ማስታወቂያ

የሸገር ወሬዎቻችን

Sort by
ነባሪ
Post Date
2022-01-14
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሊቢያው ምርጫ በመጪው ሰኔ ወር እንዲካሄድ ሀሳብ ማቅረቡ ተሰማ፡፡ በሊቢያ ምርጫው ከጥቂት ሳምንታት በፊት መካሄድ ቢኖርበትም ሊሳካ እንዳልቻለ  ዘ ሊቢያ ኦብዘርቨር አስታውሷል፡፡ የምርጫው ውዝግብ ያለ ሁነኛ መፍትሄ እንደዘለቀ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሊቢያ ልዩ ልዑክ ስቴፋኒ ዊሊያምስ ምርጫው በሰኔ ወር እንዲካሄድ ሀሳብ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ የምርጫው መካሄድ ሊቢያን ወደ ተሟላ ብሔራዊ አንድነቷ ይመልሳታል ተብሎ ሲነገርለት ቆይቷል፡፡
2022-01-14
በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እና በሩሲያ መካከል በቤልጂየም ብራሰልስ የተካሄደው የፀጥታ እና የደህንነት ንግግር ያለ ውጤት ማብቃቱ ተሰማ፡፡ ሁለቱ ወገኖች በብራስልሱ ንግግር አቋማቸውን ማቀራረብ እንዳልቻሉ CGTN ፅፏል፡፡ ሩሲያ ኔቶ ታላላቅ የጦር መሳሪያዎቹን እንዲያርቅ ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ ግን ለዚህ የሞስኮ ጥያቄ ፈቃደኛ አልሆነም ተብሏል፡፡ የሩሲያው ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር አሌክሳንደር ፎሚን የኔቶ አቋም የግጭት ስጋቱን ሊያባብሰው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የኔቶ ዋና ፀሐፊ ጄንስ ስቶልትንበርግም ከሩሲያ ጋር በዚህ ጉዳይ ያለን ልዩነት በእጅጉ የሰፋ እና ለማቀራረብም እንዲህ ቀላል አይደለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ በሩሲያ እና በምዕራባዊያ መካከል የጦር አተካራው እየተጋጋለ መምጣቱ ይነገራል፡፡ የዩክሬይን ጉዳይም ከዋነኛ መወዛገቢያቸው አንዱ ነው፡፡
2022-01-13
የኦሚክሮን ልውጥ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በከፊል የአውሮፓ አገሮች ሊዛመት እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅት አስጠነቀቀ፡፡ የድርጅቱ ባልደረባ ዶክተር ሐንስ ክሌጅ በከፊል የአውሮፓ አገሮች ልውጡ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከ6 እስከ 8 ሳምንታት ባለው ጊዜ እንደሚዛመት መናገራቸውን CGTN ፅፏል፡፡ በአውሮፓ ባለፉት 2 ሳምንታት በልውጡ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ የተያዙ ሰዎች ብዛት በእጥፍ መጨመሩን መረጃው አስታውሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ በብዛት ተሰራጭቶ የሚገኘው ዴልታ የተሰኘው ልውጥ ዝርያ ነው ተብሏል፡፡ ከ6 እስከ 8 ሳምንታት ባለው ጊዜ በአውሮፓ አገሮች እስከ 7 ሚሊዮን ሰዎች በኦሚክሮን ልውጥ ዝርያ ሊያዙ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ኦሚክሮን ሊናናቅ እና ተቃልሎ ሊታይ አይገባም ሲል ማስጠንቀቁ ተሰምቷል፡፡
2022-01-13
በብራዚል የደረሰ የጎርፍ አደጋ በጥቂቱ 10 ሰዎችን መግደሉ ተሰማ፡፡ አደጋው የደረሰው በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል እንደሆነ CGTN ፅፏል፡፡ ጎርፉ በስፍራው በሚጥለው ዶፍ ዝናብ ምክንያት የተከሰተ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከ13,000 በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል ተብሏል፡፡ በአደጋው ከሞቱት መካከል አምስቱ የ1 ቤተሰብ አባሎች እንደሆኑ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ ሰዎቹ የሞቱት ጎርፉ ባስከተለው የመሬት መናድ መሆኑ ታውቋል፡፡ የመሬት መናዱ ተሳፍረውባት የነበረችን መኪና እንደቀበረ የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች ተናግረዋል ተብሏል፡፡
2022-01-12
የላይቤሪያ የግብርና ሚኒስቴር በምዝበራ ተከላካዩ መስሪያ ቤት እየተመረመረ መሆኑ ተሰማ፡፡ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላይ ምርመራ እየተካሄደበት የሚገኘው ሥርዓት ባልተከተለ የገንዘብ አወጣጥ ምክንያት እንደሆነ ፍሮንት ፔጅ አፍሪካ ፅፏል፡፡ እንደሚባለው የላይቤሪያ የግብርና ሚኒስቴር ሹሞች የመንግሥትን ገንዘብ ያለ ሥርዓት በማውጣት ዝራው በትነው ሆነዋል፡፡ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላይ ምርመራ የተጀመረው በድንገት መሆኑ ታውቋል፡፡ የግብርና የሚኒስትሯ ጄኒን ኩፐር ለመተባበር ዝግጁ ሆነን ሳለ መርማሪዎቹ ሳያሳውቁን ድንገት መጥተውብናል ሲሉ ማማረራቸው ተሰምቷል፡፡ የምዝበራ ተከላካዩ መስሪያ ቤት በደረሰው ጥቆማ መሰረት ጉዳዩን ከሥር መሰረቱ እንደሚያጣራው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
2022-01-12
በቡርኪና ፋሶ መንግሥት ሊገለብጡ ሲዶልቱ ነበር የተባሉ 9 የጦር ባልደረቦች ተይዘው መታሰራቸው ተሰማ፡፡ በግልበጣ ሙከራው ተካፋይ ነበሩ ከተባሉት መካከል ታዋቂ የሆኑት የቀድሞ የጦር መኮንን ኮሎኔል ሞሐመድ ዞንግራና እንደሚገኙበት ኔት ብሎክ ፅፏል፡፡ ኮሎኔሉ በመንግሥት ነቃፊነታቸው የሚታወቁ ናቸው ተብሏል፡፡ የግልበጣ ሴራው ጉዳይ መመርመር እንደጀመረ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ ፕሬዝዳንት ማርክ ክርስቲያን ታቦሬ የካቢኔ ሹም ሽር ያደረጉት ከወር በፊት እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡ ቡርኪና ፋሶም በቀጠናው የፅንፈኞች የጥቃት ዒላማ እየሆነች መምጣቷ ይነገራል፡፡
2022-01-12
ሩስያ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ድንበር ማስጠጋቷ ለወረራ ነው የሚል ስጋት አለን የሚሉት ምዕራባውያን ዩክሬይን ራሷን ከወረራ እንድትከላከል ከጎኗ እንቆማለን ባይ ናቸው፡፡ ሩስያ በበኩሏ ዩክሬንን የመውረር ሀሳብ የለኝም ትላለች፡፡ በዩክሬን ጉዳይ ውዝግባቸው የተባባሰውና እርስ በርስ እየተዛዛቱ ያሉት አሜሪካና ሩስያ ዩክሬንን ያላካተተ ንግግር እያደረጉም ነው፡፡
2022-01-11
የሶማሊያ የፖለቲካ ወገኖች የፓርላማ ምርጫው ከ40 ቀናት በኋላ እንዲካሄድ መስማማታቸው ተሰማ፡፡ በአገሪቱ የፓርላማ ምርጫው ከ40 ቀናት በኋላ የሚካሄደው ከአመት በላይ መዘግየት በኋላ እንደሆነ CGTN ፅፏል፡፡ የምርጫው ጉዳይ የተለያዩ የፖለቲካ ወገኖችን በእጅጉ ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡ እንደውም አገሪቱን ወደ ለየለት የፖለቲካ ቀውስ አዘቅት ሊጨምራት የተቃረበበት ጊዜ ነበር፡፡ የፓርላማ አባላቱ የሚሰየሙት ለዚሁ ዓላማ በሚሰየሙ የአገር ሽማግሌዎች እና የጎሣ መሪዎች አማካይነት፡፡ የፓርላማ አባላቱ በፊናቸው የአገሪቱን ፕሬዝዳንት እንደሚመርጡ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
2022-01-11
የሩሲያ ሹሞች የአገራቸው ጦር ዩክሬይንን የመውረር እቅዱም ፍላጎቱም እንደሌለው ለአሜሪካ አቻዎቻቸው ነገሯቸው፡፡ ሩሲያ እና አሜሪካ በከፍተኛ ሹሞች ደረጃ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ በፀጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች የገፅ ለገፅ ንግግር ማድረጋቸውን CGTN ፅፏል፡፡ ቀደም ሲል ምዕራባዊያን ሩሲያ ዩክሬይንን ለመውረር ተሰናድታለች ሲሉ መቆየታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡ ሩሲያ በበኩሏ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ዩክሬይንን አባሉ እንዳያደርጋት በህግ ላይ የተመሰረተ ዋስትና እንዲሰጣት ስትጠይቅ ቆይታለች፡፡ ይሁንና በአሜሪካ በኩል ይሄን የሩሲያ ፍላጎት የማሟላት አቋም አልታየም ተብሏል፡፡ ሩሲያ ዩክሬይንን ካልወረረች ተጨማሪ ማዕቀብ አይጣልባትም መባሉ ተሰምቷል፡፡ የአሜሪካዋ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊንዲ ሻርማን ንግግራችን ግልፅነት የተሞላው ነበር ብለዋል፡፡ ይሁንና በርካታ ልዩነቶቻቸው እንደነበሩ በመዝለቃቸው በወደፊቱ ሊነጋገሩባቸው እንደተስማሙ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
2022-01-11
ሰሜን ኮሪያ ተጠርጣሪ ባልስቲክ ሚሳየል መተኮሷ ተሰማ፡፡ የደቡብ ኮሪያ እና የጃፓን የጦር ሹሞች ሰሜን ኮሪያ ሚሳየል መሰል ነገር አስወንጭፋለች ማለታቸውን CGTN ፅፏል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ሚሳየል መሰሉን የጦር መሳሪያ የተኮሰችው ከሳምንት በፊት ከድምፅ የፈጠነ ሚሳየል ተኩሻለሁ ካለች በኋላ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡ ቀደም ሲል አሜሪካ ፣ ፈረንሳይ፣ አይርላንድ፣ ጃፓን፣ ብሪታንያ እና አልባንያ የሰሜን ኮሪያን የሚሳየል ሙከራ አውግዘዋል ተብሏል፡፡ በቅርቡ በሰሜን ኮሪያ አድራጊ ፈጣሪው የሰራተኞች የፖለቲካ ማህበር አገራዊ ሸንጎ ተካሂዶ ነበር፡፡ በአጋጣሚው የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የአገራችንን የመከላከያ አቅም እናሳድጋለን ብለው እንደነበር መረጃው አስታውሷል፡፡