ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ታክሲ መቃቃሪያም መፋቀሪያም

ከክፋት እስከ ቅንነት በታክሲዎች ውስጥ የሁለቱም ጥግ ይታያል፡፡ የፊቱን እና አንደኛውን የጋቢና ወንበር አጥፎ ከኋላ ተጠጋግታችሁ ተቀመጡ ከሚለው ሹፌር ሙዚቃ ከፍቶ እባክህ ስልክ ላውራ አንዴ ትቀንሰው ስትሉት ይህ ታክሲ እንጂ ቴሌ ንተር አይደለም እስከሚለው እና የጐማው መተኛት የነዳጁ ማለቅ ሰው ሲጭን እስከሚታየው ሹፌር ሁሉም የታክሲ ውስጥ ትዕይንት ነው፡፡ በረዳቶች በኩልም መልስ ሲሉት ከሚቆጣው ድፍን ብር ነው የያዝኩት ትዘረዝረው ሲባል መፍትሔን መፈለግን ቶ ደግሞ ሊነጅሰኝ ገባ ብሎ ለፀብ እስኪሚጋበዘው አልፎም ትርፍ ለመጫን ካልተጠጋህ ወርደህ በሌላ ሂድ ብሎ እስከሚደነፋው ሁሉንም ይህቺው ሰሚያዊ እና ነጭ የተቀባች ታክሲ ይዛለች፡፡ በተሳፋሪው በኩልም ሌላ ቦታ የገጠመውን ችግር በረዳትና ሹፌር ላይ በመጮህ ለመወጣት የገባ ከሚመስለው ለሆነውም ላልሆነውም ታሪፍህን አሳየኝ እያለ ነገር እስከሚያከብደው እንዲሁም ሁሉም ረዳትና ታክሲ ሹፌር ያው ነው ‹‹ፀብና ገቢ አታሳጣኝ›› ብሎ ፀልዮ ነው ጠዋት ከቤቱ የሚወጣው ብሎ ማመን ቀና ለሚያናግረውም ቀና የማይመልሠው ሁሉንም በዚህች ታክሲ ውስጥ ታገኛላችሁ፡፡
ለማንኛውም ችግር ላለብን ቀናነትን እና ታጋሽ ልቦናን ይስጠን ብለን ወደ ሌላኛው ጉዳያችን እንለፍ፡፡
ልክ እንደክፋቱ እና አለመግባበቱ ሁሉ የፍቅር የመተዛዘን ጥግም እኮ እንደኔ እዚህቺው ታክሲ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡
ለምን ይህ መተዛዘኑ ታክሲ ውስጥ ብቻ የሚለው ደግሞ ይገርመኛል፡፡
ለሀሳቤ ማጠናከሪያ እንዲሆነኝ አንድ ሁለት እያልኩኝ ምሳሌ ላንሳ፡፡ታክሲ ውስጥ የሚተዋወቅ ሰው ድንገት ሲገናኝ አሊያም በሌላ ቦታ ተገናኝቶ ወደ ታክሲ ሲገባ ሁሌም የሚታይ አንድ ትዕይንት አለ፡፡ ሂሳብ ለመክፈል የሚደረግ ‹‹የውልህ ረዳት›› ይላል አንዱ ወደ ኪሱ እጁን እያስገባ ‹‹አይደለም ና እኔ ጋር›› ይላል ሌላኛው ከዛ ‹‹እንዳትቀበለው፣መልስለት፣ ይህው እኔ ጋር›› የሚሉ ምልልሶች ይቀጥላሉ፡፡ አሁን እንዲህ አይነት እኔ ካላደረግኩኝ ካልከፈልኩኝ አይነት ግብ ግብ በዚህ ጊዜ ከየት ይገኛል፤ ከታክሲ ውስጥ እንጂ፡፡
ለሰው መራራትና ማዘናችንስ ድንገት ወዳለንበት ታክሲ በእድሜ የገፋ አዛውንት ወይንም አካል ጉዳተኛ አሊያም ነፍሰ ጡር ከመጣ የምንገባበት አይደል እንዴ የሚጠፋን፡፡ እሱ አይመቾትም እዚህ ጋር ይቀመጡ፡፡
እሱ ፀሀይ ነው ነይ እኔ እነሳለው እዚህ ጋር ቁጭ በይ፣ ከኋላ ተጣብቀው ለአራት አይሆንም ኑ እዚህ ጋር የሚሉ ቀናነቶችስ መገኛቸው የት ነው ታክሲ ውስጥ አይደል እንዴ፡፡
ሌላም መጨመር እንችላለን አዲስ አበባ ካሉአት ሚኒባስ ታክሲዎች 8 ሺህ ያክሉ በየቀኑ በስራ ላይ መሠማራት ይችላሉ ከዚህ ውስጥ 6 ሺህ ገደማው ይሠማራሉ 12 ሰው በአንዴ መጫን ደግሞ ገደባቸው ነው ተብሎ ተቀምጧል፡፡
አንዳንዴ በሹፌርና ረዳት አልጠግብ ባይነት ወይንም በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት እነኚህ ታክሲዎች ከተባለው ቁጥር በላይ ይጭናሉ ድንገት በጉዞ ላይ ሳሉ ከፊት ለፊት ትራፊክ ፖሊስ ከተመለከቱ ቀጣይ ጥያቄ እባካችሁ ትርፎች ተባበሩን ውረዱልን አሊያም ትራፊክ ፖሊሱን አልፋችሁ ተሻግራችሁ ጠብቁን የሚል ነው፡፡
ታዲያ በዚህ ጊዜ ችግር የለም አንተ ከምትቀጣ በማለት የተባለውን የሚያደርጉ በጠራራ ፀሀይና ዝናብ ወርደውና መንገድ ተሻግረው ትክክል ላልሆነ ነገር እንኳን የሚተባበሩ ቀና ሰዎች የሚገኙትስ እዚህቺው ሰማያዊና ነጭ ቀለም የተቀባች ታክሲ ውስጥ አይደል እንዴ?
ሌላው አንዳንዴ ረዳት ከሹፌር ባለመግባባት አሊያም በሌላ ምክንያት ሹፌር ረዳትን አሰናብቶ ብቻውን ለመስራት ይገደዳል፡፡
ይህቺ ነገር ብዙውን ጊዜ ጠዋትና ማታ ነው የምታጋጥመው በዚህ ጊዜ ያለን ተባባሪነት ረዳት ሆነን ለማገልገል ሂሳብ ሰብስበን አንዲትም ሳናጓድል ለማስረከብ ያለን ተባባሪነት ይህም መገኛው ታክሲ ውስጥ ነው፡፡ አንድ ሁለቴ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ሹፌር ትርፍ ጭኖ ኖሮ በአጋጣሚ ትራፊክ ፖሊስ ከፊት ሲያዮ ለመተባበር ረዳት የሆኑትው ተሳፋሪዎች ድርጊቱ (ትርፍ መጫኑ) ስህተት መሆኑን ቀድሞ ቢያውቁም ሹፌሩ እንዳይቀጣ በሚል ባትሪ ስር እስከመተኛት ሲደርሱ ሁሉ ተመልክቻለው፡፡ የዚህ ሁሉ መተዛዘን መገኛው ደግሞ ታክሲ ውስጥ ነው፡፡
ታክሲ ውስጥ ስለሚታይ ፍቅርና መልካምነት ብዙ ማለት ይቻላል፡፡
ግን ይህን መልካምነት በሌላውም ህይወታችን መተርጐም ለምን ተሳነን ከታክሲው ስንወርድ ጥለነው መውረዳችን ለምን ይሆን የሚል ጥያቄ ይፈጥርብኛል፡፡
ስለ ታክሲ ስናስብ የረብሻና አለመግባባት እንዲሁም የንትርክ ቦታ አድርገንስ ማየት መልመዳችን ለምን ይሆን?
ይህንን መልካምነትና ቀና አሳቢነት የእውነት የሚኖሩት ብዙ ቢሆኑም ልክ እንደከፈልነው ሂሳብ ይህንኛውን ማንነት እዛው ታክሲ ውስጥ ጥለነው የምንወርድም ትንሽ አይደለንም፡፡
ታክሲ ውስጥ ለማናውቀው ሰው ይህንን ያክል መልካምነት ማሳየት ከቻልን በተቀረው ህይወታቸን ይህንን መኖርና መድገሙ ለምን ከባድ ሆነብን?
ታክሲ ላይ የምናሳየውን ቀናነትና ተባባሪነት በተቀረው ኑሮአችን ውስጥ መድገሙ ለምን ይከብደናል?
ከቤተሰቦቻችን ጋርስ ታክሲ ላይ ያሳየነውን አይነት ታዛዥነትና ሰው አክባሪነት እንዲሁም ቅን አስተሳሰብን መድገሙ ከባድ የሚሆንብን ለምንድን ነው?
በስራ ቦታስ ታክሲ ውስጥ አንተ ከምትጐዳ በሚል ትክክል ላልሆነው ነገር ሁሉ ከለላ እየሠጠን የሌላውን ክፍተትም እየሸፈንን በስራ ቦታችን በሌላውም ይህንን መድገም ለምን ይከብደናል?
በኔ በኩል ታክሲ ውስጥ ጠብና ግጭት ብቻ ሳይሆን የፍቅር እና መተባበር ጥግም አለና፡፡
የታክሲ ውስጥ አይነት ፍቅርን ያብዛልን እላለው፡፡
ቁልፍ ቃላት
Fri, 10/31/2014 - 05:41