ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ

ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ የቆየ አና የተለመደ የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡ ልጅ ለጉርምስና እድሜ ደርሶ ያልተለመደ ባህሪ ሲያወጣ፤ቤተሰቡ ያልጠበቀውን ችግር ሲያመጣ፤ ፀብ ሆነ ፍቅር ከጎረቤት ሲጎትት ይህም ላሳደጉት ወላጆቹ እንግዳ ሲሆን፤ የልጆች እድገት ቤተሰቡን ሠላም እና የተረጋጋ ህይወት ሲያናጋ ‹ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ› ማለት እንደሚቻል የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገር እና ፍቺዎቻቸው የሚለው የብርሀኑ ገብረፃዲቅ መፅሀፍ (ገፅ 44) ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር ‹ልጅ ዕድሜው ከፍ ካለ የቤተሰቡን ሀብት ያድፋፋል ግድ የለውም› ሲል ይፈታዋል፡፡

ልጅ ሲያድግ ቤተሰቦቹ ያልለመዱትን እና ያልጠበቁትን አመል ካወጣ ወይም የቤተሰቡን ሀብት ካድፋፋ ወላጆቹ ምን እያስተማሩት ነበር ያሳደጉት? በተለምዶ ደግሞ ልጆች ለቤተሰባቸው ሳይሆን ለጎረቤቶቻቸው ወይም ለአካባቢያቸው እንግዳ የሆነ ባህሪ ሲያመጡ ችግሩ የአስተዳደግ መሆኑ ላይ ይሰመርበታል፡፡ ስለዚህ ወላጅ ልጆቹ ‹አሳዳጊ የበደላቸው›፣‹ተንጋደው ያደጉ› ተብለው እንዳይሰደቡባቸው፣ ከእነርሱ የተሻለ የተሳካላቸው ዜጎች እንዲሆኑላቸው በተግባርም ቢሆን በምኞት የተቻላቸውን ያደርጋሉ፡፡ ልጆቻቸውን የተሻለ ወደሚሉት ትምህርት ቤት ይልካሉ፤ ጥሩ ያለብሳሉ፤ጥሩ ያበላሉ፤ ያዝናናሉ፤እነርሱ ያላዩትን ለልጆቻቸው ለማሳየት ገንዘባቸውንም ሳይሰስቱ ይመድባሉ፡፡ ብቻ ቀላል የሚባል ኢንቨስትመንት አልሆነም ልጅ ማሳደግ፡፡ ቀላል ባለመሆኑም ይመስላል Rreakonomics የተባለው የSteven D.Levitt & Stephen J.Dubner መፅሀፍ ሲል የሚጠይቀው፡፡ ከልጅ አሰተዳደግ የበለጠ ወደ ሳይንስነት ያደገ ምን ጥበብ አለ? እንደማለት፡፡በልጅ አስተዳደግ ላይ ምርምሮች ይደረጋሉ፤መፅሀፎች ይታተማሉ፣የስነልቦና ባለሞያዎች ይተነትናሉ፡፡እስካሁን ግን ባለሞያዎቹን አስማምቶ የልጅ አስተዳደግን ሳይንስ ያደረገ ጥበብ አልተደረሰበትም፡፡ ጥበብ እንደቤቱ ሳይለያይ አይቀርም፡፡

አንዳንድ ባለሞያዎች የልጆችን ማንነት ሀምሳ በመቶ(50%) የሚወስነው ተፈጥሮ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ በእኛም ሀገር ‹ፈጣሪ የባረከው ልጅ› የሚል ከእምነት ጋር የተያያዘ አባባል አለ፡፡ ልጅ ከወላጅ/ካሳዳጊዎቹ ከሚማረው ይልቅ እኩዮቹ፣ከሚውልበት ቦታ አካባቢ እና ትምህርት ቤት የሚማረው ማንነቱን ለማነፅ ሰፊ ድርሻ አለው ብለው የሚከራከሩም አልጠፉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለልጆች የተቃና ማንነት፣የተሻለ የትምህርት ውጤት፣ ስነምግባር፣የፈጠራ ችሎታ፣ ሌላው ቀርቶ አድገው ስለሚኖራቸው የደሞዝ መጠን ወሳኙ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያፈሱት ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ትኩረት፣ቅጣት፣ጭቅጭቅ፣ ድርድር እንደሆነ የሚከራከሩ አሉ፡፡ እርስዎ የትኛው ወገን ትክክል ነው ይላሉ? ወላጆች በልጆቻቸው ማንነት ላይ ምን ያህል እጃቸው አለበት? ‹ልጅ ደረሰ ቤት ፈረሰ› በሚለው ሀሳብ ላይ መነጋገር ይቻላል፡፡ ልጅ ደርሶ ቤት መፍረሱ በምን ያስታውቃል? በጉዳዩ ላይ ለማውራት ማነቃቂያ ታሪክ ይፈልጋሉ? እንግዳውስ ዛሬ (ታህሳስ ፲፩) በቅዳሜ ጨዋታ ፕሮግራም ላይ መተላለፍ የሚጀምረውን ‹ወፌ ቆመች› በእውነተኛ ሁነቶች ላይ መሠረት ያደረገ የሬዲዮ ድራማ ያዳምጡ፡፡ ድራማውን ደግመው ማድመጥ ከፈለጉ www.shegerfm.com ላይ ያገኙታል፡፡


ስም - አቶ አማረ
የቤተሰብ ሁኔታ - ባለትዳር እና የ፫ ልጆች አባት
ሚስት - ለጊዜው በአካል የለችም
ስራ - ለጊዜው ተባሯል
መኖሪያ ቤት - በቅርቡ ለልማት በመነሳት ባለ ሞጃ ሰፈር(ምናባዊ ሰፈር)
ስለልጆቹ የሚያውቀው - ስማቸውን
ቁልፍ ቃላት
Sat, 12/20/2014 - 09:40