ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ታሪክን የኋሊት/ ከዛሬ 131 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን አፄ ዮሐንስ በመተማው ጦርነት አረፉ

የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አፄ ዮሐንስ 4ኛ በወረራ መተማንና አልፎም እስከ ሳር ውሃ ተቆጣጥሮ የነበረውን የሱዳን ሰራዊት ለመዋጋት ወደ መተማ ዘመቱ፡፡አፄ ዮሐንስ ወደ መተማ ሰራዊታቸውን አስከትለው የሄዱት፣ ሰሃጢ ላይ ከጣሊያኖች ጋር የነበራቸውን ፍጥጫ ትተው ነው፡፡ሰሃጢ ላይ፣ ጣሊያኖችን ከምፅዋ ምድር ለማስወጣት ዘምተው ሳለ ድርቡሾች (የሱዳን ጦር) ወሰን አልፎ መያዙን ሰሙ፡፡ወረራውን እንደሰሙ በንጉስ ተክለ ሃይማኖት የሚመራው የጐጃም ጦር የሱዳንን ወታደሮች እርምጃ እንዲቆጣጠር አዘዙ፡፡

የጐጃም ጦር፣ ሳር ውሃ በተባለው አካባቢ ከሱዳኖችጋር ፅኑ ውጊያ ቢያደርግም አልቀናውም፡፡ንጉስ ተክለ ሃይማኖት፤ ጥቂት ራሳቸውን ሆነው ሲያመልጡ፣ አያሌ ሰራዊት ለሞትና ለምርኮ ተዳረገ፡፡በኢትዮጵያኖቹ መማረክና ሞት እጅግ ያዘኑት አፄ ዮሐንስ የሰሃጢውን ዘመቻቸውን ትተው ወደ መተማ አቀኑ፡፡አብረዋቸውም ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና መቶ ሺህ የሚደርስ ሰራዊታቸው ተከትሏቸዋል፡፡

በዛኪ ቱማል የሚመራው የሱዳን ወራሪ ጦር በመተማ ላይ ጠንካራ ምሽግ ሰርቶ ውጭውኑም በሹል እንጨትና በድንጋይ አጥሮ 60 ሺህ ይደርሳል የተባለውን ሠራዊቱን አዘጋጅቶ ተሰለፈ፡፡መጋቢት 1 ቀን ጠዋት ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት በጀግንነት እየተዋጋ የመጀመሪያውን ምሽግ ጥሶ ገባበት፡፡በሳር ውሃው ጦርነት የሞቱትን ዜጐቻቸውን ሲያዩ ቁጭት የገባቸው አፄ ዮሐንስ ራሳቸው እንደ አንድ ወታደር ሆነው በጦር ግንባር ገብተው ተዋጉ፡፡

በጦርነቱም የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል ለማድረግ በተቃረበበትና የሱዳን ሠራዊት ከምሽጉ ወጥቶ ለመሸሽ በተዘጋጀበት ወቅት አፄ ዮሐንስ እጃቸው ላይ ቆሰሉ፡፡ ቢሆንም በጦርነቱ መካከል አልወጡም፡፡እንደገና በግራ እጃቸው አልፋ ወደ ደረታቸው የዘለቀች ጥይት መታቻቸው፡፡ አጃቢዎቻቸው ወደ ድንኳናቸው ወሰዷቸው፡፡የአፄ ዮሐንስ መቁሰል ሲሰማ በኢትዮጵያኖች ዘንድ ድንጋጤ ተፈጠረ፡፡

የያዙትን ትተው ወደ ኋላ መመለስ ጀመሩ፡፡ በዚህ የተበረታታው ዛኪ ቱማል ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋገረ፡፡የንጉሰ ነገስቱ መቁሰል መዘበራረቅ የፈጠረበት የኢትዮጵያ ሠራዊትም ወደ ኋላው አፈገፈገ፡፡አፄ ዮሐንስ በመቁሰላቸው ምክንያት በማግስቱ መጋቢት 2፣ 1881 ዓ.ም አረፉ፡፡የኢትዮጵያኖቹን መሸሽ ያየው የሱዳን ሰራዊት እግር በእግር እየተከታተለ ማጥቃቱን ቀጠለ፡፡

የአፄ ዮሐንስን አስክሬን ድንኳንም ከበበው፡፡ ታላላቅ የጦር መኮንኖቻቸውና በርካታ ታማኝ ሰራዊታቸውም የንጉሳችንን አስክሬን አናስማርክም፤ እያሉ ፅኑ ውጊያ አደረጉ፡፡ ብዙዎችም በአስክሬናቸው ዙሪያ ረገፉ፡፡በመጨረሻ የደርቡሽ ጦር ድል አድርጐ፣ የአፄ ዮሐንስን አስክሬን ማረከ፡፡ አንገታቸውንም ቆርጦ ካርቱም ገበያ ላይ አዞሩት፡፡

የአፄ ዮሐንስ ሰራዊት የሞተው ሞቶ የተማረከው ተማርኮ የቀረው ወደ ደጋው አፈገፈገ፡፡ምንም እንኳ አፄ ዮሐንስ ሞተው ሰራዊቶቻቸው ተበታትኖ ደርቡሾች ጊዚያዊ ድል ቢያገኙም የኢትዮጵያን መሬት ይዘው ለመቆየት አልቻሉም፡፡
አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን የሰጡላት ኢትዮጵያም በነፃነት እስከ አሁን ኖራለች፡፡

እሸቴ አሰፋ
ቁልፍ ቃላት
ምላሽ