ማስታወቂያ

programs top mid size ad

እሯጭና አሯሯጭ

በስፖርታዊ ውድድር ላይ በተለይ በሩጫው በደንብ ይታወቃል፡፡ ብዙ ሪከርዶች ስብርብራቸው የወጣው በነዚህ ሰዎች አጋዥነትና ድጋፍ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በስፖርታዊ ስማቸው አሯሯጮች ( Pace Maker) ይባላሉ፡፡ ስራቸው እንደሚታወቀው ዙር ማፍጠን እና ማክረር ከዛ ይህንን እንዲያደርጉላቸው በሚል የሚቀጥሯቸው ዋነኞቹ አትሌቶች በሚፈለገው ደረጃ ዙሩ ከጦዘላቸው በኋላ እነዚህ አሯሯጮች ስራቸውን ተወጥተዋልና ሩጫውን አቋርጠው ይወጣሉ፡፡ ከውድድሩ በኋላ በሚገቡት ውል መሠረት ገንዘባቸውን ያገኛሉ፡፡ ለማንኛውም እነዚህ አትሌቶች ቀድመውም ውድድሩን ሲጀምሩ በአሯሯጭነት የሚመዘገቡ እና የሚለዩ ስለሆነ ገና ውድድር ሲጀመር እገሌ የእገሌ አሯሯጭ ነው ብለን በቀላሉ እንለያቸዋለን፡፡ ብቻ ይህንን እዚ ጋር እንተወውና በህይወታችን ውስጥ እየገቡ እሯጭ ይሁኑ አሯሯጭ እንዳይለዩ ሆነው ዙሩን እያከረሩብን በኋላ አቋርጠው ወደሚወጡብን አሯሯጮች እንለፍ፡፡እንዴ! መለየት አቃተን እኮ የውድድሩ ተሳታፊ ናቸው ብለን አብረን እንጀምርና ወይንም ከጀመሩ በኋላ እንቀላቀላቸውና በመሀከል እብስ ይሉብናል፡፡ ለማሸነፍ የሚሮጡ ስለሚመስለን በፈጠኑ ጊዜ እኛም እንፈጥናለን እርቀውን እንዳይሄዱ እንከተላቸዋለን፡፡ እንደነዚህ አይነት አሯሯጮች በየቦታው አሉ፡፡ በስራ ቦታ የእርሶ ህመም ያመማቸው ቁስሎት የጠዘጠዛቸው መስለው አብረዋችሁ ይጮሀሉ፡፡ 

እርሶም ጉዳዩ የጋራችን ነው መላ ልንፈልግ ይገባል፤ እያሉ ውስጦ ያለውን ሀሳብ ሁሉ ይዘረግፈላቸዋል፡፡ ሚስጥሮን ሁሉ ይናገራሉ፡፡ ቆይቶ ግን እርሶ ሚስጥር ብለው ያካፈሉት ሁሉ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ከሀላፊዎችና ከሌሎቹም ጆሮ ደርሶ ያገኙታል፡፡ ገና ይሄኔ ነው እንግዲህ የውስጦን እንዳለ ሲያጠኑ የነበሩት ግለሰብ ግዳጃቸውን ተወጥተው የሚያቋርጡ አሯሯጮች እንጂ ሩጫውን ለመጨረስ የገቡ አለመሆናቸውን የሚረዱት፡፡ ከዚህ በኋላ ቢያውቁት ምን ሊፈይዱ አንዴ ነገር ተበላሽቷል፡፡
እነዚህ አሯሯጮች የሚገኙበት ሌላ ቦታን እናንሳ ከዛው ከመስሪያ ቤት አልወጣንም፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ የሚደረግ አጠቃላይ ስብሰባ ነው ብለን እንወሠድ፡፡
አንዳንዴ ከላይ ያለው አለቃና ከታች ያለው ሠራተኛ መሀከል የሀሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል እናም ከታች ያለው ሠራተኛ በዚህ ስብሰባ የመጣው ይምጣ ሀሳባችንን እናነሳለን ይባባላሉ፡፡ እንዲህ አይነቷን ነገር የጠረጠረው አለቃ ከዛው ከሠራተኛው ውስጥ እንዴት ነው እያሉ ሀሳብ የሚሠበስቡና የስብሠባውን ሀሳብ ወዳልታሠበ መንገድ እንዳይሄድ የሚያደርጉ አሯሯጮች በተለያየ ጥቅም በመያዥ ያሠማራሉ፡፡
እናም ስብሠባው ይጀመራል፡፡ ሀላፊው መናገር የፈለጉትን ተናግረው እንደጨረሱ አሁን ሀሳብ ካላችሁ እቀበላለው እጅ እያወጣችሁ፡፡
ከዛ የነዛ አሯሯጮች እጅ ከሌሎቹ ጋር አብሮ ይወጣል፡፡ ሀላፊውም ከአሯሯጮቹ ለተወሠኑት የመጀመሪያውን እድል ይሠጣሉ፡፡ ከዛም እነዚህ ሰዎች በየተራ ተነስተው የታሠበው ሀሳብ ላይ ውሃ ቸልሰውበት ቁጭ ይላሉ፡፡ የተቀሩት አሯሯጮች በጭብጨባ ያጅቡአቸዋል አመሠግናለው ብለው ይቀመጣሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ማነው ልብ ያለው የተቃውሞ ሀሳብ የሚያነሳ አሯሯጮቹ ስራቸውን ሠርተው ሩጫቸውን አቋርጠው ይወጣሉ፡፡ ሰብሳቢውም አሸናፊ ሆነው ስብሰባውን ያጠናቅቃሉ፡፡
እንዲህ አይነቱ ጉዳይ በብዙ ቢሮዎች የተለመደ ነው፡፡
በሌላውም ስራ እንደዛው ነው በተለይ ተመሳሳይ የስራ ዘርፍ ላይ በተሠማሩ መሀከል አንድ ተፎካካሪ በመምሠል ዙሩን ያከረዋል እርሶም ካልተፎካከሩ ወድቀው መቅረቶት ነውና ከፈጠነው እኩል ለመጓዝ ፍጥነቶን ይጨምራሉ፡፡
እናም በስተመጨረሻ ዙሩን ከፊት ሆኖ ሲያከር የነበረው የሚጠበቅበትን ከሠራ በኋላ ሩጫውን አቋርጦ ይወጣል፡፡
በተለይ በፖለቲካ ነክ ጉዳዬች ውስጥ እነዚህ አሯሯጮች በቁጥርና አይነት በዝተው ነው የሚገኙት፡፡
በደካማ ጐኖ ሊያግዞት፣ሊደግፎት፣ሀሳቦን ሊጋሩ የመጡ መስለው ይቀርቦታል፡፡ እርሶም ሰው አገኘው ብለው የሚያውቁትን፣ ቢሆን የሚሉትንና የሚያስቡትን ሁሉ ይዘከዝኩላቸዋል፡፡ እነሱም ልክ ነው እያሉ ሁሉን ይሠማሉ፡፡
አንዳንዴ የሚያስጠይቅ የሚያስከስስ የሚባለውን ሁሉ ሳይቀር ቀድመው እየነኩ እርሶንም ማኖ ያስነኳሆታል፡፡
ከዛም የሚጠበቅባቸውን ከጨረሱ ማኖ ካስጠፈጠፎ በኋላ ድንገት ስንት የተማመኑባቸው ሩጫቸውን አቋርጠው ይወጣሉ፡፡
እርሶም ነገር ካከተመና ካለቀለት በኋላ ከጐኖ ሆነው አለሁልህ ሲሉ የነበሩት ሁሉ ሩጫውን አብረው ለመጨረስ የገቡ ሳይሆኑ ዙሩን አጡዘው ለመውጣት የገቡ አሯሯጮች መሆናቸውን ይረዳሉ፡፡ ደጋግመው ለነኩት ማኖም አሁን ፊሽካው ተነፍቶ የእጆ ይሠጦታል፡፡
ከፊት እየሆኑ ዙሩን ሲያከሩ ሌላው ሲከተላቸው በመሀከል ድንገት ሩጫዬን ጨርሻለው ብለው አቋርጠው የወጡ ብዙ ሰዎችን እናውቃለንና እነሱ የሀሳቤ ማጠናከሪያ ይሆኑኛል፡፡
ለማንኛውም እስቲ ተመራርቀን እንጨርስ፡፡
ሩጫውን ከጀመሩ የሚጨርሱ
ካልጨረሱ የማይጀምሩትን ያብዛልን!
ቁልፍ ቃላት
Wed, 10/22/2014 - 20:28