ህዳር 11፣2017 - ኢትዮጵያ የ4.9 ቢሊዮን ዶላር የእዳ ሽግሽግ እንደተደረገላት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተናገረ
- sheger1021fm
- Nov 20, 2024
- 1 min read
ኢትዮጵያ ከነበረባት እዳ የ4.9 ቢሊዮን ዶላር የእዳ ሽግሽግ እንደተደረገላት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተናገረ።
በመንግስት የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ካሳካቸው ነገሮች መካከል አንዱ የእዳ ሽግሽግ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል።
ይህም በየዓመቱ ኢትዮጵያ ለ #ብድር ስትከፍል የነበረውን 2 ቢሊዮን ዶላር ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር እንዲቀንስላት አድርጓል ብለዋል።
በብድር ሽግግጉ የተረፈው 1 ቢሊዮን ዶላር ለሌሎች ሃገራዊ ወጪዎች እንደሚውልና ኢትዮጵያ ባለፉት 6 ዓመታትም 10 ቢሊዮን ዶላር ለአበዳሪዎቿ መክፈሏን ሚኒስትሯ ፍፁም ነግረውናል።
ኢትዮጵያ አሁን ያለባት የውጪ እዳ ከሀገራዊ ጥቅል ምርቷን( #GDP ) 13.7 በመቶ እነደሆነ ጠቅሰዋል።
ይህንንና ሌሎችም #የማክሮ_ኢኮኖሚ_ማሻሻያው ያመጣቸው ለውጦችና ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር ውይይት ተካሂዷል።
ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ፅሁፍ ያቀረቡት ሚኒስትሯ ባለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካኝ በ4.2 በመቶ ማደጉንና እድገቱ ከሌሎች ሃገራት አንፃር አዝጋሚ እንደነበር ጠቅሰው፤ በእነዚህ ዓመታት የተሳኩና ወደ ኋላ የቀሩ ጉዳዮችን አብራርተዋል።

ባለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመለወጥ የተከሄደበት መንገድ ያመጣቸው ትሩፋቶች ቢኖሩም የተሳከ ለውጥ ግን ማሳካት አለመቻሉን አንሰተዋል፡፡
የዛሬ 60 ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር በእኩል የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የነበሩት እነ ደቡብ ኮሪያ አሁን ያሉበት ስናይ የባከነ ዘመን እንደነበር ተረድተናል ይላሉ ሲል ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም በመነሳት ነው ባለፉት 60 እየተተገበሩ ያሉ ሪፎርሞች ለምን ወደ ኋላ ቀረን፤ ለሚመጣው 50 እና ከዚያ በላይ አመት የሚያሰራ ለውጥም የሚያመጣ ሪፎርም እንዴት እናድርግ ብለን የተነሳነው ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣትን ታሳቢ እንዳደረገ የሚነገርለት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአብዛኛው ትኩረቱን ያደረገው የግሉ ዘርፍ ላይ ነው ያሉት ሚኒስትሯ በተለይ ቴክኖሎጂ፣በማኑፋክቸሪንግ፣ በፈጠራ እንዲሁም በሌላው መንግስት ለመደገፍ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
በውይይቱ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎች የማክሮ የኢኮኖሚ ማሻሻያው በአብዛኛው ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመው፤ አሉብን ይስተካከልልን ያሏቸውን ችግሮች አንስተው ምክክር ተደርጎበታል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments