ማስታወቂያ

programs top mid size ad

እስኪጣራስ ቢሆን ማን ይንገላታል

በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ነው፡፡ ነገሩ የጥንት ተረትም ይመስላል፡፡ በከተማው ያሉ ስጋ በሊታ እንስሳት በሙሉ ተይዘው ይታሠሩ ተባለ፡፡ ይህንን የሰሙ ስጋ በል እንስሳትም ሳንቀደም በሚል ወደሌላ ቦታ ስደት ጀመሩ፡፡ ከነዚህ በፍጥነት ለማምለጥ ከሚሮጡ ስጋ በል እንስሳት መሀል ጥንቸልም እግሬ አወጪኝ እያለች ስትሮጥ ጓደኞቿ ተመለክቷት
እናም ጥንቸል ሆይ አንቺ ስጋ በል አይደለሽ አያስሩሽ ለምን ትሮጫለሽ አሉአት፡፡ ጥንቸልም ‹‹እስኪጣራስ ቢሆን ማን ይንገላታል›› ብላ መለሠች፤ ብሎ ነበር ያጫወተኝ፡፡
በዚህ ዘመን ብዙውን ህይወታችንን ስናየው እስኪጣራስ ቢሆን ማን ይንገላታል የምንል የበዛን መስሎ ይሠማኛል፡፡
ሰው በህግና በሌላም ማስፈራሪያ ርህራሄውን፣ እውነቱን፣ ያየውና የሚያውቀውን ከምንም በላይ ሰብአዊነቱን በዚህ ህግ፣ መመሪያ፣ መተዳደሪያ ባወጣው ማስፈራሪያ ‹‹እስኪጣራስ ቢሆን ማን ይንገላታል›› በሚል እንዲሸሽ አይቶ እንዳላየ እንዲሆን እያደረጉት ነው፡፡
በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ አንድ የደረሠ የመኪና አደጋን አይተን በዛ ወቅት ያስተዋልነውንና ጥያቄ የሚያስንሳ የመሠለንን ሀሳብ አንስተን በወሬ ጊዜያችን ነግረናችሁ ነበር፡፡ ተገጪው ከመሬት ላይ ተንጋሎ ወድቋል፡፡ ሩሁን ስቷል እናም አፋጣኝ ህክምና ያስፈልገዋል፡፡ በዙሪያው የከበቡት ሠዎችም ይህንኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ፡ ግን ደፍሮ ተጐጂውን ወደ ህክምና ለመወሠድ የደፈረ አልነበረም፡፡ እረ ሊሞት ነው ወደ ሀኪም ቤት ይወሠድ ይላሉ ሀላፊነቱን ለመወሠድ ግን የደፈረ የለም፡፡ ዙሪያውን ከበው በሆነው ነገር እያዘኑ ከንፈር በመምጠጥ የሀሻን የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ ከመስጠት ወጪ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ለምን ቢባል ምክንያቱ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ሰው እጄ ላይ አንድ ነገር ቢሆንስ አስሸከርካሪውም እኔ መኪና ውስጥ እንዳለ ህይወቱ ቢያልፍስ መንገላታቴ አይቀር ህጉ ሊረዳ (ልትረዳ) ስትል ሀለፈ አይለኝ፡፡
በሚሉ ህግና መመሪያዎች ባመጡት ስጋትና ፍራቻ ሁሉም ወደ ኋላ ይላል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ያሳዝናል እያለ እርዳታ ለማድረግ ግን እንደ ጥንቸሏ ‹‹እስኪጣራስ ቢሆን ማን ይንገላታል›› እያለ የሚመጣውን በመፍራት ጥሎ ይሄዳል፡፡
ሰው ኑሮ ከብዶት በህይወቱ ውስጥ የተከሠተበትን የበዛ ጥያቄ አእምሮው መመለስና መቋቋም አቅቶት እራሱን አጠፋ ሲባል ይሰማል በእንደዚህ አይነቱ ወቅት እንኳን ይህ ሰው እንዲህ አይነቱን እርምጃ በህይወቱ ላይ ሊወስን ሲሄድ እያዩ፣ በሩን ዘግቶ ውሳኔውን ሲወሰን በተለያየ መንገድ እያስተዋሉ ሊረዱት ሊያድኑት ቢችሉም እንዴት አየህ የትነበርክ የሚሉና ሌሎችም የህግ ጥያቄዎች ይመጡብኛል ለምን እንገላታለው በሚል እንዳላየ ሆኖ የሚያልፉ ብዙ ነው፡፡
በቅርቡም ከ2 እና ሶስት ወራት በፊት የሆነውም ይህው ነው ልጅቷ ከእህቶቿ ጋር በአንድ ቤት ትኖራለች፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባላወቅም ከስፍራው ስደርስ ቤተሠብ ይጫሀል ጐረቤት ጉድ ጉድ እያለ ወዲህ ወዲያ ይራወጣል፡፡ ከዛም የተባለችው ሴት በር ዘግታ እራሷን ሰቀለች ተባለ፡፡ እንግባ ገመዱን ቆርጠን እናድናት አሉ ሌሎቹ አይ ፖሊስ ይምጣ ጣጣው ብዙ ነው በዚህ መሀል ብትሞት እኮ ትጠየቃለህ የሚሉ ማስፈራሪያዎች ጐረፉ ግን በዚህ መሀል ፖሊስ ደርሶ በሩን እስኪከፍት ይህቺን ዓለም ተሠናብታለች፡፡ ሰብአዊነት ሀዘኔታ ከውስጣቸን ሳይጠፋ ውስጣችን እያዘነ እንባችን እየወረደ የምናለቅስለት ነገር እንዳይከሠት ለማድረግ እድሉ ቢኖረንም ግን ማንም አይደፍርም፡፡ ሰብአዊነቱና ሀዘኔታው ህግና መመሪያ በፈጠረበት ስጋት ሰብአዊነቱ ተኖ ይጠፋል፡፡
‹‹እስኪጣራስ ቢሆን ማን ይንገላታል›› በሚል ሁሉም ወደ ኋላ ይላል፡፡
በዚህ መንገድም ስንቱ ከጐናችን ሲያልፍ ለሀገር ብዙ የሠሩና ገና ይሠራሉም የተባሉ ምሁራን ሲጠፋ አይተናል፡፡
ይህ የምንመራበት የምንተዳደርበት ህግና መመሪያ ከሚሠጠን የበዛ ጥቅም ውጪ የሚፈጥርብን እንዲህ አይነቱ ስጋትና ፍራቻ በስራችን እና በሌላም ወደ ኋላ ሲያስብለን ይታያል፡፡ ያየነውን፣ ስህተት መስሎ የተሰማንን ነገር ደፈር ብለን ከመናገራቸን በፊት ጣጣ ያመጣብኝ ይሆን?ያስጠይቀኝ ይሆን? ትክክለኛ መሆኔ እስኪረጋገጥ ያንገላታኝ ይሆን በሚል ስጋት ውስጥ ቀድመን እንገባለን፡፡ አንዳንዴ ህጉን ጠንቅቆ ካለማወቅ እንጂ ጉዳዩ ምንም ላያስጠይቅ የሚችል ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡
እናም አንዱ በአንዱ ላይ በደል ሲፈፅም ሰው በራሱና በሌላው እንዲሁም በሀገሩም ላይ ያልተገባ ነገር ሲያደርግ እያየን ያየነውን ለማጋለጥ፣ ያሳዘነንን ነገር ይፋ ለማውጣት እንፈራለን፡፡
የሚያስፈራን ደግሞ ጉዳዩ ሳይሆን ከዛ በኋላ ህጉ የሚያመጣው ጥያቄና ጣጣ እንዲሁም እንግልት ነው፡፡ እናም እንደ ጥንቸሏ ‹‹እስኪጣራስ ቢሆን ማን ይንገላታል እንላለን፡፡
ቁልፍ ቃላት
Tue, 07/15/2014 - 09:17