ማስታወቂያ

programs top mid size ad

እስቲ ወደራሳችን እንመልከት

ሰውዬው በተወለደበት ሀገር ኑሮውን ይገፋል አሉ፡፡ ይህ ሰው ፂሙን ማሳደግ የሚወድ አይነት ነው፡፡ እናም ይህ ዠርጋጋ ሪዙ መለያው ሆኖ፣ እሱም ወዶት ይኖራል፡፡ ይህ ሰው ምግብ ሲመገብ የተወሰነው ሪዙ ላይ ይንጠባጠባል ግን በፍፁም አፅድቶት አያውቅም፡፡ ከጊዜ ጊዜ ይህ ነገር ሲደጋገም ሪዙ ላይ የሚንጠባጠበው ምግብ ተበላሽቶ መጥፎ ጠረን ያመጣበት ጀመር፡፡ ይህ ሰው ምንድን ነው የሚሸተኝ እያለ ዙሪያውን ማሰስ ጀመረ፡፡ ከዛ ችግሩ ከከተማው ነው በማለት ወደ ሌላ ከተማ ተጓዘ፡፡ እዛም ቢደርስ ሽታው አልጠፋ ይለዋል፡፡ በመጨረሻም ከአንድ መደምደሚያ ላይ ደረሰ አለ፡፡ መደምደሚያውም ‹‹ዓለም ሸታለች ማለት ነው›› የሚል ሆነ፡፡ ግን እንደዚህ ሪዛም ሰው ወደራሳችን ማየት ተስኖን ወደ ውስጣችን መመልክት አቅቶን ትክክል ያልሆነ መደምደሚያን የምንሠጥባቸው አጋጣሚዎች በጣም እየበዙ እኮ ነው፡፡ በተመሳሳይ ቋንቋ መግባባት እኮ እየተሳነን ነው፡፡ ሁላችንም እናወራለን መሰማማት መግባባት የለምና፡፡ መጫጫህ ብቻ ወደራሳችን ማየት አንፈልግም፡፡ ከቤት እስከ ስራ ቦታ በሌላውም ኑሮአችን ችግራችንን ወደሌላው ማላከክ እንጂ ወደ ውስጣችን ማየት ችግሩ ከኔ ይሆን እንዴ ብሎ መጠየቅ የለም፡፡ ጓደኛሞች በአንድ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ያነሳሉ ከዛ እንዲህ ብታደርግስ ይለዋል አንደኛው በዛ መሠረት ያደርጋል ግን ውጤቱ በተቃራኒው የማይሆን ሊሆን ይችላል በዚህ ጊዜ አንተ ባልከኝ መሠረት እንዲህ አድርጌ ውጤቱ እንዲህ ሆነ ብትሉ ያ ጓደኛችሁ አይቀበላችሁም፡፡ ምን አልባት እኔ ባልኩት መሠረት ላይሆን ይችላል ያደረጋችሁት አሊያም እኔ መች እንዲህ አልኩኝ ብሎ እርፍ ይለዋል፡፡እንጂ መስሎኝ ነው ጓደኛዬ ይቅርታ ማለት የለም፡፡ በየጐዳናው ላይ የሚርመሠመሱትን ተሽከርካሪዎች ተመልከቱአቸው በአጋጣሚ አንዱ በአንዱ መንገድ አውቆም ይሁን በአጋጣሚ ሊገባ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተማው በጡረምባ ጩህት ይናወጣል፡፡ ጥፋተኛውም የኔ ጥፋት ነው ብሎ አያምንም ያኛውም አያልፈውም፡፡ መጫጫህ፣ እኔ ነኝ ጥፋተኛ መባባል የለም፡፡ ይህን ለማድረግ በቅድሚያ ወደራሳችን መመለስ ያስፈልገናላ፡፡ በባለ ትዳሮች መሀከል አንዳንዴ ነፋስ ገብቶ ትዳር ሠላም ሊያጣ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ጉዳዩ ከቤት አልፎ ከሽማግሌና ጐረቤት ጆሮ ይደርሳል፡፡ በዚህ ጊዜ በሉ ሠላም አውርዱ ሲባል ባል ወይም ሚስት እሱ እኮ እሷ እኮ እያሉ መጫጫህ ይጀምራሉ፡፡ አትሠማኝም አይሠማኝም ያጠፋል ታጠፋለች መባባል ብቻ ነው፡፡ ብቻ ወደራሳችን መመልከት መፍትሔ ለማግኘት ከራሳችን መጀመር ተስኖናል፡፡ ችግራችንን በራሳችን ጉያ ተሸክመን መፍትሔ ፍለጋ እንደክማለን፡፡ በክፉ ባህሪያችን በዙሪያችን ያሉ ወዳጆቻችን ሲርቁን ለምን ምን አስቀይሜአቸው ይሆን ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ የራቁትን ‹‹ምቀኞች ሁሉ›› ብሎ መፈረጁን እንመርጣለን፡፡

መፍትሔን ለማግኘት ከራሳችን መጀመር አቅቶን እስከዛሬም መላን ልናመጣ ያልቻልንባቸው ብዙ ጉዳዬች በዙሪያችን ይኖራሉ፡፡ ወደራሳችን ተመልሠን ይቅርታ ችግሩ የኔ ነው አንልም፡፡ አንዳንዴ ማጥፋታችንን ልቦናችን ቢያውቀውም እንኳን በትዳራችን ውስጥ ነፋስ እንዲገባ ያደረገውን ምክንያት ተሸክመን ሌላ የምክንያት አይነት እንደረድራለን፡፡ በየመስሪያ ቤቱ ሂዱ ያንን ሪዛም ሰው የሚመስሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በተለይ በአለቃና ከታች ባለው ምንዝር ሠራተኛ መሀከል ደግሞ ይህ ነገር በብዛት ይታያል፡፡ ከላይ ያለው አለቃ ይሄ ይሄ ነገር ይሠራ ሲል ያዛል ሠራተኛው የተባለውን ለማድረግ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ላይሟሉለት ይችላል፡፡ ግን ሲጠይቅ ማንም አይሠማውም ጊዜው ሲደርስ አለቃ ስራዬን ከየት አደረሳችሁት ይላል፡፡ አልተሠራም ሲባል ለምን አይልም መጫጫህ፣ አለፍ ሲልም አቅሙ የሚችለውን እርምጃ መወሠድን አማራጩ ያደርጋል፡፡ ለምን ስራው አልተሠራም ስራው እንዲሳካ እኔ ምን ማድረግ ነበረብኝ ብሎ የሚጠይቅ ወደራሱ የሚመለከት የለም፡፡ ፖለቲከኞቻችን አይስማሙም ችግራቸው፣ ጥፋታቸው እንደ ሪዛሙ ሰውዬ ፈጦ እየታየባቸው ለራሳቸው ግን አይታያቸውም፡፡ ለማየትም አይፈልጉም፡፡ የሚነግራቸውም አይሹም፡፡ ይህንን ደፍሮ የሚያደርግ ካለም ወዳጅ ሳይሆን ጠላታቸው ነው የሚሆነው፡፡ የኔን ሀሳብ ስማ እኔ ያልኩትን ወደህም ይሁን ሳትወድ ተጋት ማለት ብቻ ነው፡፡ ወደራሳቸው ለማየትና ሌላውን ለማዳመጥ ዝግጁ ባለመሆናቸው ሀገርና ህዝብን ይወከላሉ የምንላቸው ሰዎች የኔን ካልሠማህ የኔን ካልሠማህ ሲባባሉ ተረጋግተው ለመደማመጥ ባለመቻላቸው ጥፋቱ የኔነው ከምልማ ሞት ይሻለኛል ብለው ብዙዎች ለአንድ ሀሳብ ተነስተው መጨረሻ ላይ በተለያየ መንገድ ሲበታተኑ ታዝበናል፡፡ ሚስጥሬን አወጣብኝ ስለኔ ተናገረ በሚል ሀገር ይያዝ ሲባልም እንዲሁ በተደጋጋሚ አስተውልናል፡፡ እስቲ ከራሳችን እንጀምር ከመጫጫህ መጥተን መደማመጥ እንጀምር እንደዛ ሪዛም ሰው ችግሩንም መፍትሔውንም ተሸክመነው መላን ፍለጋ ከመድከም በስተመጨረሻም ሪዛችንን በማፅዳት ብቻ መላን ማምጣት እየቻልን ዓለም ሸታለች ማለት ነው ብለን ከመፈረጅ እንድን ይሆናል፡፡
ቁልፍ ቃላት
Tue, 12/09/2014 - 07:59