ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ታሪክን የኋሊት -ጥር 18፣ 2013

ኢጣሊያኖች፤ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ ወረራ በጀመረችበት ወቅት የመጀመሪያው የመከላከል ጦርነትና ሽንፈት የገጠማት ዶጋሊ ላይ ነበር፡፡

የአሁኗ “ኤርትራ” የዚያን ጊዜዋን ባሕረ ነጋሽ  የሚያስተዳደሩት ራስ አሉላ አባ ነጋና ሰራዊታቸው የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ተዋግተው ድል ያደረጉት የዛሬ 134 ዓመት  በዛሬው ቀን ነበር፡፡

ምፅዋን የተቆጣጠሩት ቱርኮች ተዳክመው በነበረበት ጊዜ በእንግሊዞች ርዳታ ግብፆች እንዲተኩዋቸው ተደረገ፡፡ ይሁንና ግብጾች ፤ በሱዳኖች ወይም በድርቡሾች ተቃውሞ በጦር ሀይል ስለተመቱ አቅም አነሳቸው፡፡

በከሰላም የግብፅ ሃይል በሱዳኞቹ ተከቦ ለእልቂት በተቃረበበት ወቅት እንግሊዞች ጣልቃ ገቡ፡፡ እንግሊዞቹ ወደ ኢትዮጵያው ንጉስ ነገስት አፄ ዮሐንስ መልዕክተኛ ልከው ስምምነቱ እንዲፈረም አደረጉ፡፡

ስምምነቱ፤ ኢትዮጵያ የተከበቡትን ግብጾች ከሱዳኖች ከባባ አውጥታ ወደ ሃገራቸው እንዲሄዱ እንድታደርግ ግብፆችም የምፅዋን ይዞታቸውን ለኢትዮጵያ እንዲያስክቡ ነበር፡፡

አፄ ዮሐንስ እንደስምምነቱ ቃላቸውን ፈፀሙ፡፡ ግብፅን ከሱዳን ከበባ አውጥተው ወደ ሃገራቸው ሸኗቸው፡፡

እንግሊዞችና ግብፆች ግን ስምምነቱን ክደው ኢጣሊያኖች ምፅዋን እንዲይዙ ረዷቸው፡፡ ኢጣሊያች በምስጢር በመርከብ እያጓጓዙ ወታደሮቹን ማስፈር ጀመሩ፡፡

ከምፅዋም እያለፉ የዊአን የዙላን የሰሐጢን መሬት ተቆጣጥረው ወታደር አሰፈሩባቸው፡፡

ሰላዮቻቸውንም አሰማሩ፡፡በጊዜው ከከሰላ እስከ ቀይ ባህር ያለውን የአሁኗን የኤርትራ ግዛት የሚያስተዳደሩት ራስ አሉላ ሰላዮቹን ያዟቸው፡፡

ለኢጣሊያው ጦር አዛዥ ጄኔራል ካርኖ ዠኒም የያዝከው ቦታ የኢትዮጵያ ስለሆነ ጦርህን ከዊአ እስከ ጥር 13 ድረስ አስነሳ ዙላ ያለው ወታደርም ከ1 ወር በኋላ ይውጣ፤ አለበለዚያ ወዳጅነት መቅረቱን እወቀው… ሲሉ ጥር 5፣ 1979 ማስጠንቀቂያ ላኩበት፡፡

ጀኔራል ካርሎ ዥኒ ግን ዊአ ያሉት ወታደሮች እንደማይነሱ እንዲያውም ሃይሉን እንደሚያጠናክር የኢጣሊያ መንግሥት ሌሎችን ሲያከብር ራሱም መከበር ይፈልጋል ሲል መለሰላቸው፡፡

“ፈረሴ የሚጠጣው ከቀይ ባህር ነው” የሚሉት ራስ አሉላ አባነጋ፤ በጀኔራሉ መልስ ተናደዱ፡፡ 

5000 የሚደርሰውን ሰራዊታቸው አስከትለው፤ ከከተማቸው ከአስመራ ተነስተው የጊንዳን ቁልቁለት ወርደው በጣሊያቹ ምሽግ አጠገብ ሰፈሩ፡፡

በዶጋሊ አካባቢ የሰፈረው ጦር አዛዥ ማዥር በርቲ፤  የእርዳታ ጦር እንዲላክለት ለጄኔራሉ ላከ፡፡

ሰሐጢ ካለው ምሽግ የሰፈረው ኮሎኔል ቶማስ ዲ ክሪስቶፎሪ ለርዳታ እንዲደርስለት ታዘዘ፡፡

ኮሎኔል ዲ ክሪስቶፎሪ  የጦር ትጥቁን ሲዘጋጅ አድሮ  540 የነጭ ወታደሮችና 50 የሃገር ተወላጅ ባንዳዎችን ጨምሮ 10 መድፍና 2 መትረየስ ይዞ ንጋት ላይ ዶጋሊ ደረሰ፡፡

ራስ አሉላም ወታደሮቻቸው ስፍራ አስይዘው ነበርና ኮሎኔኑ በጉዞ ላይ እንዳለ በተኩስ አጣደፉት፡፡ 

ክሪስቶፎሪ፤ ወታደሩን የመከላከያ ቦታ አስይዞ ተታኮሰ፡፡

የራስ አሉላ ሰራዊት፤ ከበባውን አጥቦ ኢጣሊያቹን አጣደፋቸው፡፡

በፍጥነት በጨበጣ ተቀላቅሎ የኢጣሊያቹን አንገት ሰየፈው፡፡

ጣሊያቹ አልቻሉም፤ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በታጠቁም የውጊያ ስልት የሚያውቁትንና የጦር ልምድ ያላቸውን የራስ አሉላ ውጊያ ሊቋቋሙ አልቻሉም፡፡

አዛዥ ኮሎኔል  ክሪስቶፎሪ  ከ22 መኮንኖች ጋር ተገደለ፡፡

418 የሚሆኑት የኢጣሊያ ወታደሮች በራስ አሉላ ሰራዊት በውጊያው ላይ ተገደሉ፡፡

ከኢትዮጵያኖቹ በኩል 1000 ያህል ሙትና ቁስለኛ እንደሆኑ ተገምቷል፡፡

ራስ አሉላ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የአውሮፓ ሰራዊት ድል ለማድረግ ቀዳሚው ሆነዋል፡፡

የጀግንነት ዝናቸውም ከኢትዮጵያ እስከ አውሮፓ የተዘረጋ ሆነ፡፡

ራስ አሉላ፤ ከደጋሊው ጦርነት 11 ዓመት በኋላ በትግራይ በነበረው የሹማምንቶች ጦርነት ቆስለው ሞተዋል፡፡

በ1974 ላይ ለራስ አሉላና ለወታደሮቻቸው ደጋሊ ላይ ሐውልት ቆሞላቸው ነበር፡፡

ነገር ግን፤ ሻዕቢያ ኤርትራ ነፃ ሃገር ሲያደርግ ሐውልቱ እንዲፈርስ አድርጓል፡፡

በዶጋሊ ለሞቱት ኢጣሊያች በሮም የቆመው ሐውልት አሁንም በፒያሳ አደባባይ ይታያል፡፡
 

ቁልፍ ቃላት
ምላሽ