ማስታወቂያ

programs top mid size ad

አዲስ ዓመት መጣ የቋጠርካትን አውጣ

አዲስ ዓመት አዲስ በመሆኗ ትፈራለች እንጂ በደንብ አብጠርጥረን ካየናት ከእንቁነቷ ጣጣዋ የሚብስ ይመስለኛል፡፡ ክፍያ የሌላት ጳጉሜን አስከትላ መጥታ ልክ አግብታን ስታበቃ የበዓል ሽርጉድ ወጪን ታስከትልብናለች፡፡ ቤተሰብ ልጅ ካለ ደግሞ አዲስ ልብስ ፣አዲስ ጫማ እረ ምኑ ቅጡ፡፡ ግን የምንበዛው ሺህ አመት አይኖር በሚል አሊያም ገና በዓመቱ መጀመሪያ የምን ማማረር ነው፣ ገና በዓመቱ መጀመርያ ሮሮ ከጀመርኩኝ ዓመቱን ሙሉ አይለቅኝም በማለት ሁሉን ዋጥ አድረገን የቋጠርናትን ሆጭ እናደርግላታለን ለአዲስ ዓመት፡፡ አዲስ ዓመት መቼ በዚህ ብቻ ትላቀንና በዓሉን አለፍ እንዳልን ትምህርት ይመጣል፡፡ ለወሮች ዝግ ሆነው የሠነበቱት ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፡፡ አዲሱ የአዲስ አመት የወጪ ምዕራፍም አፏን ከፍቶ ወደ እርሶ ይመጣል፡፡
መቼም ከዓመት ዓመት የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ ነገር እንደሆነ እንደናፈቀን ቀርቷል፡፡ በየቦታው የሚለጠፈው ነገር ሁሉ በኑሮ እና በእቃ ውድነት አለያም በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የዋጋ ማስተካከያ አድርገናል የሚል ነው፡፡ ደግሞ ቃሉ ጭማሪ አይባልም ‹‹ማስተካከያ›› ነው፡፡

ሰው ግራ እያገቡ እና ለብቻው እንዲያወራ እያደረጉ ማስተካያ፡፡ ለነገሩ ነጋዴዎቻችንም ይህቺን ዋጋ እየጨመሩ ማስተካከያ አድርገናል ማለትን የለመዱት ከመንግስት ይመስለኛል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጨምሮ ማስተካከያ የትራንስፖርት ታሪፍን ከፍ አድርጐ ማስተካከያ በሌላው ጭማሪ አድርጐ ማስተካከያ አድርጌያለው የሚለን መንግስት ነው፡፡ ቆይ እሱን ተወት እናድርገውና ይሄ የትምህርት ቤት ክፍያና የቁሳቀስ ወጪ ነገር አፋጣኝ መላ የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ እንዴ እንደዋዛ ሀምሌና ነሰሴን ተማሪው አርፎ ሲመለስ የሚጠየቀው የምዝገባ፣ ወርሀዊ ክፍያ በጣም አስደንጋጭ እየሆነ እኮ ነው፡፡ መቼም በዚህ ጊዜ በቃ ማስተማር አልችልም አቅም የለኝም ተብሎ ልጅን ከቤት ማስቀመጥ አይታሠብ ነገር፡፡ ደግሞ ከምዝገባውና ከወርሀዊ ክፍያው ውጪ ትምህርት ቤቶቻችን አሟሉ እያሉ መጠየቅ የጀመሩት የቁሳቁስ አይነት ደግሞ ግራ የሚያገባ እየሆነ ነው፡፡ እንዴ ልጄን ወደ ትምህርት ቤት ነው ወደ ሌላ ቦታ ነው የምልከው ብለው እንዲያስቡም እያደረገ ነው፡፡ እንደ ሩጫ ሲከብድ አቋርጦ አይወጣ ነገር ትምህርት ነው፡፡ ያውም ለውድ ልጅ የሚደረግ፡፡

ደግሞ እኮ መንግስትም ቢሆን የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ተገቢ አለመሆኑን እና የተጋነነ መሆኑን በተደጋጋሚ በተለያየ መንገድ ሲናገር ይሰማል፡፡ ግን እርምጃ መውሠዱ ላይ ‹‹እንቃወማለን›› ብሎ እንደመናገሩ የተበረታ አይመስለኝም፡፡
ዛሬ ዛሬ ለመያዝ እና ለመቆጣጠር እንኳን ያስቸግራሉ ምን አድራሻ አላቸውና የሚባሉ የንግድ አይነቶችን ሁሉ መንግስት ተቆጣጣረ ሲባል እየሠማን እነዚህ በደንብ ተደላድለውና ለቁጥጥርም ተመቻችተው ያሉ አልጠግብ ባይ ትምህርት ቤቶችን መቆጣጠሩ ክብደቱ ምኑ ላይ እንደሆነ አልገባኝም፡፡ በፊት ይህ አስደንጋጭ የሚባል የትምህርት ቤት ጭማሪ ቅንጡ የሚባሉት ትምህርት ቤቶች ላይ ተደረገ ሲባል ነበር የምንሠማው አሁን ግን ይህ ክፉ በሽታ መካከለኛና አነስተኛ የሚባሉት ጋርም ደርሷል፡፡
ደግሞ ሰሞኑን አንድ የሸገር አድማጭ ደውለው ልጄን ትምህርት ቤት ላስመዘግብ ስል አቅርብ ተብዬ ተጠየቅኩኝ ብለው የነገሩን የቁሳቁስ መዓት ልጆን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ ከሰዓት አይደለም ለወራት የሚመለስ አይመስሎትም፡፡ ምዝገባው እሺ ይሁን ሀይ ባይ እስኪመጣ በልጅ አይጨከንምና አስመዘገብን ደግሞ የዚህ ሁሉ ቁሳቁስ መዓት ምንድን ነው ነበር ያሉት ደዋዩ፡፡ ምን እንደተጠየቁ ልዘርዝርላቹ፡፡ ሰባት እርሳስ፣ ሁለት መቅረጫ፣አምስት ሶፍት፣ሦስት ላጲስ፣ ሁለት ሳሙና ፣ሦስት ግሉ (ማጣቢቂያ)፣ አንድ ፓኬት ከለር፣ ሁለት ክላሰር፣ ሁለት ፋስትነር አስራአንድ ባለ ሃምሳ ሉክ ደብተር፣ አንድ የስዕል ደብተር፣ አንድ መቀስ፡፡ ያሳያችሁ ከዛ ስር ነቃይ ክፍያ በኋላ ትምህርት ለመጀመር ቀለል አድርገው አሟሉ ያሉአቸው ቁሳቁስ ይሄ ነው፣ ያውም በአንዴ፡፡ 

የሚያስገርመው ይህንን ሁሉ እንዲያሟሉ የተጠየቁት ደግሞ የኬጂ ተማሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የትምህርት መሳሪያዎች ወሳኝና የግድ ሊሆኑ ይችላሉ ግን ቢያንስ ቀስ በቀስ መሆን የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ እንደ ኔ ልጄን ይህንን ሁሉ ቁሳቁስ አስከትዬ ወደ ትምህርት ቤት ስልከው እዛው የሚሠነብት አሊያም እድሜው ደርሶ የራሱን ህይወት ለመምራት ከቤት ተሠናብቶ የሚወጣ እንጂ ከሰዓት የሚመለስ መስሎ አይሠማኝም፡፡ ማጋነን ባይሆን ባለኝ ጀምሬ ቀስ በቀስ አድጋለው የሚሉ የመንደር ሱቆች ሁሉ ይህንን ያክል እቃ በአንድ ጊዜ ላይዙ ይችላሉ፡፡ ወይስ ይህ ትምህርት ቤት ከኋላ መስኮት ቢጤ ከፍቶ ሱቅ ሊከፍት አሊያም በጊዜዋ የንግድ ቋንቋ እህት ኩባንያ ምናምን በሚል የትምህርት ቁሳቁስ መሸጫ ሊከፍት አስቦ ይሆን? ብቻ ነገሩ ሁሉ ግርም የሚል ነው፡፡ ዛሬ ገና ትምህርቱ ሳይጀመር ባለ ትምህርት ቤቶች እንዲህ ከጨከኑብን ተቆጣጣሪውም መልሱ ዝም ጭጭ ከሆነ ነገ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቹን የነገው የቤት ስራችሁ መቶ መቶ ብር ይዞ መምጣት ነው፡፡ ደግሞ እንዳትረሱ ከአስር የሚታረም ነው አይሉአቸውም ትላላችሁ፡፡
 
ቁልፍ ቃላት
Thu, 10/02/2014 - 08:25