ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ነሐሴ 01, 2005:ታሪክን የኋሊት

ነሐሴ 01, 2005

በ1960ዎቹ መጀመሪያ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን መልካም መልካሙን ለሕዝባቸው ለመናገር ብዙ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለዋል፡፡ የዛሬ 39 ዓመት በዛሬዋ እለት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉ፡፡ በዚያች እለት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ያሉበት ምክንያት እንደቀዳሚዎቹ ጊዜዎች አልነበረም፡፡ ኒክሰን ያን ዕለት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ያሉት የሀገሬ ሰዎች ሆይ ከእንግዲህ “በኃላፊነቴ አልቀጥልም” “በቃኝ” “እለቃለሁ” ለማለት ነበር፡፡ እንደዚያም አሉ፡፡ ኒክሰን እንዲህ ለማለት የተገደዱት ወደው አልነበረም፡፡ በ2ኛው የምርጫ ዘመናቸው አስቀድሞ የምርጫው ዘመቻ እንደተጧጧፈ በዋሸንግተን ዋተርጌት ወደነበረው የዴሞክራቶቹ የፖለቲካ ማህበር ብሔራዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ለፖለቲካ ማህበሩ ባዕድ የሆኑ አምስት ሰዎች ይዘልቃሉ፡፡

ለመረጃ መመንተፊያ የጽምፅ መቅረጫ ገመዳቸውን ይዘረጋጋሉ፡፡የፅህፈት ቤቱ የደህንነት ጉዳዮች ኃላፊ እጅጉን ጠንቃቃና ሲበዛ ተጠራጣሪ መሆን ወደ ዴሞክራቶቹ ቢሮ የዘለቁት ባዕድ ሰዎች ያሻቸውን አድርገው እንዲወጡ አላስቻላቸውም፡፡ ሰዎቹ ከዚያው ሳይወጡ ፖሊስ እጅ ከፍንጅ አፈፍ አደረጋቸው፡፡ ነገሩን እንደቀላል ወንጀል ለማቃለል ተሞከረ፡፡ እንደዚያ ግን አልሆነም፡፡ ጉዳዩ ሲውል ሲያድር ወደ ዋይት ሐውስ ደጃፍ ተጠጋ፡፡

ፕሬዝዳንት ኒክሰን ነገሩን በማቃለል በተቻላቸው ከራሳቸው ሊያርቁት በብርቱ ጣሩ፡፡ አልተሳካላቸውም፡፡ ካዱ፡፡ የሚያምናቸው ግን አላገኙም፡፡ ጉዱ እየፈጠጠ መጣ፡፡
የዋሸንግተን ፖስት ወሬ አጠናቃሪዎች ቦብ ውድ ዋርድና ካርል በረንስቴይ ከፌዴራል የምርመራ ቢሮ / ኤፍ.ቢአይ / በዚያን ጊዜ በይፋ ካልተጠቀሱት ምንጫቸው ያገኙትን መረጃ ዘረገፉት፡፡ ጉዱ ተዝረከረከ፡፡

ኒክሰን ከግራም ከቀኝም ከያቅጣጫው ግፊቱ በረታባቸው፡፡
ድርጊቱም የዋተር ጌቱ ቅሌት ተሠኘ፡፡
የአገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካላት ኮንግረሱም የሕግ መወሰኛው ሴኔትም በዚሁ ጉዳይ ምርመራ ተጠመዱ፡፡

ሴኔቱ በዚህ ቅሌት መነሻ ኒክሰን እንዲከሰሱ ወደሚል አቋሙ አዘነበለ፡፡

ያ- ከመሆኑ አስቀድሞ ኒክሰን ከባለ እንቁላላማ ቅርፁ የዋይት ሐውስ ድህፈት ቤታቸው ስልጣኔን በገዛ ፍቃዴ እለቃለሁ አሉ፡፡ ይሄንን ጉድ ድፍን አሜሪካ ሰማው፡፡ ወሬው ለዓለም ተዳረሰ፡፡

ሪቻርድ ኒክሰን ከዚህ ጊዜ በኋላ ዘግይተውም ቢሆን ማሩኝ አጥፍቻለሁ ሲሉ ይቅርታ ጠየቁ፡፡ በእግራቸው ምክትላቸው የነበሩት ጄሬርድ ፎርድ ተተኩ፡፡

መረጃውን ለጋዜጠኞቹ ያሾለከው የኤፍ.ቢ.አይ የቀድሞ ሹም ዊሊያም ማርክ ፌልት መሆኑን ራሱን ያስተዋወቀው ድርጊቱ ከተፈፀመ 32 አመታት በኋላ ነበር

ክስተቱ የሕግ የበላይነት እስከምን ደረጃ እንደሆነ ታየበት፡፡
በዘመናዊ የአስተዳደር ዘይቤ መገናኛ ብዙሃን በተለምዶ ከሚንቆለጳጰሰውም በላይ አራተኛው የስልጣን አካል መሆኑ በተግባር ጭምር የተረጋገጠበት ሆነ፡፡
ቁልፍ ቃላት
ምላሽ