top of page

ህዳር 12፣2017 በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2030 ረሃብና ድህነትን ከዓለም ለማጥፋት የተቀመጡ ግቦች እንደማይሳኩ ከመግባባት ላይ መደረሱ እየተነገረ ነው

በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2030 ረሃብና ድህነትን ከዓለም ለማጥፋት የተቀመጡ እንደማይሳኩ ከመግባባት ላይ መደረሱ እየተነገረ ነው፡፡


ዘላቂ የልማት ግቦች በሚል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃገራት እንዲፈፅሟቸው የተቀመጡ ግቦች እንደማይሳኩ በአብዛኛው መግባባት ላይ መደረሱን በጉዳዩ ዙሪያ ሙያዊ ሃሳባቸውን የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምግብና ኒውትሪሽን ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት አሻግሬ ዘውዱ ነግረውናል፡፡


ከዚህ ላይ የተወሰኑ ማሳያዎችን እንጥቀስ በአውሮፓውኑ 2030 ረሃብን ከዓለም ማጥፋት ይቻላል በሚል ቢቀመጥም አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አፋጣኝ ድጋፍ ይፈልጋሉ፤ በአለም ዙሪያም ከ800 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል፡፡


እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP) የዘንድሮ ዓመት 2017 ሪፖርት መሰረት በአለም ዙሪያ ከ1.1 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በድህነት ውስጥ ናቸው፣ ኢትዮጵያም 68 በመቶ የተጠጋ ህዝቧ ድህነት ውስጥ ነው በሪፖርቱ መሰረት፡፡


የሥነ ምግብ ተመራማሪው እንደሚሉት በተመድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት 5 ዓመታት ብቻ ነው፤ በዚህ አካሄድ ውጥኑ ሊሳካ አይችልም፡፡

ለዚህ የበቃነውም በተለይ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወዲህ ሌሎችም ምክንቶች ተዳምረው ድህነትን ለመቀነስ ለደሃ ሃገራት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ ሃገራት ድጋፋቸውን በማቆማቸው ሂደቱ እንደተደናቀፈ ያነሳሉ፡፡


ማሳያ የሚሉትን የሚጠቅሱት ተመራማሪው ለምሳሌ በመቀንጨር ዓለም አሁንም ድረስ 24 በመቶ ላይ ናት፤ ኢትዮጵያም መቀንጨርን በሰቆጣ ስምምነት በአውሮፓውያኑ 2030 አጠፋለሁ ብላ ውጥን ብትይዝም አሁን 39 በመቶ ላይ እንደቆመች ነው ይላሉ፡፡


ኢትዮጵያ በዚህ አካሄዷ ከቀጠለች መቀንጨርን ለማጥፋት ከ50 ዓመታት በላይ እንደሚፈጅባት ያስረዳሉ፡፡


የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ፍፁም አሰፋም በበኩላቸው ዘላቂ የልማት ግቦችን እስከ ዛሬ 5 ዓመት ለማሳካት ተመድ ያስቀመጣቸው ግቦች እንደማይሳኩ መግባባት ላይ መደረሱን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ግቦቹን ለማሳካት ስራዎችን ብትሰራም የተቀመጡላትን ግቦች ልታሳካ እንደማትችና ግቦቹን ለማሳካት የቀረቡት 16 ያደጉ ሃገራት ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡


ለአብነትም ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት 6452 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ሃይል እያመነጨች ቢሆንም 48 በመቶ ህዝቧ ብርሃን አላየም፤የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት 69 በመቶ ቢደርስም ከ30 በመቶ በላዩ ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ እንዳላገኘ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራን በተመለከተ ገለፃ ባደረጉበት ወቅት በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያ ባስተናገደችው ከረሃብ ነፃ አለም መፍጠር በሚለው ጉባኤ በቀሩት 5 ዓመታት ድህነትን ለመቀነስ መሰራት አለባቸው ተብለው በመፍትሄነት የተቀመጡትን ምርታማነትን መጨመር፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ የስራ እድል መፍጠር፣ምርቶች ላይ እሴት መጨመርና ሌሎችም መሆናቸውም በማጣቀስ ዶ/ር አሻግሬ ያብራራሉ፡፡


ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምትሰራቸው ስራዎች ውጤታማ መሆን የሚችሉት በመንግስት መቼ የትኛው ስራ መሰራት አለበት የሚለው ሲታወቅና መቅደም ባለበት በተለይም ስራን ሊፈጥሩና ምርትን ሊጨምሩ በሚችሉ መስኮች ላይ ትኩረት መደረግ ሲችል ነው ሲሉም መክረዋል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page