ማስታወቂያ

programs top mid size ad

መደነስ ክልክል ነው

ክልክል ነው፡፡ 
ማጨስ ክልክል ነው!
ማፏጨት ክልክል ነው!
መሸናት ክልክል ነው!
ግድግዳው በሙሉ ተሠርቶ በክልክል
የቱ ነው ትክክል?
ትንሽ ግድግዳ እና ትንሽ ሃይል ባደለኝ!
‹‹መከልከል ክልክል ነው›› የሚል ትዕዛዝ አለኝ፡፡
በእውቀቱ ስዩም ‹‹ስብስብ ግጥሞች››
ይህን ወግ መፃፍ ሳስብ ትዝ ያለችኝ አጭር ግጥም ነች፡፡ አንድ ሆቴል ግድግዳ ላይ ተፅፎ የተመለከትኩት ነው ‹‹መደነስ ክልክል ነው›› ይላል እንዲህ አይነቱን የክልከላ ፅሁፍ በሌሎች አንድ ሁለት ሆቴሎች ውስጥም በተመሳሳይ ተፅፎ ተመለኬቼዋለው፤ እንዲያውም በአንዱ ሆቴል መጨፈር መደነስና፣መጮህ ክልክል ነው ተብሎ ተፅፎ ነው ያየሁት፡፡ ከዛ ከስሯ ብዙ ቦታ ሳያት የምታስቀኝ አጭር ፅሁፍ ከወረቀቱ በስተቀኝ ግርጌ አለች፡፡ ድርጅቱ!
ይህንን ፅሁፍ እያየው እዛው የተፃፈበት ሆቴል ውስጥ ሆኜ ብዙ ነገር ማሰብ ጀመርኩኝ ለምንድን ነው ህይወታችን በተከለከለ ነገር የተሞላው አሁን ቢከለከል ቢከለከል መደሠት መደነስ ይከለከላል፡፡
በዚህ ጊዜ ሩጫ በበዛበትና ከሚያስደስት የሚያሳስብ በሞላበት ድንገት የሚደንስ ሰው ሲታይ እንኳን፣ አብዷል እንዴ በሚባልበት ጊዜ ጭራሽ መደነስ ክልክል ነው!፡፡
በየቢሮውና በየተቋሙ ሂዱ የተስተናገዳችሁበት መብታቹሁ ነው የተባለችሁት ነገር ነገ ስላለመከልከሉ ምንም መተማመኛ የላችሁም፡፡ በነጋታው አሊያም ሰንበትበት ብላችሁ ስትሄዱ እሱማ ተከልክሏል ትባላላችሁ፡፡
ለምን ብላችሁ ስትጠይቁ ለሚበዙት እንዲህ ነው የሚል አሳማኝ መልስ አታገኙም ኦ! አታድርቁኝ ተከልክሏል አልኩ ተክልክሏል! አሊያም ትዕዛዙ ከላይ ነው የተላለፈው ወይንም ቦርዱ አሊያም ኮሚቴው ነው የወሠነው ትባላላችሁ፡፡
አንዳንዴ ክልከላው ለሚጠቅም ነገር ሲሆን ደስ ይላል፡፡ ግን የሚበዙት የበለጠ ግራ መጋባትና መምታታት ከመፍጠር ያለፈ አይሆኑም፡፡ አንድ ምሳሌ ላንሳ በአዲስ አበባ በአሁኑ ሰዓት ያለው የአገልግሎት ሰጪ ታክሲዎች ቁጥር ከነዋሪው ጋር አለመጣጣም ሁሌም ችግር ሲሆን የሚታይ ነው፡፡ በሚሊየኖች የሚቆጠረው የአዲስ አበባ ህዝብ በቁጥር ሀያ ሁለት ሺህ ሰማንያ ዘጠኝ አይበልጥም የሚባለው የከተማ ታክሲ (እንደውም በስራ ላይ ያለው ከስምንት ሺህ አይበልጥም ይባላል) አልበቃ ብሎት ግፊያ ግርግር በአሁኑ መገለጫው ደግሞ ረጀም ሰልፍ መታየቱ አዲስ አይደለም፡፡ ታዲያ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሰማያዊና ነጭ ከተቀቡት ውጪ የሆኑ የክፍለሀገር ሚኒባስና ሚዲባሶች ሁሉ ስራ ላይ ሲውሉ ይታያል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ችግር እያለ እነዚህ ድጋፍ ሰጪዎችም በአቅማቸው ችግሩን ተንፈስ የማድረግ ስራን እየሠፋ ድንገት ከሁለት እና ሶስት ወር በፊት ይመስለኛል የታክሲ መንጃ ፈቃድ ካልያዛችሁ ከተማ ውስጥ እነዚህን ሚኒባሶች ማሽከርከር አትችሉም ተብሎ ይህንን ሲያደርጉ የተኙትም አንድ አንድ ሺህ ብር ቅጣት ተቆነደዱ፡፡ ማነው የከለከለው ከላይ ነው መስራት አይችሉም፡፡ እናም ነገሩ ሁሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ቆይቶ ከላይ የተባለው ቢሮ እሱ እንዳልከለከለ ተናገረ ብቻ ነገሩ ቆይቶ ቢስተካከልም ለአንድ ሰሞንም ቢሆን ያልተገባ ክልከላ ተጋዡን ለእንግልት ሹፌርና ባለቤቱን ለወጪ ዳርጐ ከረመ፡፡
ሌላም ከመፍቴሄ ይልቅ መምታታትን የሚፈጥር ብዙ ክለከላን እየመዘዙ ማነሳሳት ይቻላል ብቻ እሱን ተወት አድርገን ወደ ሆቴላችን እንመለስ፡፡ የተጠመቀ ቢራና ድራፍት እንዲሁም በመልክ በመልኩ ከባንኮኒው የተደረደረ የሀገር ውስጥና የወጪ አልኮል መጠጥን እየሸጡ ደስታን መንጠቅ ለምን አስፈለገ? ከቤቱ አስተናጋጆች አንዷን ጠርቼ ጠየኩኝ ቤቱ ይረበሻል በዛ ላይ እቃ ይሠበራል ብላኝ ወደ ስራዋ ተመለሠች፡፡ ‹‹ስለመጠጣቱ ሳያሰቡ ስለመደነሱ መጨነቅ›› እውነት የክልከላው መነሻ ይህ ከሆነ ሌላ አማራጭ መፈለግ ደስታን ከመንጠቅ አይሻልም ነበር? ስል አሠብኩኝ፡፡
ለመደነስ መጠጣት የግድ ባይሆንም ተነስቶ መውረግረግ ግን አንድ ሁለት ሲባል ይብሳል እናም ይህ ክልከላ እዚህ ቤት መሆኑ የባስ ከበድ ይላል፡፡ በዛ ላይ ምክንያቱ አሳማኝ አይደለም፡፡ ለዛም ነው በየመሀከሉ ድንገት ነሸጥ ያደረጋቸው ጠጪዎች ተነስተው ወዝወዝ ማለት የሚጀምሩት፡፡ ፈርጣማው የቤቱ ጠባቂ ወዲያው አፈፍ አድርጐ ወደነበሩበት ቢመልሳቸውም፡፡ በተደጋጋሚ ይህንን የሚያደርጉትንም ፈርጣማው የቤቱ ጠባቂ ሂሳባቸውን በግድ እንዲከፍሉ አድርጐ ከቤቱ እያዳፋ ያስወጣቸዋል፡፡
በቤቱ የቀሩት ተስተናጋጆችም አሁን ምን አለበት ቢደንስ ምናምን እያሉ ያጉተመትማሉ፡፡ ሰዓቱ እየገፋ ሲመጣ ግን ምን ታመጣላችሁ በሚል አይነት ሁሉም ደናሽ ሆነ፡፡ አስተናጋጆቹም ክልከል ነው ለማለት ፈርጣማው የቤቱ ጠባቂም እያዳፋ ለማስወጣት በቁጥር ተበለጡ...ቤቱ ዳንስ ብቻ ሆነ፡፡
ይህንን ትርኢት እያየው ድሮም ያለቦታው የገባ ትክክል ያልሆነ በየቢሮው እና ተቋሙ አለፍ ሲልም በሀገር ደረጃ የሚሆን የማያግባባ ክልከላ መጨረሻው ይህው ነው ስል አሰብኩኝ፡፡
ይህቺን ይህንን ሁሉ ያሳየችኝን ሆቴልም ያልተገባ ክልከላ የበዛበት ሀገር ብትሆን ብዬ አሠብኩኝ፡፡ በውስጧ የተደረደሩትና ለጠየቃቸው የሚሸጡት መጠጦች ደግሞ ስለመብትና ነፃነት የሚያወሩ ፅሁፎች፣ ጠጪው ህዝብ፣ እነዛ ለመደነስ የሚሞክረውን ተስተናጋጅ ክልከል ነው እያሉ የሚነግሩት አስተናጋጆች የተሳሳተ መሪ ጉዳይ አስፈፃሚዎች ፤ፈርጣማው የቤቱ ጠባቂ ደግሞ የተሳሳተ ሀላፊ መስለው ታዩኝ፡፡
እናም ሁሉም ነገር እንዲው ነው ስል አሠብኩኝ ያልተገባ ክልከላ እየከለከልን መቆየት ይቻል ይሆናል ግን ሰዓት እየገፋ ጊዜ እየነጐደ ሲሄድ የተከለከለው የታፈነው መፈንዳቱ አይቀርም፡፡
ቁልፍ ቃላት
Tue, 08/19/2014 - 08:45