ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ለዘመን ፈተና

በእድር በማህበር…
በጀማ በደቦ፣
ቢለምድም ወገኔ…
መኖር ተሰባስቦ፣
ጨብጦና አቅፎ...
ስሞ ተሳስሞ፣
ፍቅሩን ካልገለፀ…
ባይረካም ፈፅሞ፣
“በቃ አትሰብሰቡ!
ይቅር መተቃቀፍ!
መጨባበጥ ካለ…
ያስከትላል መርገፍ፡፡
መነካካት ይብቃ !
ዋ! ብትሳሳሙ፣
መታመም አለና …
ለየብቻ ቁሙ !”
ካለማ ዘመኑ…
ጊዜ ካዘዘማ፣
በሕይወቱ ፈርዶ…
ማነው የማይሰማ?
ለመጣው ወረርሽኝ…
መድኃኒት ከታጣ፣
ማነው? በቸልታ…
ጤናውን የሚያጣ፡፡
መዋደድ ፍቅራችን…
በልባችን ካለ፣
ለዘመን ተገዝተን ….
ብንቆይም ግድ የለ…
ይኼም ያልፋልና…
እንኑር በተስፋ፣
ለጊዜ እንታዘዝ …
ትውልድ ከሚጠፋ፡፡
ተጨባብጦ መኖር…
ተጎራርሶ መጥገብ፣
ተቃቅፎ መሳሳም…
መደሰት በአጀብ፣
ወጀቡ ካለፈ…
ይመለሳል ደግሞ፣
የዛሬን ይቅርብን…
ከመማቀቅ ታምሞ፡፡
ለስሜት መግለጫ …
ከቃል በዘለለ ፣
በዓይኖቻችን ቋንቋ …
መግባባት እያለ፣
ጊዜው አስገድዶን…
በአካል ብንራራቅ፣
የፍቅር ፈገግታ…
ያቀራርባል ሳቅ፡፡
ግዴለም አንለፍ…
የዘመኑን ኬላ፣
ቸልተኛ ሆነን…
ከነገ አንጣላ፡፡
ማስተዋል ከቻልን…
ከገባን ብልሃቱ፣
ጨለማው ይበራል…
አይቀርም መንጋቱ፣
ሀብታምና ደሀ…
ቀለም ሳይለያይ፣
በዓለም ከዘመተው …
ከመጣብን ገዳይ፣
ሞትን አሸንፈን …
በሕይወት ለማምለጥ፣
እንማረክ ለውሃ…
እጆቻችን እንስጥ፡፡
ከእጃችንም በላይ...
ልባችንን እናፅዳ ፣
አምላክ እንዲያድነን…
ከመጣብን እዳ፡፡
ይቅርታህን ስጠን…
አውጣን ከመአቱ !
እንበለው ፈጣሪን…
እንፀልይ በብርቱ፡፡
ለዘመን ፈተና…
ሳለልን ምላሹ፣
ይቅር መደናገጥ…
ደርሶ መረበሹ፡፡

ወንድሙ ኃይሉ
ቁልፍ ቃላት
Wed, 03/25/2020 - 13:55