእርሱ ተናባቢ (interoperable) የሆነ የኤቲኤም ግብይት እንደተከናወነ ተናግሯል።


ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ79 መቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል።


በተመሳሳይ የ970,434 የፖስ ግብይቶች የተከናወኑ ሲሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ሲነፃጸር የ169 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡


በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ የብር መጠኑ 113,295,441,276 ብዛቱ 14,140,881 የሆነ ከባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ባንክ ወይንም አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ገንዘብ የማስተላለፍ (P2P transfer) አገልግሎት የተከናወነ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት አንጻርም የ584% ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡


በበጀት ዓመቱ ኢትስዊች 380,795 የሚሆኑ የካርድ እና የፒን ፐርሰናላይዜሽን (personalization) አገልግሎቶችን ለአባል ባንኮች የሰጠ ሲሆን ይህ አገልግሎትም ካለፈው ዓመት አንጻር የ26 በመቶ እድገት አሳይቷል።


ኢትስዊች ፈጣንና ተናባቢ የሆኑ የክፍያ ሥርዓቶችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡


ከነዚህም መካከል የብሔራዊ ክፍያ ጌትዌይ ዘመናዊ የኢኮሜርስ መድረክ ሲሆን ከደንበኞች የባንክ ሒሳብ በመገናኘት በተለያዩ የመክፈያ ዘዴዎች ማለትም ክሬዲት ካርድ፣ ዴቢት ካርድ እና በሞባይል ገንዘብ መክፍል የሚያስችል የክፍያ አማራጭ ነው፡፡


ይህም የሙከራ ስራ ለማድረግ የሚያስችለውን ፍቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አግኝቷል፡፡


ከ 12 ዓመት በፊት የተቋቋመው ኢትስዊች አክሲዮን ማህበር በሁሉም ባንኮች እና በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ በርካታ ማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች ባለቤትነት የተያዘ ነው፡፡


በዋናነት ቀላል፣ ተመጣጣኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀልጣፋ የኢ-ክፍያ መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ለችርቻሮ ክፍያ አገልግሎት ሰጪዎች ለማቅረብ የተቋቋመ መሆኑ ይታወሳል፡፡

የሸገርንወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


bottom of page