ማስታወቂያ

programs top mid size ad

አምና መሪዎቼ ሲዋኙ ባየሁ ግዜ ደስ አለኝ…

እነሆ ክረምት መጣ… ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሞቱ አመት ሞላ፡፡ ኢቲቪ በግድ አስታውሱ በግድ ዳግሞ አልቅሱ ብሎ ሙት አመት ምናምን እያለ ሆዳችንን ሊያባባ ይሞክራል እንጂ እኛማ ከሳቸው ሞት በኋላ ስንት የሚያስለቅስ ገጥሞናል፡፡ ሆድ ይፍጀው ብለን እንጂ፡፡
አሁንም ክረምት መጣ ኧረ እንደውም ወደ መጋመሱ ነው…እኛም ያኖርንበት የጠፋንን ወፋፍራም ልብስ በራሳችንና በአጋዥ ግብረሀይል ተረድተን ፈልገን አጠብን ተኳኮስን፡፡ ከአምና የተረፈ ቡትስ ጫማ ያለን እሱን ጠራረግን…የሌለንም ለሸመታ ወጣን…ምን ዋጋ አለው? …ዋጋው ጨምሯል…ንሯል!
ለአንድ ደንበኛ ቡትስ የሚጠየቀው ብር ከሆኑ ዓመታት በፊት ጋሻ መሬት ይገዛበት ነበር አሉ፡፡
በጣም እርር...አንጀታችን ቁስል…ወሽመጣችን ቁርጥ ብሎ…እንደው የት ሀገር ልሂድ? ብለን አልተማረርንም፡፡ እኛ እኮ ኩሩ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ቲማቲም እንኳ በኪሎ 25 ብር እየገዛን አይደለም እንዴ?
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በዝርክርክ አሰራር 3 ነጥብ አስቀነሰብን ሲባል እንዳላንባረቅንበት…ግብርና ሚንስቴር የቲማቲም በሽታ ሊገባ መሆኑን እያወቀ ምንም ሳያደርግ አንቀላፍቶ ይህው የ10 ሳንቲም ፌስታል(መጠሪዋ እንጂ ለካ ዋጋዋ 25 ሳንቲም ገብቷል) የማትሞላ ቲማቲም በ100 ብር ስንገዛ የፈረደበትን ፈጣሪን አማረርን እንጂ ተቋሙን ምንም አላልንም፡፡
ይበለን!
ግብርና ሚኒስቴር ልጅ…ፌዴሬሽኑ የእንጀራ ልጅ ነው እንዴ? ነው ወይስ መንግስት በፌዴሬሽኑ ጉዳይ እንደርጎ ዝንብ ጥልቅ አይልም ስለተባለ ማን አባቱ ያስጥለዋል ብለን ነው?
መተውን የመሰለ ነገር እያለ ምን አበሳጨኝ…ቲማቲም ሆይ እደጊ ተመንደጊ በኪሎ መቶ ብር ግቢ፡፡ እኔ እንደው እርሜን አውጥቻለሁ ያለቲማቲም አይኖርም እንዴ? ብያለው፡፡
ስለክረምት ነበር አይደል የማወራው?
የዘንድሮው ክረምት ለየት ያለ ነው፡፡ የናንተን ባላውቅም በተለይ እኛ ሰፈር በረዶውም አይጣል ነው፡፡ ይቀውራል፡፡ ምቱ ሃሳብን…አልፎ አልፎ ደግሞ የበሉትን ሁሉ እየበተነ የአምቦ ውሃን ስራንም ደርቦ ይሰራል፡፡
አቤት አስፓልቱ ደግሞ…ጉድ አይደል?
እመት ቻይና እጅሽ ይባረክ ብያለሁ፡፡ እውነት አሁን እሷን የመሰለ ወዳጅ ከወዴት ይገኛል? በአንድ ክፍያ መልቲ ፐርፐዝ የሆነ አስፓልት ሰርታልን መሄዷን ልብ ብላችኋል?
በጋ በጋ እንደ አስፓልት ክረምቱን ደግሞ የዋና ገንዳ ይሆናል፡፡
ያኔ አቶ መለስ ዜናዊ አስረስ የሞቱ ግዜ….ስናለቅስ ደረታችን ስንደቃ ለመሪያችን ያለንን ፍቅር ለዓለም ስናሳይ ሳምንት ከምናምን አለፈና…አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንዲሉ የእሳቸውም (የአቶ መለስ) አስክሬን ከቤተመንግስት ወጥቶ በክብር ወደ መስቀል አደባባይ ሲሄድ ከዛም ወደ ቀብር ቦታ ሲሸኝ ሰውም ባቻ ሳይሆን ሰማዩም አለቀሰ፡፡እንደጉድ ዘነበ፡፡ አስፓልቱም 2ኛ ስራውን ደርቦ መስራቱን ተያያዘ፡፡
ማን ባለስልጣን ቀረ? ከሟቹ በቀር፡፡ አባይ የተቀየሰው ወደ አዲስ አበባ በሚመስለው አስፓልት ላይ መሪዎቼ ሲምቦጫረቁ ሳይ ልቤ አላዘነም፤ እስቲ ይቅመሷት አለ እንጂ፡፡ ብዙዎቹ ማለት ይቻላል ያን ህይወት ረስተውታል፡፡
ወዳጅነታችን ውሃ ለመሻገር እስከመተዛዘል መድረሱን በዚህም የፈጠርነው የስራ እድል መንግስት በኮብልስቶን ለተደራጁት ከሰጠው እንደማይተናነስ የምናውቀው እኛ ነን፡፡
መሪዎቻችን ያንን ቀን…እንዳያልፉት የለ እያሉ…አለፉት ግን ረሱት መሰለኝ፡፡ ይኸው እኛ ተረኛዎቹ ዛሬም እንዋኛለን፡፡
ለነገሩ ይበለን!
መቸም ጣት መቀሰር ይቀናናል እንጂ ሰው አየ አላየ ብለን የጣልነው ቆሻሻ እና የደፈነው ቱቦ ገና ብዙ ያሳየናል፡፡
የራሳችን ጥፋት በሙሉ አፋችን የመንግስታችንን ስህተት እንኳ እንዳንናገር ሸብቦናል፡፡
ይበለን!
ስንዋኝ እንገናኝ ይሆናል፡፡
ቁልፍ ቃላት
Thu, 08/01/2013 - 11:48