ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ሚያዝያ 28፣ 2013- የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት ፈረጀ

የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት ፈረጀ፡፡

ቡድኖቹን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ምክር ቤቱ በ1 ድምፀ ተዓቅቦ እና በ312 የድጋፍ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

የተጠቀሱት ቡድኖች በንጹሃን ዜጎች ላይ ጭምር ሲፈፅመኑ የቆዩት አሁንም እየፈፀሙ ያሉት ድርጊት የሽብርተኝነት ወንጀል መሆኑን የውሳኔ ሀሳቡ ያስረዳል፡፡

ውሳኔው በምክር ቤቱ ከመፅደቁ በፊት ሽብርተኛ አይደለሁም ብሎ ማስረጃ ይዞ የሚቀርብ አካል ካለ በሚል ምክር ቤቱ ጥሪ ቢያደርግም በጊዜ ገደቡ ማስረጃ ይዞ የቀረበ አካል እንደሌለም የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል፡፡

በምክር ቤቱ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የፌዴራል ዋና ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁትን ቡድኖች በገንዘብ የረዱ፣ በሚዲያ የሚያግዙ፣ አመራርና አባል የሆኑ በህግ ይጠየቃሉ ብለዋል፡፡ 

ይህ ሲደረግ ግን እንደቀደመው ጊዜ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈፀም በተሻለ መጠን ጥንቃቄ እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን ያለመከሰስ መብታቸው ያልተነሳና ሕውሃትን ወክለው በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ወንበራቸው ተጠብቆላቸው ስራቸው የቀጠሉ አባላት እንዳሉ ይታወቃልና ሕውሃት እንደ ድርጅት በሽብርተኝነት ከተፈረጀ የእነዚህ አባላት እጣ ፋንታ ምን ይሆናል ለሚለው በውሳኔ ሀሳቡ ላይ አልሰፈረም፡፡

ሸገር ዐቃቤ ሕግን ጠይቆ እንደተረዳው በምክር ቤት የቀሩትም ሆኑ ሌሎች የሕውሓት የቀድሞ አባላት ሰላማዊ እስከሆኑ ድረስ ህጉ ወደ ኋላ ሂዶ አይሰራም የሚል ምላሽ አግኝቷል፡፡

በመሆኑም ተጠያቂ የሚያደርገው ከዚህ በኋላ ሲደግፉ መገኘት እንጂ የቀድሞ አባል መሆናቸው ተጠያቂ አያደርጋቸው ተብሏል፡፡

አሁን በምክር ቤት አባልነት ያሉም ቢሆንም ሕውሃት የሚለውን ቡድን ወክለው ሳይሆን የመረጣቸው ሕዝብ ወክለው የተገኙ በመሆናቸው የሕውሃት በሽብርተኝት መፈረጅ በእነሱ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ አይኖርም መባሉን ሰምተናል፡፡ 

መንግስት ቀደም ሲል “ኦነግ ሸኔ” ሲል ይጠራው የነበረውን ቡድን  አሁን “ሸኔ” በሚል ስያሜ በሽብርተኝነት እንደፈረጀው ይታወቃል፡፡

ይህም ጥያቄ ሲያስነሳ ነበርና እኛም ዐቃቤ ሕግን ጠይቀናል፡፡

በህጋዊ በመንገድ ተመዝግቦ ኦነግ በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀስ ስላለ ከእሱ ለመለየት ነው “ሸኔ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የሚል ምላሽ አግኝተናል፡፡ 

የሁለቱ ቡድኖችን ሽብርተኝነት መፈረጅ ተከትሎት የምክር ቤቱ አባላት መንግስት  “ህውሓት”ና “ሸኔ” በንጹሃን ዜጎች ላይ ጭምር የፈፀሙት ጭፍጨፋ በዝርዝር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያስረዳ በቡድኖቹ ላይም የፀጥታ ሀይሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል፡፡

ቁልፍ ቃላት
ምላሽ