ማስታወቂያ

programs top mid size ad

እቅድ ዶሮ...አፈፃፀም ሽሮ

ይህቺን አባባል ማን እንደተናገራትና የት እንደሰማዋት ባላስታውስም ሀሳቤን ትገልፀዋለችና ርእስ እንድትሆነኝ መረጥኳት፡፡ አዲሱ ዓመት መጣ፣ ባለፈው ሳምንት 2006ዓ.ም ስንለው የነበረው ዓመት 2007 ዓ.ም ሆኖ ከሱም ላይ ዛሬ 6ኛው ቀን ሊነሳለት ነው፡፡ እናም 2007 ከ359 ቀኖች በኋላ አሮጌ የሚለው መጠሪያ ይለጠፍለታል፡፡ መንግስት ሰኔ 30ን የበጀት መዝጊያ ሀምሌ አንድን የአዲስ የበጀት ዓመት መጀመሪያ ብሎ ይጠራዋል፡፡ በዚህ ሰሞንም የአሮጌው ዓመት ስራ ግምገማ የአዲሱ በጀት ዓመት እቅድ ወሬ ይበዛል፡፡ ከታቀደው ምን ያክሉ በየዓመቱ ከዳር እንደሚደርስ ግን ሁላችን የምናውቀውና የምንሠማው ነው፡፡ ልክ እንደመንግስት እኛም አዲስ አመት ሲመጣ እቅድ አንድ ሁለት እያልን የእቅድ አይነት እንደረድራለን፡፡ 
በአዲሱ ዓመት የተጣላዋቸውን እታረቃለው ያስቀየምኳቸውን ብቻ ሳይሆን ያስቀየሙኝንም ጭምር፣ ከገባሁበት የመጠጥ፣ የጫት፣የሲጃራ፣ የአደንዛዥ እፅ ሱስ ነፃ እሆናለው፣ ትምህርቴን ካቆምኩበት እቀጥላለው፣ ትዳር እይዛለው፣ ልጅ እወልዳለው ወ.ዘ.ተ ብቻ የእቅድ አይነት ይደረደራል፡፡
ግን ከምናቅደው ምን ያክሉን በዓመቱ መጨረሻ ከዳር እናደርሰዋለን አሊያም የምናቅደውስ ምን ያክል የምንፈልገውንና የተዘጋጀንበትን ነው ብለን ስንጠይቅ ታሪኩ ሌላ ይሆናል፡፡
የምንበዛውም በአዲስ ዓመት ይታቀዳል ሲባል ሠምተን እንጂ ተዘጋጅተን የምናቅድ አይመስለኝም እናም ዓመቱ መጨረሻ ላይ እንዴት ነው ሲባሉ ሞከርኩ አልተሳካልኝም ይላሉ፡፡
ደግሞም በብዞዎቻችን የአዲስ አመት እቅድ ተብለው የሚቀርቡት ሀሳቦች ዓመትን መጠበቅ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡
አሁን የተጣሉትን ለመታረቅ አዲስ ዓመትን መጠበቅ ምን የሚሉት ነው?አዲስ አመት ሲመጣ ዓመቱን ሙሉ ገና ከሩቁ ሲተያዩ መንገድ ይቀይሩ የነበሩ የቀድሞ ወዳጆች በዚህ ጊዜ ይቅር ይባባላሉ፡፡
ሌላው የሚያስገርመው ይህ ከሆነ በኋላ ሳምንት እንኳን ሳይቆይ እነዛው ሰዎች ሌላ ፀብ ውስጥ ይገባሉ፡፡ አንዳንዴም እነዛው በአዲስ ዓመት ይቀር የተባባሉት ይሆናሉ መልሠው ፀብ ውስጥ የሚገቡት እናም አንዳንዴ ሳስበው እነዚህ ሰዎች ቀድመው ያሰቡትን እቅድ እረስተው ለመጪው ዓመት ይቅር የሚሉትን ሰው ከአሁኑ ማዘጋጀቱን የተያያዙት ሁሉ ይመስላሉ፡፡
ሌላው በአዲስ አመት መግቢያ ብዙዎቹ የአዲስ አመት እቅዳችን ብለው የሚያነሱት ደግሞ የግል ህይወታቸውን የተመለከተ ነው ላጤ ከሆኑ ትዳር መያዝ ልጅ መውለድ ምናምን ይላሉ፡፡
ይህን ሳስብ በአንድ ወቅት የሠማሁት ቀልድ ትዝ አለኝ፡፡ ልጁ በቃ ትዳር ለመያዝ ወስኛለው ይላል፡፡
ጓደኛው በሠማው ተደስቶ ደስ ይላል ግን ማንን ልታገባ ነው ሲለው እሱን ገና አላወቅኩም ብሎ ይመልሳል፡፡
የኛም የምንበዛው እቅድ እንዲሁ ይመስለኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ያላዘጋጀነው አሁን ከየት ይመጣል፡፡
ዓመቱን ሙሉ የቀረቡትን ሲያርቅ የነበረ ፣ነገሩ ሁሉ ከአንድ ቀንና ለሊት ያልዘለለ የሆነው ሁሉ አዲስ ዓመት መጣ በሎ የዘንድሮ እቅዴ ትዳር መያዝ ነው ይላል፡፡ እረ ከዚህም አልፎ የልጅ አባት መሆንንም የሚጨምርበት ብዙ ነው፡፡
ሌላው ብዙዎቻችን አዲስ አመት መጣ ብለን እቅድ እያልን በተደጋጋሚ የምናነሳው ደግሞ ዙሪያችንን ከበበን የሱስ ክምር መውጣትን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሰሞኑን የናንተው ሬዲዬ ላይ የተወራውን አንድ ወሬ ሠምታቸሁታል? አዲስ አበባ ለአዲሱ ዓመት የደስ ደስ ከአንዱ ፋብሪካ ብቻ የስምንት ሚሊየን ብር አረቄ ጠጣች የሚለውን ቁጥሩ ካለፈው ዓመት ጨምሯልም ነበር የተባለው፡፡ ለማንኛውም እኛ ወደ ሀሳባችን እንመለስ እናም አዲስ አመት ሲመጣ ከዚህ በኋላ መጠጥ በደረሰበት አልደርስም፣ጫት ለፍየል ይሁን ብያለው፣ ሲጃራን በአይኔ አያሳየኝ፣ ሌላውንም እንዲሁ እንላለን በአጠቃላይ በአዲሱ ዓመት ሱስ ደህና ሠንብት ብለን እናቅዳለን፡፡
ግን ለአንዳንዶቹ ቢሳካላቸውም ለሚበዙት ከማቅድ ባለፈ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም፡፡ ቀድመን ያልተዘጋጀንበት አዲስ አመት መጣ ብለን ስላቀድን እንዴት ሊሳካ ይችላል፡፡
ሱስን ለማቆም ህክምናውም፣ በውስጡ ያሉትም ሲናገሩ እንደሚሠማው ዝግጅት፣ ውሳኔ እንዲሁም ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ አንድም ዝግጅት ሳናደርግ እንዴት ሊሳካልን ይችላል?
እናም በሌላውም ቢሆን አዲስ አመት መጣ ብለን ሳይሆን ለውጡ እንደሚያስፈልገን አምነን እና ተዘጋጅተን ብናቅድ መልካም ነው፡፡
ይህን ማድረግ ስላለቻልን ነው በዓመቱ መጨረሻ እራሳችንን ስንገመግመው ‹‹እቅድ ዶሮ አፈፃፀም ሽሮ›› ሆኖ የምናገኘው፡፡
ቁልፍ ቃላት
Fri, 09/19/2014 - 06:48