ማስታወቂያ

programs top mid size ad

‹‹ውስንነት›› ዘመን አመጣሿ መሸወጃ


ስብሰባ ውስጥ ነን አሉ ወይንም የአንዱ መስሪያ ቤት ሪፖርት እየቀረበ ነው፡፡ ሀላፊው ከፍ ካለው ቦታቸው ላይ ተቀምጠዋል፡፡ እናም ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ መስሪያ ቤታችን በዘንድሮው ዓመት ብዙ ስራዎችን ሠርቷል፡፡ይህንን ያክል በመቶ ስኬት፣ እንትን ደግሞ ይህንን ያክል እየተባለ የስኬት መዓት ይደረደራል፡፡ ከዛም ወደ መጨረሻው ገፅ ላይ አነስ ተደርጐ ያጋጠሙ ችግሮች ወይንም በነሱ አባባል ‹‹ተግዳሮቶች›› ተብሎ አንድ አምስት ነጥብ ይዘረዘራል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ይባልና የተወሰኑ ነጥቦች ይዘረዘራሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ሳስብ ብዙዎቹ ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ ይፈጠርብኛል፡፡ ችግሩ እንደ ስኬቱ በተብራራ ቃልና በድፍረት አይነገርም እና በዘመኑ የመሸወጃ ቃሎች ተድበስብሶ ይታለፋል፡፡
ከስኬቱ አንፃር ሲታይ ችግሩ ምንም ማለት ነው ይባላል፡፡ አሊያም በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተሠሩ ስራዎች ጐን ለጐን በተወሰነ ደረጃ የአቅም ውስንነትን አይተናል ይላሉ፡፡ ግን የትኛው ውስንነት ነው?
መቼም ሁሉም ነገር የራሱ ጥግና ጫፍ ይኖረዋል፡፡ የስኬትም ይሁን የክፍተት እናም ውስንነት በሁለቱም መንገድ አለ ማለት ነው፡፡
ታዲያ ብዙዎቹ ሀላፊዎቻችን ጥንካሬውን አድምቀው ፅፈውና ድምፃቸውን ጐርነን አድርገው ተናግረው ሲያበቁ ድክመቱን አንድ ሁለት እያሉ ቆጥረው ሲነግሩን በማይገባና ችግሩን በማያሳይ ቋንቋ ውስንነት አለ ብለው ያልፉታል፡፡
በቅርቡ እንኳን የሰማነውን አንድ እውነት እናንሳ አዲስ አበባ እና ሌሎቹም የክልል ከተሞች የመብራት ችግር ከአቅም በላይ ሆኖባቸው የመብራት ያለህ ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
እንደውም ችግሩ ከመብዛቱ መብራት መጥፋቱ ማስገረሙ ቀርቶ ጥያቄው ስንት ቀን ሆነው የሚል ሆኗል፡፡ ልክ እንደ መልካም ስኬትም አንዱ መብራት ጠፋ ሲል ስንት ቀን ሆነው ብሎ ጓደኛው ሲጠይቀው አራት ቀን አሊያም አምስት ቀን ሲል ውይ ምን አላት እኔ ጋር ሁለት ሳምንት ሆነው ብሎ መመለሱም ተለምዷል፡፡
ከዚህ በኋላ ሻማ ለልደት ብቻ ነው ብንባልም እስካሁን ሻማ ለምሽትም ለልደትም እንደሆነ አለን፡፡ ብቻ ይህንን እንተወውና ወደ ጉዳያችን እንመለስ፡፡
በቅርቡ አንደኛው የመንግስት ተቋም ይህንን የመብራት መቆራረጥ ተረት የሚያደርግ መላን ፈጥሬያለው እስካሁንም እነ ቻይናና ህንድ ሲቀልዱባችሁ ከርመዋል አለን፡፡
ይህንን ሲቀለድባችሁ ነበር የተባለውን እቃ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሸንም እውነት ሲቀለድብን ከርሟል እንዴ ተብሎ ሲጠየቅ በፍፁም ብሎ መለሠ፡፡ ታዲያ ካልሆነ የኛ ችግር ምንድን ነው ሲባል የሀይል ችግር ሳይሆን ችግሩ የማከፋፈያዎቹና ማከማቻዎቹ የአቅም ውስንነት ነው ብሎን እርፍ አለው፡፡ እኛ የምንፈልገው አንድ ሁለት ተብሎ የሚቆጠር ምክንያት፡፡ ደግሞ እኮ መላ አመጣሁላችሁ ያለን ኩባንያም አለ ያለን ችግርም ያው ቃሉ ተቀያየረ እንጂ ውስንነት አይደል እንዴ?
ይህ ሁሉ ያልፍና ደግሞ እሺ እነዚህ ውስንነቶች እንዴት ነው የሚፈቱት ምን እየተሠራ ነው ብላችሁ ስትጠይቁም ተመሳሳይ ግራ አጋቢ መልስን ታገኛላችሁ፡፡
ችግሩ እንዳለ አይተናል ለመፍታትም ዝግጅት እያደረግን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው ትባላላችሁ፡፡ አሊያም ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ነው ለማለት ይቻላል ይባላል፡፡
እየተሠራ ነው፣ ሊሠራ ነው፣ተሠርቷል አሊያም አልተሠራም ግልፅ እና ትክክለኛ ምላሽ ነው ግን ምላሹ ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው ወይንም ለማለት ይቻላል ሲባል ምን ማለት ነው?
ዝግጅቱ አልቆ ስራው ተጀምሯል፤ ስራው ተጀምሮ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል ወይንስ ምን? እንደኔ እነዚህ ሀሳቦች የትኛውንም ሀሳብ የማይወክሉ እና የማያብራሩ ይመስለኛል፡፡
እናንተስ ምን ትላላችሁ?
ብቻ ሲሰራ ተሠራ ሲጠፋ ጠፋ የምንባባልበት በግልፅ የምንመሠጋገንበትና የምንወቃቀስበትን ጊዜ ያምጣልን፡፡.... እኔ በሰዓት ውስንነት ምክንያት ሀሳቤን ጨርሻለው ለማለት ይቻላል፡፡
 
ቁልፍ ቃላት
Fri, 09/05/2014 - 07:33