top of page

ህዳር 10፣2017 - ‘’የገቢ ግብር እንዲቀነስ ጠ/ሚኒስትሩን በደብዳቤ በድጋሚ ጠይቄያለሁ’’ኢሰማኮ

  • sheger1021fm
  • Nov 19, 2024
  • 1 min read

በቋሚ ደመወዝ የሚተዳደሩ ሰራተኞች አሁን ያለውን የኑሮ ጫና መቋቋም እንዲችሉ የሚከፍሉት ግብር እንዲቀነስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በደብዳቤ በድጋሚ መጠየቁን የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ተናገረ፡፡


ከዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጉዳዩ ዙሪያ እንዲያነጋግሩኝ ጠይቄ፣ በዚህም መሰረት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተን የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በጉዳዩ ላይ ጥናት አድርገው እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ሰጥተው ነበር በሏል ኮንፌደሬሽኑ፡፡


ይህንን ተከትሎ ጉዳዩ ምላሽ ያገኛል ብለን ጠብቀን ነበር ይሁንና ምላሽ ባለማግኘታችን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በድጋሚ በደብዳቤ ለመጠየቅ ተገድደናል ያሉን #የኢትዮጵያ_ሰራተኛ_ማህበራት_ኮንፌደሬሽን የውጭና ህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ አያሌው አህመድ ናቸው፡፡


አሁን ካለው የኑሮ ጫና አንፃር ደሞዝተኞች የሚከፍሉት የገቢ ግብር መነቀስ አለበት ስንል የገንዘብ ሚኒስቴርን ቀድመን ጠይቀናል የሚሉት አቶ አያሌው ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘታችን ነውም ብለዋል፡፡


ተፃፈ የተባለው #ደብዳቤ ይዘትም ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮንፌደሬሽኑ ጋር የተነጋገሩበት ችግር እንዳልተፈታና የሰራተኞች ችግር መቀጠሉን አካትቷል።

በተጨማሪም የደመወዝተኛ ሰራተኞች የግብር መነሻ የሆነው 601 ብር የግብር ህጉ በወጣበት ወቅት መነሻ ደመወዝ ነበር አሁን ግን በዚህ መነሻ የሚከፈል ደሞዝ ሳይሆር ህጉ ላይ በመሆኑ ልክ አይደለም፡፡


ተገቢው ጥናት ተደርጎ ከታክስ ነፃ የሚደረጉ ሰራተኞች ምን ያህል የሚያገኙ ናቸው? የሚከፈለው ግብርስ በመቶኛ ምን ያህል መሆን አለበት? የሚለው አሁን ካለው የብር የመግዛት አቅም ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበትም ያነሳሉ፡፡


ኃላፊው እንደሚሉት ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ በሰራተኛው ሲጠየቅ የቆየ ነው፡፡


የተፃፈው ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ገብቷል፤ እርሳቸውም ጉዳዩን ተረድተው ከሚመለከታቸው ጋር መክረውበት ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተስፋቸውን ነግረውናል፡፡


#በማክሮ_ኢኮኖሚ_ማሻሻያው የመንግስት ሰራተኞችን ለመደጎም የተደረገው ማስተካከያ የተወሰነ ይደጉማል ነገር ግን የግል ድርጅት ሰራተኞች የዚህ ተጠቃሚ አለመሆናቸው ተጨማሪ ጉዳት እንዳለው አቶ አያሌው ጠቅሰዋል፡፡


ደመወዝተኛው በሁለት መንገድ እየተጎዳ መሆኑንና ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ባልተወሰነበት ሁኔታ 601 ብር ከሚከፈለው 10% ከ10,900 ብር ተከፋይ ደሞዝተኛ 35 በመቶ ግብር ማስከፈል ፍትሃዊ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡


የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ተደረገ የተባለው የደመወዝ ጭማሪ ግብር የሚቆረጥበት በመሆኑ ተጫማሪው መልሶ ወደ መንግስት ካዝና እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይጠቅሳሉ፡፡


ምንታምር ፀጋው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page