ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ጥር 13፣ 2013/ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት እና ማባሪያ ላጣው ግድያ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እጃቸውን ያስገቡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠየቀ

Image
የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት

የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት እና ማባሪያ ላጣው ግድያ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እጃቸውን ያስገቡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠየቀ፡፡

ምክር ቤቱ ጥያቄውን ያቀረበው በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ መተከል ዞን በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ እና መፈናቀል አስመልክቶ ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ ነው፡፡

በዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ፣ ‹‹የጥፋት ኃይል›› ብለው ከጠሩት አካል ጋር እጃቸውን ያስገቡ አሉ ብሏል፡፡

መንግሥትም አመራሩን አጥርቶ ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች፣ እንዲሁም የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ናቸው፡፡

ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች፣ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የግድያ ጥቃት በተመለከተ ከሚመለከታቸው ጋር ተነጋግረውና መረጃዎችን አጥርተው ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ተሰጥቷቸው በነበረ የቤት ሥራ መሠረት ነው ዛሬ ለምክር ቤቱ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት፡፡

በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 2 በመጥቀስም፣ ችግሩ እየሰፋ በሄደ ጊዜ የአዋጁን የተፈፃሚነት ወሰን ማስፋት እንደሚቻል በማስታወስ፤ በመተከል ዞንም ችግሩን በመደበኛ ሕግ ለመቆጣጠር ካልተቻለና ከክልሉ አቅም በላይ ነው ተብሎ ከታመነበት በክልሉ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማስፋትና የፌደራል መንግሥት የጀመረውን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

መንግስት ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃርም ግን የተቀናጀ ስራ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ 

ለዜጎች የእለት እርዳታ ከማቀረብ ባሻገርም አካባቢዎችን አረጋግቶ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ ከመንግስት ይጠበቃል ተብሏል፡፡  

በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለውን በዜጎች የሚደርስ ግድያ መፈናቀልና ንብረት ማውደም በአስቸኳይ ስለሚቆምበት ሁኔታ፤ ተጎጂዎችም ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት የተውጣጣ ራሱን የቻለ ቡድን ተቋቁሞ በየጊዜው የሚታየውን ለውጥ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብም በውሳኔው ሀሳብ ተካቷል፡፡

የውሳኔ ሀሳቡ በምክር ቤቱ  ሰፋ ያለ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ በ4 ተቃውሞና 2 ድምፀ ተአቅቦ እንዲሁም በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

ቁልፍ ቃላት
ምላሽ