ህዳር 10፣2017 - በ2017 የትምህርት ዘመን ለመመዝገብ ከታቀደው የተማሪ ቁጥር የተመዘገበው በ10 ሚሊዮን ያነሰ እንደሆነ ተነገረ
- sheger1021fm
- Nov 19, 2024
- 1 min read
በ2017 የትምህርት ዘመን ለመመዝገብ ከታቀደው የተማሪ ቁጥር የተመዘገበው በ10 ሚሊዮን ያነሰ እንደሆነ ተነገረ።
በመላ ሀገሪቱ በ2017 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ባሉ ትምህርት ቤቶች ከ32 ሚሊዮን በላይ #ተማሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም የተመዘገቡት ግን 21 ሚሊዮን 723 ሺህ ነው ተብሏል።
ቁጥሩ ከታቀደው የቀነሰው በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ነው ተብሏል።
ይህ የተነገረው በህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት የሰው ኃብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የትምህርት ሚኒስቴርን የበጀት ዓመቱ የ3 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በተመለከተ ከመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው።
ወደ #መምህርነት ሞያ የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን በውይይቱ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተናግረዋል።
ይህንን ለማስተካከል የተለያዩ የማትጊያ ሥርዓቶች ይዘረጋሉ ብለዋል።
#የመምህራን_ባንክ የማቋቋም ሀሳብ መኖሩን
ከነዚህ አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ይህም መምህራን በሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የራሳቸው ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ተብሏል።
የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እንደ ሀገር የመምህራን ብቃት በረዥም ጊዜ ዕቅድ ሊሰራበት እንደሚገባም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የመምህራንን አቅም ለመገንባት ከ44,000 በላይ መምህራን ሥልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።

የትምህርት ጥራትን ችግርን ለመቅረፍ በመንግሥትና #በግል_ትምህርት_ቤቶች መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ይገባልም ብለዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር፤ የዩኒቨርቲዎችን የተማሪ ቁጥር ለመጨመር ብሎ የትምህርት ጥራትን ጥያቄ ውስጥ አልከትም ብሏል።
በተያያዘም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች፤ በተማሪዎች ምገባ ተጠቃሚ እንደሆኑ ተጠቅሷል።
የሁለተኛ ደረጃ የተማሪ መፅሐፍት በሁሉም ክልሎች 1 መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ የማዳረሱ ስራም ትኩረት ከተሰጧቸው ስራዎች መካከል ነው ሲል የእንደራሴዎች ምክር ቤት ተናግሯል።
ማንያዘዋል ጌታሁን
תגובות