ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ከምንጩ ለማድረቅ

ይህቺ ‹‹ከምንጩ ለማድረቅ›› የምትል ቃል መነሻዋ ከወዴት እንደሆነ በደንብ ባላስታወስም፡፡ ዛሬ ከሚበዙት የመንግስት ቱባ ቱባ ባለስልጣኞች አንስቶ እስከታችኞቹ ድረስ ከአፋቸው ገብታ አልወጣም ብላለች፡፡ እናም በየተገኘው መድረክና አጋጣሚ ከምንጩ ለማድረቅ ሲባል ይዋላል፡፡ ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ፣ስራ አጥነትን ከምንጩ ለማድረቅ ሸብርተኝነትን ከምንጩ ለማድረቅ ብቻ ምን አለፋችሁ ከምንጩ የሚደርቀው ነገር ብዙ ነው፡፡ ለኔ ግን ለዛሬ ወጌ መነሻ እንዲሆነኝ ወደ መረጥኩት ከምንጩ እንዲደርቅ እየተሠራበት ነው ወደተባለው ጉዳዬ ልለፍ፡፡ የተለያዩ ጥናቶች ችግሩ አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ቢናገሩም ጉዳዩ ግን አይን አውጥቶ ጥናትን ሳይፈልግ በግልፅ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ከጊዜ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የሱሰኝነት ችግርና መዘዙ፡፡እናም ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት ወይንም ‹‹ከምንጩ ለማድረቅ›› መንግስት እየሠራው ነው ሲል ይሰማል፡፡
ግን በተግባር እየሆነ ያለው ሲታይ ለኔ ነገሩ እንዴት ነው የሚያስብል ሆኖብኛል፡፡ ከዚህ ትወልድን እያጠፋ ማህበራዊ ህይወትን እያመሳቀለ፣ ኢኮኖሚያዊና በጤናም ላይ ችግርን እያስከተለ ነው ከሚባለው ሱሰኝነት አንዱ የሺሻ ሱስ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተሠራ አንድ ጥናት ላይ እንደተመለከትኩት ከዛሬ 500 ዓመት በፊት በቱርክ አንዳንዶቹ እንደሚሉት ደግሞ በሶሪያና ህንድ ተጀመረ የተባለው የሺሻ ሱስ ሀገር አቆራርጦ መጤ ቢሆንም በኛም ሀገር ባህል እስከ መምሠል ደርሷል፡፡ ይህ ጥናትም ይህንን ጉዳይ በመረጃ አስደግፎ ስለአሳሳቢነቱ ተናግሯል፡፡
ግን ጥናቱ ቢወጣም፣ ከተሠራ 3 ዓመት ቢሆነውም የተወሠደ እርምጃ የለም፡፡ የጥናቱ ባለቤትን በቅርቡ አግኝቼ ስራችሁ የት ደረሰ አልኩኝ እኛ እርምጃ የመወሠድ ሀላፊነት ላላቸው ቢሮዎች ሁሉ ሠጥተናል አሉኝ፡፡ ምን ምላሽ አገኛችሁ ምን ለውጥስ መጣ ብዬ ጠይቄ የሰማሁት መልስ ግን አስቂኝ ነበር፡፡
በጥናቱ ውጤት ላይ እርምጃ ለመወሠድ የሚያስችል ሌላ ጥናት እየተሠራ ነው ነው የተባልኩት፡፡

ዛሬም ግን ሺሻ ቤቶች በየመንደሩ እንደ አሸን ይፈላሉ፡፡ አንዱ ሲዘጋ አስር ሆኖ ይከፈታል፡፡
ሌላው አስገራሚው ነገር የህጉ አፈፃፀም ላይ ያለው ልዩነት ነው፡፡ እነዚህን ቤቶች ለመዝጋት ድንገት ግብረ ሀይል ይመደብና በየመንደሩና ጉራንጉሩ እየገባ አሠሳ ይጀምራል፡፡ ወደ መሀል ከተማ ወረድ ስትሉ ደግሞ ያለ ማንም ከልካይ ከእንግዳ መቀበያ ቤቶች እስከ ትላልቅ ሆቴሎች በነፃነት ይሸጣል፣ በነፃነት ይጨሳል፡፡ ያውም ለአንድ ዙር በየጉራንጉሩ በ10 እና በ15 ብር የሚሸጠው እዛ ዋጋው ከፍ ብሎ ሰማንያም፣ ዘጠናም ፣መቶ ብር ሆኖ፡፡ እረ እንዲያውም መንግስትም Others እየተባለ ሪሴት እየተቆረጠ ገቢን ይሠበሰባል፡፡
እነዚህን ቤቶች ለማየት ብዙ መድከም አያስፈልግም ሂዱ ወደ 22፣ ወረዱ ወደ ካዛንቺስ ካሻችሁም ዝቅ በሉ ወደ ቦሌ ሞልቶላቹአል፡፡ ከዛ መለስ ብላችሁ ቴሌቪዥናችሁን ስትከፍቱ ሱሰኝነትን ከምንጩ ለማጥፋት የሚሠሩ ስራዎች ተጠናከረው ቀጥለዋል የሚል ዜናን ትሰማላችሁ፡፡
ከዚህ ውጪ ሌላው የሚያስገርመኝ እነዚህ ለዚሁ ተግባር የሚውሉት ቁሳቁሶች ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ በሞቴ ይለፉ ተብለው ገብተው በተዋበ መስታወት ውስጥ ተቀምጠው ሲሸጡ ማንም ምንም ሳይላቸው በየቤቱ ከገቡ በየመንደሩና ጉራንጉሩ ከተበተኑ በኋላ ለመቆጣጠር የሚሮጠው ነገር ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሌላውንም ማየት ይቻላል ጫት ትውልድ እየገደለ ሀገር እያጠፋ ነው ሲባል ይሠማል ይህ ችግርም ከምንጩ ሊደርቅ ይገባዋል ይባላል፡፡ ገበሬው እህል ይዘራበት የነበረውን መሬት ወደ ጫት እርሻ ሲለውጥ ማንም ምንም ሳይል ለሀገር ውስጥና ለወጪ ገበያ ሲያቀርብ ማበረታቻ ሁሉ እየተደረገለት ከመነሻው መሀል ከተማ እስከደርስ ምንም ሳይባል ነጋዴውም በወግ በወጉ ደርድሮ ሲሸጥ ግብር ክፈል እንጂ ግድ የለም እየተባለ ከመሸጫው ቤት ውስጥ ሆኖ ሲቅም የተገኘ ህገ-ወጥ ነው ይቀጣል ይባላል፡፡
እርግጥ ነው የንግድ ፈቃዱ ለሽያጭ በሚል የወጣ ቢሆንም እንደኔ አሳሳቢው ጥፋቱ እና መስፋፋቱ እንጂ ቦታው አይመስለኝም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከምንጩ ለማድረቅ ከሚሠሩ ስራዎች አንዱ በመኪና ውስጥ በመናፈሻና መዝናኛ ቦታዎች ይህንን ሲያደርጉ የተገኙን ሕገ-ወጥ እያሉ መያዝ ሆኗል፡፡
ይህንን ሳስብ ውስጤ የተፈጠረብኝ አንድ ስጋት አለ፡፡
በአንድ ወቅት በቅርብ የማውቀው ሰው ከልጄ ተደበቄ የማጨሰውን ሲጋራ ድንገት ሳልረግጥ ጥዬው አልፌ ስመለስ በአስራዎቹ እድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ልጄ ልክ እንደኔ ለማድረግ ሲሞክር አገኘውት ብሎ የነገረኝን አስታውስኩኝ ይህንንም ከዛ ለይቼ አላየውም፡፡
ይህንን ሱሰኝነትንም የመከላከሉ ትልቁ ዓላማ መጪውን ትውልድ ከዚህ የፀዳ እንዲሆን ማድረግ ይመስለኛል የሚባለውም እንደዛ ነው፡፡ እናም መተባበሩ የሁሉም ድርሻ ቢሆንም አንድ ሰው ይህን አመልህን በውጪ መፈፀም አትቸልም ከተባለ አማራጩ ሊሆን የሚችለው በመኖሪያ ቤቱ መሸሸግ ይመስልኛል፡፡ እዛ ደግሞ ልጅ ሌላውም ይህንን ክፉ ሱስ የሚጠላ አሊያም በሩቅ የሚያውቀው ይኖራል እናም እንደኔ አስተሳሰብ ይህ አማራጭ በውጪ የምታደርገውን እና ክፉ አመልህን ወደ ቤትህ ይዘህ ግባ ለማያውቁትም አሳውቅ ከማለት ለይቼ አላየውም፡፡
ከዚህ ወጪም በሌላውም ጉዳይ ተመሳሳይ መምታታቶችን ማየት ይቻላል ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ››አይነት ብዙ ጉዳዬች አሉን፡፡
በዚህ በኩል በዘንድሮው ዓመት ከጫት ሽያጭ ይህንን ያክል ገቢን አገኘን፡፡ ቡናን አስከነዳው ምናምን እያልን በኩራት እናወራለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እረ ትውልድ አጠፋ ስንል እንሠማለን፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከመነሻው እስከ ተጠቃሚው በክብርና በእንከብካቤ ተጋጉዞ ሲመጣ በሞቴ እለፍ ብለነው መጨረሻ ላይ ማጣፊያው ይጠፋናል፡፡
ይህ የበዛ ችግራችን አንዱ ማሳያ እንጂ ብቸኛው አይመስለኝም፡፡ ድካማችን ለለውጥ እሩጫችን ለውጤት ቢሆን መልካም ይመስለኛል፡፡ ብቻ ይህንን ስራ የመስራት ሀላፊነቱ የተሠጣቸሁ ከምንጩ በማድረቅ ስራ ላይ ተጠምደን አልሠማንም እንዳትሉኝ፡፡
 
 
ቁልፍ ቃላት
Tue, 07/22/2014 - 09:54