ማስታወቂያ

programs top mid size ad

'ጦሲ ኤሬስ!' . . . (ፈጣሪ ያውቃል)

በፊት ሁለት የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች አሁን ወደ 33 ደርሷል፡፡ በየቀበሌው የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከፍቷል፡፡ከመምህራን በተጨማሪ የፕላዝማ አጋዥ የማስተማሪያ ስልት ተፈጥሯል፡፡ የክፍል ተማሪ ጥምርታ በአብዛኛው 1 ለ 52 ሆኗል፡፡የፈረቃ ትምህርት በከፊልም ቢሆን ቀርቷል፡፡ ለትምህርት ረጅም ሰዓት ተሰጥቷል፡፡ በዲፕሎማ ሲያስተምሩ የነበሩ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን አብዛኛዎቹ ድግሪ ያላቸው እንዲሆኑ ተደርጓል …….. እና ሌሎችም ባለፉት 22 አመታት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሰራሁ ብሎ ከሚናገራቸው እና ከተመሰገነባቸው ትምህርት ነክ ስራዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ስለነዚህ መልካም ስራዎች ስናነሳ እነዚህ ትምህርት ቤቶችም ተቆጥረው ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የኔ የጉዞ ማስታወሻ ነው፡፡
ይህ ፎቶ በአንድ ገጠር ከተማ በተገኘሁበት ምሽት ላይ የተነሳ ነው፡፡ እንደምታዩት ብዙ ስልኮች ተሰብስበው ባትሪያቸውን እየሞሉ ነው፡፡
ይህች ገጠር መንደር ወይም ቀበሌ በጋሞ ጎፋ ዞን ውስጥ ትገኛለች፡፡ ዋጅፎ ትባላለች፡፡
ከወላይታ ወደ አርባምንጭ ሲሄዱ መሃል አከባቢ የመኪናዎ 4ት ጎማ ተቦርቡሮ የኮሮኮንች ንጣፍ የመሰለ አስፓልት መንገዷን ረግጦ ያልፋል፡፡
ይህች የገጠር መንደር እንደብዙዎቹ አቻ መንደሮቿ መብራት የላትም፡፡ የመብራት ማማ ግን በገበሬዎቹ በር  ያልፋል፡፡ ኔትወርክ የለም፡፡ ስልክ ግን በየገበሬው እጅ ገብቷል፡፡
ታዲያ ስልክ ቻርጅ የሚደረገው ጀኔሬቴር ለመግዛት አቅማቸው በፈቀደላቸው 3ት ገበሬዎች ቤት ነው፡፡ ለዚህም ለአንድ ግዜ 3ት ብር መክፈል ይገባዎታል፡፡
3ቱ ባለጄኔሬተሮች ስልክ ቻርጅ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ቴሌቭዥን ገዝተው ሰው ለሰው ድራማ እሁድ መዝናኛን የእግር ኳስ ጫወታዎችን እያሳዩ የአከባቢውን ሰው ከውጭው ሕይወት ጋር ያቀራርባሉ፡፡
ምሽት ላይ በሱቆቻቸው በር በቤታቸውም መብራት ይበራል፡፡ በአከባቢው ያሉ ተማሪዎች ምሽት ላይ ከሱቆቹ ደጅ ቁጭ ብለው ያጠናሉ(እኔ በሄድኩበት ወቅት ትምህርት የተጀመረበት ባለመሆኑ ከመስማት ውጭ ለማየት ግን አልቻልኩም)፡፡
ከአከባቢው ሰው እንደሰማሁት እዚህ አከባቢ በቀደመው ግዜ እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት ነበር፡፡ የተመሰረተው በ1960ዎቹ ነው፡፡
ልጆች ወደ 9ኛ ክፍል ሲያልፉ ወደ አርባምንጭ ወይም ወላይታ ሄደው እንዲማሩ ነው የሚደረገው፡፡ ወላጅ የቤት ኪራይ የመክፈል ቀለብ የመቁረጥ ግዴታ ውስጥ ይገባል፡፡ ልጆቹን በቅርብ የመከታል እድሉን ያጣል፡፡
የመንደሯ ትምህርት ቤት አሁን እስከ 10ኛ ክፍል እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ይህ ከወጪ አንፃር ለወላጆች እፎይታ ቢሆንም ልጆቹ ምን ይማራሉ? እንዴት ይማራሉ? ምንስ ይፈተናሉ? ከተቀረው ተማሪ ጋርስ እንዴት ይወዳደራሉ? ብሎ ለጠየቀ መልሱ ግራ የሚያጋባ ነው የሚሆነው፡፡
የአከባቢው ሰዎች እንኳ ልጆቻችሁ በዚህ ውስጥ ተምራው አልፈው የተሻለ ነገር የሚያገኙ ይመስላችኋል ወይ? ብትሏቸው 'ጦሲ ኤሬስ…ጎዳ ኤሬስ' ይሏችኋል፡፡ 'ፈጣሪ ያውቃል… እግዚያብሔር ያውቃል' እንደማለት ነው፡፡ ከትምህርት ስርዓቱ ይልቅ በፈጣሪያቸው ያላቸው ተስፋን ያሳያል፡፡
አሁንም ቢሆን በትምህት ቤቱ መከፈት እፎይ ያላለው ወላጅ ጥሪቱንም አሟጦም ቢሆን ወደ ከተማ እየላከ ነው ልጁን የሚያስተምረው፡፡ ባይሆን አዲስ የተከፈተው ትምህርት ቤት በቀደመው ግዜ በተለያየ ምክንያት ከ8ኛ ክፍል በላይ መግፋት ያለቻሉ በእድሜ የገፉ ሰዎችን እያስተናገደ ነው፡፡
እንዳልኳችሁ ይህ የገጠር ከተማ መብራት የለውም፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ከተማ ወጣ ማለት ከቸሉ ሰዎች ውጭ የአከባቢው ሰው ከዘመናዊው የኤሌትሪክ ብርሃን ጋር የተዋወቀው በነዛ ጥቂት ባለጀነሬተሮች ነው፡፡ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ለከተሜው ተማሪ መማሪያ ተደርጎ የተዘጋጀው ፕላዝማ ለአከባቢው ታዳጊዎች ትርጉም የማይሰጥ የቃላት ድርድር ነው፡፡
ብዙዎቹ የአከባቢው ታዳጊዎች አለም የደረሰበት የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን ከስሙ ባለፈ ስለቅርፁም ሆነ ስለጥቅሙ የሚያውቅት ነገር የለም፡፡
እዚህ ፎቶ ላይ የምታዩት ታዳጊ ዘንድሮ 8ኛ ክፍል ሚንስትሪ ተፈታኝ ነው፡፡ ድንገት ይዜ የነበረው ላፕቶፕ ኮምፒውተርን ነው ለመጀመሪያ ግዜ ለመንካት ዕድል የገጠመው፡፡ በወቅቱ እሱ የነበረው ደስታ ከየት መጡ ያልተባሉ ታዳጊዎች ከበው ለመንካት ለማየት የነበራቸው ጉጉት በቃላት የሚገለፅ አይደለም፡፡( በርግጥ ኮምፒውተር ለከተሜው ተማሪም ቢሆን ዛሬም ድረስ ብርቅ ነው)
እንግዲህ አነዚህ ታዳጊዎች እንዲህ ባለው ጨለማ ውስጥ እየኖሩ ላይብረሪ በሌለው፣ ቤተ ሙከራ ምን እንደሆነ በማይታወቅበት (የመምህራኑ  ብቃትም ገና መጠናት ያለበት ነው ብለው ወላጆች ጥያቄ በሚያቀርቡበት) እንዲህ እና መሰል ችግር ውስጥ ነው የሚማሩት፡፡
በዚህ ውስጥ አልፈው ነው የተሻለ አቅርቦት ማግኘት ይችላሉ ከሚባሉት የአዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች የመንግስት ትምህርት ቤቶች  ተማሪዎች ጋር እነሱ ለሚኖሩባት ገጠር መንደር የአመት በጀት የሚሆን ክፍያ እየተከፈለላቸው ከሚማሩ ቅምጥሎች ጋር ለሃገር አቀፍ ፈተና ተቀምጠው የሚወዳደሩት፡፡
በርግጥ በዚህ አስቸጋሪ መንገድ አልፈው፣ ተመችቷቸው ነው የተማሩት ከሚባሉት ቀድመው መገኘት የቻሉ ብዙ ብዙ አሉ፡፡ ግን በተሰጣቸው ብቁ የሚያደርግ ትምህርት ነው ወይስ በፈጣሪ ፀጋ ነው ለዚህ የደረሱት? መሆን የሚገባውስ እንዴት ነው?
በቂ መፅሐፍ ቢኖር ባይኖርም ፤ ወንበር ጠረጴዛ ጠፍቶ ልጆች በድንጋይ ላይ ተቀምጠው የሚማሩበት ጣሪያ እና ግድግዳ ብቻ ያላቸው ትምህርት ቤቶች በሽ በሽ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ተደጋጋሚ ትችት የሚቀርብበት ኢሕአዴግ ደግሞ ደጋግሞ የነገረን ጥራት ቀስ ብላ ትመጣለች ታገሱ የሚል ነው፡፡ ግን እስከ መች?
ኢሕአዴግ ከገባ የተወለዱ እኮ አግብተው ወለዱ፡፡ ትመጣለች የተባለችው ጥራት ሳትመጣ የነሱ ልጆችም ትምርት ቤት ይሂዱ?
                   በድጋሚ ጥራት ወዴት አለሽ?
የስልክ እና የኔትወርክ ጉዳዮችን ደግሞ በጥቂቱ እንዳስስ…
በዚች ገጠር መንደር ኔትወርክ በችርቻሮ እንጂ በጅምላ የለም፡፡
በዚህ አከባቢ የሚኖር ሰዎች አንዱን ቀን ከእንቅልፍ ሲነቁ በስልካቸው ላይ የኔትወርክ መኖር ምልክት አዩ፡፡ ኔትወርክ የተገኘበት አከባቢ ወይም እርሻ አባወራ ነዳጅ ግቢው የተገኘ ያህል በኩራት ነው የሚያወራው፡፡
ቀን ቀን በነዚህ ኔትወርክ አደባባዮች ወጣቶች እናት እና አባቶች ኔትወርኩን ፈልገው ስልካቸውን ጨብጠው እጃቸውን ወደላይ ሲያወራጩ የተቃውም ሰልፉ በዚህች ገጠር ከተማም የቀጠለ ሊመስሎት ይችላል፡፡
ህይወት ግን ይቀጥላል. . . ጥሩ ቀን እስኪመጣ!
ሰላም ሁኑ
ቁልፍ ቃላት
Wed, 11/20/2013 - 11:57