ማስታወቂያ

programs top mid size ad

የመአዘን ምት መቺውም እሱ...ለጐል ተሻሚውም እሱ

የመአዘን ምት መቺውም እሱ
ለጐል ተሻሚውም እሱ

የቅርብ ወዳጄ ነው የስራ ጫናን አሊያም በህብረት ሊሠራ የሚገባን ስራ በተለያየ ምክንያት ለብቻ መስራት የግድ ሲሆን ይህንን ለመግለፅ ክብደቱን ለማብራራት የሚጠቀማት ቃል ነች፡፡ ‹‹የመአዘን ምት መቶ ለጐል ሄዶ መሻማት ማለት ነው›› ይላል፡፡እንዲህ አይነቱ ነገር የግድ ሲሆን ጥንካሬን ማሳያ ነውና ሊደነቅ የሚገባው ነው፡፡ ከዛ ውጪ ሁሉ ባለበትና በሞላበት ሁሉን እኔው ካልሆንኩኝ ማለት ግን ትርጉሙ ሌላ ይመስለኛል፡፡ አሁን አሁን ግን ይህ የመአዘን ምት መቺውም እኔ ለጐል የምሻማውም እኔ የምንለው ነገር እየበዛ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ሌላ ሌላውን ተወት አድርጌ ሀሳቤን ነብስ ይዘሩበታል ያልኩአቸውን ነጥቦች ከማስታወቂያችን ከፊልምና ሙዚቃችን አንድ ሁለት እያልኩኝ ላንሳ፡፡
ሙዚቃ እና ሙዚቀኞቻችንን ላስቀድም፤ እንደድሮው ሰብሰብ ብሎ እንዲህ ቢሆንስ እንዲህ ብናደርገውስ ብሎ መስራት ቀርቶ አሁን በርን ዘግቶ እዛው ነገርን ሁሉ ጨርሶ ደግሞ ወደሚቀጥለው ማለፍ ሆኗል፡፡ ለማንኛውም ይህን ጉዳይ ለሌላ ጊዜ እንተወውና ወደ ሀሳባችን እንመለስ ሙዚቃችን ላይ አሁን አሁን አዳዲስ ስራ ወጣ ተብሎ ጀርባውን ገልበጥ አድርገን ነበብ ነበብ ስናደርግ ዘፋኙ፣ የግጥሙ ፀሀፊ፣ የዜማውም ፀሀፊ አንድ ሰው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ይህ አቅምን ማሳያ ከድምፅ ባለፈ በሌላውም ምሉእ መሆንን የሚያሳይ ነውና ሊበረታታ እና ሊደገፍ የሚገባው በመሆኑ እኔም እስማማለው፡፡ ግን አንዳንዴ አሁን ይሄ ስራ መሆኑ ነው! ጆሮ መቀለጃ ነው እንዴ! የሚባሉ ስራዎች እየበዙ ለመምጣታቸው እኔ በግሌ አንዱ ምክንያት ይህው ይመስለኛል፡፡ ሌሎችንም በምክንያትነት ማንሳት ቢቻልም ወጪ ለመቀነስም ይሁን በሌላው ምክንያት በእርግጠኝነት ለመናገር ባልችልም እኔው የመአዘን ምት መቺ እኔው ለጐል ተሻሚ እንሁን ማለታችን እየበዛ መምጣቱ እንዲህ አይነት ጉዳት ያለው ይመስለኛል፡፡
እናም የመጫወቻ ቦታ እና ድርሻችንን መለየቱ የተሻለ ይሆናል፡፡
ሌላኛው መአዘን ምት መቺውም ለጐል ተሻሚውም አንድ ሰው እየሆነ የመጣበት ስራ ደግሞ ማስታወቂያችን ነው፡፡ ምርትና አገልግሎት ገበያ እንዲያገኝ፤ ፈላጊው እንዲበዛ በየጋዜጣና መፅሔቱ በየሬዲዩና ቴሌቪዥኑ ይተዋወቃል፡፡ ላስተዋዋቂው ገቢን፣ ለፈላጊው አማራጭን ይሠጣል፡፡
ከዚህ ውጪ አንድን ምርት ወይንም አገልግሎት ሌላው ባለሙያ ሲያወራው እና ሲያስተዋውቀው መልዕክቱ አቅም ይኖረዋል ተአማኒነትም ያገኛል፡፡ የማስታወቂያው ህግም ይጠበቃል ብዬ አምናለው፡፡
አሁን አሁን ግን የራሳችንን ተቋም ጉድ ታዩበታላችሁ ኑ ተመልከቱት ማለታችን እየበዛ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ይሄንን ለማረጋገጥም ብዙ መልፋት አይጠበቅባችሁም ትንሽ ጊዜ ስጡና ማስታወቂያዎችን በተለይ በሬዲዮና ቴሊቪዥን የሚተላለፉትን ስሟቸው ወይንም ተመልከቷቸው፡፡ እራሴ የመአዘን ምት ልምታ እራሴ ለጐል ልሻማ ሲሉ ታዩአቸዋላችሁ፡፡
ወደ ፊልምና ትያትራችን እንሂድ እንደ አሸን ፈልተው ለመቁጠር ያስቸገሩትና በስንት ጥበቃ በረጅም ጊዜ የሚከሰቱት ስራዎች፡፡
ስለ ይዘትና ስለሌላውም ሞያዊ ነገር ብዙ ለማለት እወቀቱ ባይኖረኝም እንደ ተመልካች ግን አጨብጭበንም ተበሳጭተንም የወጣንባቸው ፊልሞች አሉና ስለሁለትም የግል ሀሳቤን ለማንሳት እችላለው፡፡ ለአሁኑ ግን ሀሳቤ እሱ አይደለምና ይቆይ፡፡ እነዚህ ከፋብሪካ እንደሚወጣ ምርት ለመቁጠር ያዳገቱን ፊልሞችና ስንት ጠብቀን ከስንት ጉጉት በኋላ ብቅ የሚሉ ትያትሮቻችን ላይም ይህ ሁሉንም እኔ ልሁን የሚባለው ነገር በስፋት ይታያል፡፡ ፊልምና ትያትሮቻችን ላይም ፀሀፊው፣ ዳይሬክተሩ፣ ተዋናዩ አንድ ሰው ሲሆን ይታያል፡፡ ይህም በሙዚቃ ስራዎች ላይ እንዳነሳነው ጥንካሬን ብቃትንም የሚያሳይ ነውና በዚህ በኩል ሊደነቅ የሚገባ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ግን የበለጠ ያማረና የተሳካ ስራን ለመስራት በተወሠነ ነገር ላይ ሙሉ ትኩረትን አድርጐ ሌላውን ለሚገባው ባለሙያ መስጠት ያሻል ከሚሉት ወገን ነኝ፡፡
 
ሌላው የበለጠ የሚያስገርመኝና እኛው የመአዘን ምት መተን እኛው ለጐል እነሻማ ማለታችን ብሶበታል ብዬ እንዳስብ ያደረገኝ ደግሞ እነዚህ ፊልምና ትያትሮች ፀሀፊያቸው አንድ ሰው ዳይሬክተሩም እራሱ፣ ተዋናዩም ያው ሰው ሆኖ ከተሠራ በኋላ ስራው ለህዝብ ጆሮ በማስታወቂያ ሲደርስም በዛው ሰው መሠራቱ ነው፡፡
ይህንንም ለማረጋገጥ ብዙ መድክም አይገባችሁም እገሌ የተባለ ፊልም አሊያም ትያትር ፀሐፊው እገሌ ዳይሬክት ያደረገው እገሌ ተዋናይ እገሌ እገሊት እያሉ የራሱን ስም ያውሠው በሠራው ማስታወቂያ መስማት መደጋገም ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡
ይህ ነገር እራሴ ካልሆንኩ ሰው የሠራው አያረካኝም በማለት ይሁን አልያም ወጪ ለመቀነስ በእርግጠኝነት ለመናገር ባልችልም ከመደጋገም ትክክለኛ ስራ መምሰል ጀምሯል፡፡ የስራውን ተአማኒነት ግን ይቀንሰዋል ብዬ አምናለው፡፡ ደግሞም ይህንን ለመስራት እውቀትና ልምዱ ኖሯቸው የተቀመጡትን ሰዎች እውቅና መንፈግም ይመስለኛል፡፡
ከማስታወቂያና ሙዚቃው ከፊልምና ትያትሩ ወጪ በሌሎች ዘርፎችም ይህ የበዛ ስምና የስራ ድርሻን ለራስ መስጠት የመጫወቻ ቦታን ለይቶ ያለማወቅ ችግር ይታያል፡፡
እናም የመጫወቻ ቦታችንን ብንለይ እኛው የመአዘን ምት መቺ እኛው ለጐል ተሻሚ ባንሆን መልካም ነው፡፡
ቁልፍ ቃላት
Tue, 08/26/2014 - 08:43