ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ኧረ በናታችሁ እንደማመጥ!!!

ብንድማመጥ ልንግባባ እንችላለን፤ ከተግባባን ደግሞ ሁሉም ጥሩ ይሆናል፡፡ ግን የምንደማመጥ ይመስላችኋልን? አብዛኛዎቻችን፣ ሌላው የሚናገረውን ከማደመጥ ይልቅ፣ የሚያሰበውን እናውቃለን ባዮች ለመሆን በመፈለጋችን ማዳመጥ ትተናል፡፡ የምናገረውን ስማ እንጂ የምትናገረውን ልስማህ ማለት አቅቶናል፡፡ ጠርጣሪ ስሜታችን አሸንፎናል፡፡ ስለዚህ የምንሰማውን ከማመን ይልቅ የተናገረውን ማንነት፣ ‹‹ልቡንና ኩላሊቱን›› ለመመርመር እንባጃለን፡፡ ስለዚህ የማዳመጥ ሃይላችንን፣የመረዳት አቅማችንን፣ ራሳችን አንቀን እየገደልነው ይመሰለኛል! ግን ለምን አንደማመጥም?

በተለይ የፖለቲካ እሳት በጋመበት ቦታ፣ ጓደኛሞች ጭምር ተረጋግቶ መደማመጥ ካቆምንም 40 እና 50 አመት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ‹‹ይቺ ሃሳብ ከየት እንደምትመጣ እናውቃለን!›› ‹‹ምን ማለት እንደፈለግህ ገብቶናል፤›› ‹‹ይኸ ሃሳብ ከአንተ በመምጣቱ አዝናለሁ …የሚሉ ውሳጣቸው የጥፋት እሳት የያዙ መልሶች መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡
በተለይ፣ መስበርና መቀንጠስ የሚያስችል ሹመት ከተሰጠው ሰው፣ እንዲህ ያለ ግብረ መልስ ሲመጣ የበትሩ ሰምበር እንደሚያሰፈራራ ትረዱታላችሁ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ወትሮም ለማደመጥ የሚፈልጉ ስላልሆኑ ብትከራኩሩቸው መታነቂያችሁን ያዘጋጁላችኋል፡፡ ‹‹እሺ›› ብትሉ አያምናችሁም፡፡ ‹‹በልብህ የምታስበውን የማላውቅ ይመስለሃል?›› እያሉ ይደነፉባችኋል፡፡
ልብ መርማሪ ነን ስለሚሉ፣ ብትናገሩም አይሰማችሁም እሺ ብትሉ አያምናችሁም፡፡ ታዲያ የሌላውን ሃሳብ መረዳት ሳይሆን ማዳመጥ እንኳ እየቆጠቆጠን እንዴት ያለ ማህብረሰብ እንደምንገነባ መገመት ይቻላል?
‹‹እኔ ብቻ ልክ ነኝ›› የሚለው መረን የለቀቀ አምልኮ፣ ስንትና ሰንት ዜጐችን እንደጨረሰ መርሳት አንችልም፡፡ አሁንስ ቢሆን ያንን ጭፍንነት አልፈነው ሄደናል? አይመስልኝም፡፡ ትክክሉ እኔ ብቻ ነኝ፤ ከእኔው ሀሳብ ካፈነገጥህ እንጠርጦስ ውረድ›› የሚለው ያገደደ አስተሳሰብ፣ ተሻሸሏል የሚል ካለ፣ ይኸን ከመስማት በላይ ደስ የሚል ነገር እንደሌለ መናገር እወዳለሁ፡፡
ሃገር የሚገነባው፣ ቤተሰብ የሚደረጀው ፣ግለሰብ የሚያድገው፣ አንዱ ከሌላው ቀሰሞ መሆኑን፣ የአንዱ ወልጋዳነት በሌላው ታርቆ መሆኑን፣ ልማዳችን አላስተማረን ይሆናል፡፡ ግን እስከመቼ በልማዳችን እያሳበብን እንኖራለን? እኛ እንደ መንግስትም፣ እንድ ቡድንም፣ እንደ ቤተሰብም፣ እንደ ሰራተኛም፣ የለከፈንን ያለመደማመጥ ደዌ፣ ባለማከማችን በእጅጉ ተጐድተናል፡፡
በየመስሪያ ቤቱ ይደረጋሉ የሚባሉ ግምገማዎች፣ ከ20 ዓመታት በኋላም፣ ጥርስ መንከሻ ቂም መቋጠሪያና ማጥቂያ አለመሆናቸውን የሚያረጋግጥልኝ ካለ፣ ለመታረም ዝግጁ ነኝ፡፡
ጉድፋችንና እድፋችንን እንዲነገር ስለማንፈልግ ለማዳመጥም ሞት ስለሚመስለን የጠላትነት አስተያየት አድርገን እንወሰደዋለን፡፡
በየመስኩ ያሉ ባለሙያዎች ፣እንዲናገሩ፣ እንዲሰሩ፣ ከመፍቀድና እድል ከመሰጠት ይልቅ፣ የሁሉም ባለሙያ ዐዋቂ እኔው ካልሁን ‹‹ሞቼ ልረፈው›› ብለው እግር ከወርች የቀፈደዱ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤት ሃላፊዎቹና ባለቤቶች፣ አንገታችንን አላነቁንም፤ ብሎ የሚያሳምነኝ ካለ ደስታውን ባልቻልሁት፡፡
‹‹አፍ ያለው ያግባሽ›› እንደሚባለው አይነት፣ በየመድረኩና በየሚዲያው እፊት እፊት ‹‹ሰለጮሁ›› እንዲሰገድላቸውና ‹‹ስምቡሌ ስምቡሌ›› እንዲባሉ በመፈለጋቸው እንቅፋት ሆነው የሚያስቸግሩን ‹‹የአፍ ሰዎች››አልበዙም፤ ብለን መናገር ብንችልማ እንዴት ደስ የሚል ወሬ በሆነ ነበር፡፡
ራሳቸውን ብቻ፣ እንደኮርማ ሻኛ የቆለሉ ሰዎች፣ በየድርጅቱ በየመስሪያ ቤቱ፣ የሚያስቸገሩት ባለማደመጣቸው ብቻ አይደለም፤ ዝም ቢሉም ለምን ዝም አለች? ምን አሰባ ይሆን? የሚል የቤት ስራ ይፈጥራሉ፡፡ የቤት ስራቸው ለራሳቸው ብቻ ባደረጉት ባልከፋ፡፡ ክፋቱ የቤት ስራቸውን ሌላው እንዲሰራላቸው መፈለጋቸው ነው፡፡
የተነገረውን ሰምተን ሃሳቡን መተቸትና መቃወም መልካም ነገር ሆኖ ‹‹ይቺ የነማ ሀሳብ እንደሆነች እናውቃታለን፤››ማለት ምን አመጣው?
ባለሙያውን በሙያው ላይ ሲናገር ለመደመጥ ካልፈለገን ስለባለሙያነት፣ ስለትምህርት ስለመረዳዳት ላንቃችን እስኪሰነጥቅ መስበክ ምን ይፈይዳል?
መሐንዲሱ ስለቅየሳ፣ ሐኪሙ ስለመድሃኒቱ፣ የታሪክ ባለሙያው ስለ ታሪክ ሲናገር አዳምጦ ከተሳሳተ በእውቀት ላይ ተመስርቶ፣ መተቸት ፣መቃወም የተገባ ነው፡፡ ግን በአብዛኛው የምናየው እንደዚያ አይደለም፡፡
ወሬና ታሪኩን ለይቶ ለመናገር የማይችልና፣ ስልጠና የሌለው ሰው፣ ‹‹ታሪክ ካለስተማርሁ እያለ ያዘኝ ልቀቁኝ›› ይላል፡፡ እንዲህ አይነቱን ሰው ጥያቄና ክርክር ካቀረባችሁለት፣ በጥቁር መዝገብ ተከተባችሁ ማለት ነው እንዲህ አይነት ሰው የሆስፒታል አስተዳደር ሰራተኛ ቢሆንም ለዶ/ሩ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ምን
አይነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ሊኖረው እንደሚገባ ቢያስተምረው አይግረማችሁ፤ መደማመጥ ያለመቻል የሚያመጣው ጉድለት ከዚህም በላይ ይከፋል፡፡
እናም እላችኋለሁ፤ እንደማመጥ፡፡ ሃሳብን መቃወምን ጠላትነት አይደለምና እንደማመጥ፣ ሁሉን እናወቃለን እያለን ከመኮፈስ ይልቅ የሌላውንም እናዳምጥ፡፡ ተደማምጠን መልካሙን መንገድ ብንይዝ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ እንደ ቁራ ለብቻ መጮህ ኪሳራ እንጂ ትርፍ ሲያስገኝ አላየንም፡፡
 
ቁልፍ ቃላት
Tue, 11/11/2014 - 20:02