ማስታወቂያ

programs top mid size ad

ቻው ቻው አንተ ሠልፋም ዓመት

ስለጊዜ ስናስብ ስለዘመን ለውጥ ስናወራ በዘመን እና ጊዜ ውስጥ አብረው የመጡና ያለፉ እንዲሁም ጊዜ ጥሎአቸው የሄደ ክስተቶችም አብረው ይነሳሉ፡፡ እኔ... ያጠፋውን አጥፍቶ ያቀናውን አቅንቶ እብስ ሊል ከጫፍ ስለደረሰው 2006ዓ.ም ሳስብ ከውስጥም ከውጪም በተለያየ ምክንያት መሠለፋችን የበዛበት ዓመት ሆኖ እንዳለፈ ይሠማኛል፡፡ ከውጪ የብዙዎቹ መነሻ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነበር፡፡ ከአፍሪካ እንደምሳሌ የነግብፅና፣ሊቢያ የነናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ የተቃውሞ ሠልፍ፤ከተቀረው ዓለም የነቱርክና ታይላንድ የነግሪክና ፓኪስታን የተቃውሞ ሠልፎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ብራዚል እንኳን ታላቁን የአለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታን አስተናግዳ ያጠናቀቀችው በዚሁ በህዝባዊ ተቃውሞ ታጅባ ነው፡፡
ወደኛው የውስጥ ጉዳይ ስንመለስም 2006 ሠልፋም ዓመት ነው ብዬ አስባለው፡፡

በተለያየ ምክንያት አውቀነውም ይሁን ሳናውቀው ተሠልፈናል፡፡ በፖለቲካውም ቢሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎች የጠሩአቸው ህዝባዊ የተቃውሞ ሠልፎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በተደጋጋሚ በዚው በሠልፋም ዓመት ተካሂዶአል፡፡
ያላት የከተማ ትራንስፖርት አማራጭ ቁጥር ከህዝቧ ቁጥር ጋር አልጣጣም ብሏት በተለይ በስራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት የተኮለኮለ ህዝብን ማየቱን የተለማመደችው አዲስ አበባ ነዋሪው ከታክሲ ግፊያ ወደ ሰልፍ እንዲሸጋገር ያደረገችው በዚው በ2006 ሠልፋም ዓመት ነው፡፡ መነሻው ከሜክሲኮ አካባቢ እንደሆነ የሚነገርለት የታክሲ ሰልፍ ዛሬ ተለምዶ ጠዋትና ማታ መሠለፍ ነው፡፡ በግርግር ከኪስ አውላቂዎች የጠበቀን የታክሲ ሠልፍ አንዳንዴ ደግሞ የሠልፉ እርዝመት የ1 ብር ከ50 ሳንቲም መንገድ ያክል ተቀጣጥሎ ሀሞታችንን ፍስስ ሲያደርገውም ከርሟል፡፡

መታየት ከጀመረ ሰንበትበት ቢልም በየዳቦ ቤቱ በተለይ ምሽት ላይ ዳቦ ሸምቶ ለመግባት ረጃጅም ሠልፍ መታየቱም በዚህ ሰልፋም ዓመት የባሠበት ይመስለኛል፡፡ እንዴ እረ ምን ይሄ ብቻ! ለስንዴ፣ ለስኳርና ለዘይትም የተሠለፍናቸው ሠልፎችስ? በየቀበሌውና ሸማቾች በራፍ እንደጉድ አይደል እንዴ የተሠለፍነው፡፡

በየነዳጅ ማደያውስ የተሠለፍነው ለቤት ፍጆታችን ጀሪካኖቻችንን ይዘን አሽከርካሪውም መኪናውን ሠልፍ አስይዞ በተለይ በወሩ መጨረሻ ከ25 እስከ ከ26 በኃላ ገና ለገና ነዳጅ ይጨምሯል አልያም ይጠፋል በሚል የመኪናው ሠልፍ የጉድ ነው፡፡
በየባንኮቹ ለቤት ምዝገባ ለ40/60 ለ20/80 እና ለ10/90 በሚል ለስንት ቀን ተሠለፍን ያ ጊዜ አለፈና ደግሞ ገንዘብ ለመስጠት ሌላ ሠልፍ፡፡
ኔትዋርክ የለም፤ደካማ ነው፤ መብራት ጠፋ እየተባልን ገንዘብ ለመክፈል እንዲሁም ለመላክና ለመቀበል በየባንኩ ስንሠለፍም ከረምነው፡፡
ወደ እስፖርታችን እንለፍ መቼም ዘንድሮ ለአፍሪካ ዋንጫና ለዓለም ዋንጫውም ትንሽ ቀረብ ማለት የቻልንበት ደጋፊውም ከነማንቼና አርሴ ጊዜውን ሸርፎ ስለዋሊያዎቹ ለማውራት የቻለበትም ዓመት ነበር፡፡ ታዲያ በእግር ካሱም ይህቺ ነቃ ነቃ ማለት መምጣቷን ተከትሎ ካምቦሎጆአችንም ወደ ውስጥ በሚገቡ ሠልፈኞች ተጨናንቆ ነበር፡፡ ኳሳችንማ ሙሉ ሌት ከቀን የዘለቀ የደጋፊዎች ሠልፍንም አሳይቶናል፡፡
መቼም ቢሆን በዙሪያቸው ተመጋቢ ተመልካችና አድናቂ የማያጡት ስጋ ቤቶቻችን በፆም መግቢያና መውጪያ የሚሠለፍላቸው መብዛቱም ዘንድሮ ብሶበታል፡፡ ዝነኛ ከሚባሉት ልኳንዳ ቤቶቻችን እስከ አነስተኛዎቹ የቀበሌ ቤቶች በፆም መግቢያና መውጪያ ወቅት በሠልፍ ሲጨናነቁ ተመልክተናል፡፡
ሌላው ዓመቱን ሙሉ ሲያሠልፈን የከረመው ደግሞ የውሃ ችግር ነው፡፡ ከየቧንቧችን መምጣቷ ብርቅ የሆነብን ውሃ እዚህ ሰፈር መጥታለች ሲባልና ጀሪካኖቻችንን ተሸክመን ስንጓዝ እሷን ብለው ከየአካባቢው የመጡ በቁጥር ሲበዙ ሠልፍ ስንገባ ዓመቱ አለፈ፡፡
በየአካባቢው የተቀመጡት ነጫጮቹ የውሃ ማጠራቀሚያዎች ዙሪያም እነሰም በዛም ለተራ የሚሠለፍ አልጠፋም፡፡
ብቻ ምን ያልተሠለፍንበት አለ፡፡ የነሱ የመምጫ ጊዜ ብርቅ እየሆነ ወርሃዊ የመክፈያ ጊዜያቸው ቶሎ ቶሎ የሚመጣው መብራትና ውሃ እንዲሁም ስንት ሲታማ የከረመው ስልክም በአገልግሎታቸው እያበሳጩን ለወርሃዊ ክፍያቸው ሲያሠልፋን ከርመዋል፡፡
ለግብር፣ ለፊልምና ትያትር እንዲሁም ለሙዚቃ ኮንሠርት እንደከዚህ ቀደሙ ዘንድሮም ደጅ ጠንተናል፣ ተሠልፈናል፡፡
ይህንን ሁሉ ያሳየን ዓመት ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል፡፡ አዲሱ ዓመት ሊቀበለንም እጁን ዘርግቷል፡፡
እኔም መልካም መመኘት መልካም ነውና
መጪውን ዓመት እንኳን በደህና መጣህ
ተሠናባቹን ቻው ቻው አንተ ሠልፋም ዓመት ብዬዋለው፡፡
ቁልፍ ቃላት
Tue, 09/09/2014 - 08:15