• Slider One

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የሀገሪቱ ሰንደቅ ከፍ ሲል አብሮ የሚዘመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን ዜማ የደረሱትና ያቀናበሩት የሙዚቃ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ሉሉ ማረፋቸው ተሰምቷል

የሀገሪቱ ሰንደቅ ከፍ ሲል አብሮ የሚዘመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን ዜማ የደረሱትና ያቀናበሩት የሙዚቃ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ሉሉ ማረፋቸው ተሰምቷል፡፡ነሐሴ 10 ቀን 1930 ዓ.ም በድሬዳዋ የተወለዱት አቶ ሰለሞን ሉሉ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን በውጭ ሀገር ትምህርታቸውን አጠናቀው ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤትን በኃላፊነት ካገለገሉ መምህራን አንዱ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡አቶ ሰለሞን በቂ መምህር በሌለበት ወቅት ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት አሁን ወዳለበት ደረጃ እንዲበቃ ካደረጉ ባለሙያዎች አንዱና የትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ምሩቅም ናቸው፡፡

በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥም ለሦስት ያህል ጊዜ በዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ብሔራዊ በሆኑ የሙዚቃ ዝግጅቶችም ላይ በቀዳሚነት ተሣታፊ በመሆን የሰሩና ከኢትዮጵያ ውጭም በሞስኮ ኦኬስትራ የካቲት በሚል የፃፉት የሙዚቃ ሥራቸው የተሰራ ሲሆን በቡልጋሪያ መስከረም የሚል ሥራቸው በኦኬስትራው ታዋቂ የሆነ ሥራቸው ነው፡፡በኢትዮጵያ አዲሱ ህገ-መንግሥት ሲረቀቅና ሲዘጋጅም ለመቀስቀሻነት የዋለው በአቶ ሰለሞን የተሰራ መዝሙር ሲሆን ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረክ ሰንደቋ ከፍ ሲል የሚዘመረው ብሔራዊ መዝሙሯ የዜማ ደራሲና አቀናባሪም ነበሩ፡፡

አቶ ሰለሞን በሙዚቃ ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፎችን በማቅረብ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የበዙ የሙዚቃ ምርምሮችን ያደረጉና በዋናነትም በትራምፔት የሙዚቃ መሣሪያና ለሙዚቃ ተማሪዎች ከሚሰጡ ትምህርቶች ዋነኛ የሚባለው ሶልፌጆ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ተማሪዎች በተግባርና በንድፈ ኃሣብ ደረጃ የተማሩትን የሙዚቃ ትምህርት ወደ መድረክ አምጥተው እንዲያቀርቡ ፕሮግራም ነድፈው በዓመት ሁለት ጊዜ የሙዚቃ ዝግጅት እንዲቀርብ በማድረግ ወጣቶችን በሙያቸው ያበረታቱ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡

ነሐሴ 10 ቀን 1930 ዓ.ም በድሬዳዋ የተወለዱት የሙዚቃ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ሉሉ ባጋጠማቸው ህመም በሀሌሉያ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ትላንት እረፋድ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብራቸው ሥነ-ሥርዓት እስካሁን እንዳልተወሰነ ከባልደረቦቻቸው ሰምተናል፡፡

ምህረት ስዩም
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ለካባ ድንጋይ ማውጫ ተቆፍሮ በተተወና ውሃ ባቆረ ጉድጓድ ውሰጥ አንዲት የ12 ዓመት ታዳጊ ገብታ ህይወቷ አልፏል

ለካባ ድንጋይ ማውጫ ተቆፍሮ በተተወና ውሃ ባቆረ ጉድጓድ ውሰጥ አንዲት የ12 ዓመት ታዳጊ ገብታ ህይወቷ አልፏል…በአዲስ አበባ ጉለሌ ወረዳ 1 ጀርመን ኤምባሲ አካባቢ ዛሬ ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ የ30 አመት ሰው ወንዝ ውስጥ ሞቶ ተገኘ፡፡በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ዛሬ ለሸገር ሲናገሩ በወንዝ ውስጥ የተገኘውን ግለሰብ አስክሬን ለፖሊስ አስረክበናል ብለዋል፡፡

ባሳለፍነው ቅዳሜ ደግሞ አቃቂ ወረዳ 8 መሀሙድ ካባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለካባ ድንጋይ ማውጫ ተቆፍሮ በተተወና ውሃ ባቆረ ጉድጓድ ውሰጥ አንዲት የ12 ዓመት ታዳጊ ገብታ ህይወቷ አልፏል፡፡ቅዳሜ በዘነበ ከባድ ዝናብ የተከሰተ ጐርፍ ደግሞ በአቃቂ ወረዳ 3 ሰፈረ ገነት አካባቢ፣ ቦሌ ወረዳ 3 ጉርድ ሾላ፣ ቦሌ ወረዳ 8 ሰሚት በርካታ ቤቶች የጐርፍ አደጋ አጋጥሟቸዋል ተብሏል፡፡

የወደመው ንብረት ግምት ለጊዜው አልታወቀም ሲሉ አቶ ንጋቱ ነግረውናል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የቴሌ ሞባይል ካርድና የሚፋቅ ሎተሪ ማተም የሚችል ማሽን ለመግዛት በጀት ይዣለሁ ብሏል

ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የቴሌ ሞባይል ካርድና የሚፋቅ ሎተሪ ማተም የሚችል ማሽን ለመግዛት በጀት ይዣለሁ ብሏል፡፡ይህም በደንበኞቼ ለሚስጥራዊ ህትመት ሥራ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ማሽኖችን ግዛ እያሉ ለጠየቁኝ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ነውም ብሏል፡፡

ድርጅቱ አሁን እየተጠቀመባቸው ያሉ ማሽኖች ረጅም አመታት ያገለገሉ በመሆናቸው አሰራሩን ለማዘመን እንቅፋት ሆኖበት ቢከርምም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዘመናዊ ማሽኖችን እየተከልኩ ነው ብሏል፡፡የቼክ ፐርሰናላይዜሽን ለመጀመር የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራም እንዳጠናቀቀ ድርጅቱ በአመታዊ የውይይት ፕሮግራሙ ሲናገር ሰምተናል፡፡

ለወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የሚያገለግሉ ህትመቶች ትልቅ ሥራና ቀጣይነት ያላቸው በመሆናቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ብታስደግፍ የሚል አስተያየት እንደተሰጠው የሚናገረው ድርጅቱ አሁን ላይ ሰርተፍኬትና የመዝገብ ላይ ህትመቶችን ባለኝ ማሽንና የሰው ኃይል ርብርብ በማድረግ እየሰራሁ ለፌዴራልና ለክልሎች እንዲሰጥ አድርጌያለሁ በ2010 ለወሳኝ ኩነቶችም ሆነ ለሌሎች ህትመቶች የሚያገለግሉኝን ተጨማሪ ማሽኖች ለመግዛት በጀት እንዲያዝ አድርጌአለሁ ብሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 22፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • በግብር ከፋይ ነጋዴዎች ላይ በተደረገ የሂሣብ ምርመራ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ቢወሰንም የተሰበሰበው 35 በመቶ ብቻ ነው ተባለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • ለኢትዮጵያ በአመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስገኝላታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የካሉብና ኢላላ የተፈጥሮ ጋዝ ነገር ከምን ደረሰ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ21 ፋብሪካዎች የዳሰሳ ጥናት አድርጌአለሁ፤ ከእነዚህም ውስጥ በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ ሆነው የተገኙ ጥቂቱ ናቸው አለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ፈጣን ሎተሪና የተንቀሣቃሽ ስልክ ካርድ ለማተም አቅጃለሁ አለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ዜማ ደራሲና አቀናባሪ አቶ ሰሎሞን ሉሉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • በአዲስ አበባ ጉለሌ ወረዳ 1 ጀርመን ኤምባሲ አካባቢ ዛሬ ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ የ30 አመት ሰው ወንዝ ውስጥ ሞቶ ተገኘ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ /ECA/ በግሉ የመገናኛ ብዙሃን ችግሮች ዙሪያ ምክክር እየተደረገ ነው ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኢትዮጵያ የአቮካዶ ምርት ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ ጀመረች ተባለ

ኢትዮጵያ የአቮካዶ ምርት ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ ጀመረች ተባለ፡፡ማሻፍ የተባለ የእሥራኤል ድርጅት ምርቱ ላይና ለአለም ገበያ ተስማሚነቱን በተመለከተ ጥናት አድርጓል ተብሏል፡፡የፌዴራል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የአነስተኛ ሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ይገዙ እስካሁን 11 ነጥብ 5 ቶን ምርት ወደ ኔዘርላድ መላካቸውን ለሸገር ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም ተስፋ ሰጪ ምላሽ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ቅድሚያ የአገር ውስጥ ፋላጎት ማሟላትን በተመለከተም አርሶ አደሩ እራሱ አምርቶ ለራሱ ፍጆታ ተጠቃሚ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡በቀጣይም በምርጥ ዘሮችና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም በማድረግ ወደ ውጪ የመላኩን ሥራ አጠናክሮ ለመቀጠል መታሰቡን አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡

በዚሁ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ቲማቲምና ቃሪያ በቀዳሚነት በስፋት እየተመረቱ እንደሆነም ሰምተናል፡፡

ቴዎድሮስ ብርሃኑ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአዲስ አበባ ታክሲ ሹፌሮች ስለ ትራፊክ አደጋ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አሰጣጥ እውቀት የላቸውም ተባለ

ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአዲስ አበባ ታክሲ ሹፌሮች ስለ ትራፊክ አደጋ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አሰጣጥ እውቀት የላቸውም ተባለ፡፡በከተማዋ በ400 ታክሲ ሾፌሮች ላይ በተደረገው ጥናት ውጤት ላይ እንደተገለፀው 345ቱ ወይንም 86 ነጥብ 3 በመቶዎቹ ስለ ትራፊክ አደጋ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ አሰጣጥ እውቀቱ የላቸውም ይላል፡፡

ወሬው የተሰማው ትናንት በጀመረውና ዛሬ ፍፃሜውን በሚያገኘው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመንገድ ደህንነት ኮንፈረንስ ላይ ጥናት ሲቀርብ ነው፡፡ጥናቱ እንዳመለከተው ምንም እንኳን አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ የታክሲ ሹፌሮች ስለ ትራፊክ አደጋ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ አሰጣጥ እውቀቱ ባይኖራቸውም ድጋፍ ለማድረግ ያላቸው ፍላጎትና አመለካከት ግን ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡

በጥናቱ ከተካተቱት 400 የታክሲ ሹፌሮች ውስጥ ከግማሽ በላዩ ሁለቴና ከዚያ በላይ የትራፊክ አደጋዎችን በሥራቸው ወቅት ተመልክተዋል ብለዋል፡፡በአዲስ አበባ ከሚደርሱና ሞትን ከሚያስከትሉ የትራፊክ አደጋዎች ቀዳሚው የሚደርሰው በታክሲዎች በመሆኑ ለታክሲ ሹፌሮች ስለ መጀመሪያ ሕክምና እርዳታ አሰጣጥ ሥልጠና መስጠት የሟቾችን ቁጥር በመቀነስ በኩል አስተዋፅኦ ከፍተኛ ይሆናል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ታክሲ ሹፌሮች መንጃ ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ሥልጠናውን ቢያገኙ መልካም ነው ተብሎም ምክረ ኃሣብ ቀርቧል፡፡በአዲስ አበባ በቀን ቢያንስ አንድ ሰው በትራፊክ አደጋ ህይወቱን ያጣል፡፡

ንጋቱ ሙሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 19፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የወደፊት ታሳቢ የምርት አቅርቦትና ዝውውር ማከናወኛ መላ ሥራ ላይ ላውል ነው አለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ደንብን ለማስከበር የሚወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ምንም አይነት የህግ ማዕቀፍ የላቸውም አለ፡፡ (ቴዎድሮስ ብርሃኑ)
 • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሠራተኞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ደንብ እያዘጋጀ ነው፡፡ (በየነ ወልዴ)
 • የኢትዮጵያ የእንስሣት እርባታ ባለሙያዎች ማህበር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ላይ የበኩሌን ለመወጣት እድል ሊሰጠኝ ይገባል አለ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • ለጤና ጐጂ ንጥረ ነገር ይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ አምስት የምግብ አይነቶች ናሙናቸው ከገበያ ተወስዶ ጥናት እየተደረገባቸው ነው፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • ሰቆጣ ማይኒንግ የተባለውና በማዕድን ዘርፍ የተሰማራው ኩባንያ በኢትዮጵያ የብረት ማዕድን ለመሰማራት ግማሽ ቢሊየን ዶላር ማዘጋጀቱ ተሠማ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግድ መዳከም አንዱ ምክንያት አለም አቀፍ መስፈርትን አሟልተው አለመገኘታቸው ነው ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ከአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች ስለ ትራፊክ አደጋ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ እውቀቱ ያላቸው ከ13 በመቶ አይበልጡም ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካሣ ከፈልኩ አለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • ኢትዮጵያ የአቮካዶ ምርት ለአውሮፓ ገበያ ማቅረብ ጀመረች ተባለ፡፡ (ቴዎድሮስ ብርሃኑ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ ዘንድሮ ለአምስት ሚሊየን አንድ መቶ አሥራ ሦስት ሺ ሦስት መቶ ስልሣ ሰባት...

የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ ዘንድሮ ለአምስት ሚሊየን አንድ መቶ አሥራ ሦስት ሺ ሦስት መቶ ስልሣ ሰባት ተጠቃሚዎች አገልግሎት ሰጥቻለሁ አለ፡፡ ኤጀንሲው ለጥናትና ምርምር ሰዎች፣ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ለሌሎችም ጠቃሚዎች የንባብ አገልግሎት የሚሰጥበት ክፍል ጥበት ገጥሞት ብዛት ያላቸው ተገልጋዮች ማስተናገድ አለመቻሉንም ተናግሯል፡፡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ እንዳለው አዳሙ ለሸገር ሲናገሩ ያለብንን የቦታ ጥበት ያስቀራል የተባለውና መንግሥት በሦስት መቶ ሚሊየን ብር የሚያስገነባው ባለ 13 ፎቅ ህንፃ በመጠናቀቅ ላይ ነው ፤ ህንፃው ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት ከ11 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ ይችላል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው ከንባብ አገልግሎቱ ባለፈ ዘንድሮ ከተለያዩ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም መስጊዶች ከአንድ መቶ አሦስራ ሦስት ሺ በላይ ጥንታዊና ታሪካዊ የሥነ-ፅሁፍ ሐብቶችን በዲጂታል ካሜራና በማይክሮ ፊልም ሰብስቧልም ተብሏል፡፡ በኤጀንሲው በሚሰጠው የብሬል ንባብ አገልግሎትም ዘንድሮ 486 አይነስውራን ተጠቅመዋል ያሉት አቶ አዳሙ የአይነስውራን አንባቢያን ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው ለዚህም አይነስውራኑ የቦታውን ርቀት በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡ ወደፊት እነሱ በሚበዙበት ሥፍራ የብሬል ንባብ አገልግሎት ለመጀመርም ኃሣብ አለ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ወንድሙ ኃይሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ከዚህ ቀደም ወደ ሀገር ገብተው የማያውቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥራት ለመፈተሽ መቸገሩን የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት ተናገረ

ከዚህ ቀደም ወደ ሀገር ገብተው የማያውቁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥራት ለመፈተሽ መቸገሩን የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት ተናገረ፡፡በዚህ ዓመትም ከቀረቡለት 26 ሺ የጥራት ፍተሻ ጥያቄዎች 39ኙን የማላውቃቸው ቴክኖሎጂዎች ስለሆኑ አልችልም ብዬ መልሼያለሁ ብሏል፡፡ለመጡት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈተሻ መሣሪያ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የተዘጋጀ ደረጃም እንደሌለው ተናግሯል፡፡ኢትዮጵያ ወደ ሀገር በምታስገባቸውና ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች የጥራት ችግር ላይ መላ ለመፈለግ የጥራት ፈታሽ ድርጅቱ ከአምራች አስመጪና ላኪዎች ጋር ዛሬ እየመከረ ነው፡፡

አስመጪዎች ወደ ሀገር የሚያስገቧቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ጥራት ለመፈተሽ ይችል ዘንድ ለሚያስመጧቸው እቃዎች ቀድመው እንዲያሳውቁትም ጠይቋል፡፡የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በልሁ እንዳሉት የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች እየሰፉ ነው ከዓለም ወደ ሀገር የሚገቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም እየጨመሩ ነው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የጥራት ፈታሹ መሥሪያ ቤት አቅም አብሮ ካላደገ ፈተናው እየከበደ ይሄዳል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው የግብርና ምርቶችና እንደ ቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ያሉ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ነው፤ ለዚህ አንዱ ምክንያት የአለም የዋጋ መዋዠቅ ነው ቢባልም የሚላኩ ምርቶች ከሌሎች ጋር በጥራት ተወዳዳሪ አለመሆናቸውና እሴት ተጨምሮባቸው አለመላካቸው ለገቢው መቀነስ ሌላው ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዳሉትም ከዚህ ቀደም ወደ ኖርዌና ጀርመን የተላከ ማር ስኳር ተቀላቅሎበት በመገኘቱ መመለሱን፣ የበርበሬና የገብስ ቆሎም አፍላ ቶክሲን አለባቸው ተብለው ከአለም ገበያ ተሰብስበው መመለሳቸውን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ በማር ውስጥ ስኳር ስለመቀላቀልና አለመቀላቀሉ የመፈተሻ ቴክኖሎጂ አስመጥቶ ሥራ ጀምሯል ብለዋል፡፡በሌሎች ምርቶች ላይ ግን ተጨማሪ ፍተሻዎችን ካላደረግን ከዓለም ጋር ተወዳዳሪ መሆን አንችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሰቆጣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የብረት ማዕድን እንዲያመርት ፍቃድ ተሰጠው

ሰቆጣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የብረት ማዕድን እንዲያመርት ፍቃድ ተሰጠው፡፡ኩባንያው ለአሥር አመታት ስምንት መቶ አርባ ሺ ቶን የብረት ማዕድን ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ዛሬ በማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በተደረገ ስምምነት እንደተባለው ለኩባንያው ፈቃድ የተሰጠው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋግ-ህምራ ዞን በሰቆጣና ዝቋላ ወረዳ ወይም በልዩ ስማቸው ደብረብርሃን ረታ ገነትና ደብረ ህይወት በተባሉ ቦታዎች ነው፡፡

አጠቃላይ ሥፋታቸውም 16 ካሬ ኪሎ ሜትር መሆኑ ተነግሯል፡፡ኩባንያው ለኢንቨስትመንትም 422 ሚሊየን ብር ወጪ እንደሚያደርግም ተሰምቷል፡፡ስምምነቱ ለ20 ዓመታት የሚፀና ሆኖ የፈቃድ ዘመኑ ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረት በእያንዳንዱ የፈቃድ እድሣት ጊዜ ለ10 ዓመት ያልበለጠ ጊዜ ሊታደስ ይችላል ተብሏል፡፡ዛሬ ስምምነቱን ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳና የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሉቺያኖ ፍራቶሊን ፈርመውታል፡፡

ዮሐንስ የኋላወርቅ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ነሐሴ 18፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ከአውሮፓ ህብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ፕሮጀክት ነድፎ በሴቶች ላይ የሚደርስን ጥቃት ለማስቆም እየሰራ ነው ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት እግረ መንገድ የምሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት እየተወደደልኝ በመሆኑ አዳዲስና ዘመናዊ አውቶብሶችን ገዝቼ አሰማርቻለሁ አለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • በድምሩ ከ904 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ እቃዎች በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡና ሊገቡ ሲሉ ተይዘዋል ተባለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • የውጭ ሀገር ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዲስትሪ እየተቀላቀሉ ነው ተባለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋሉ 27 ግለሰቦች ላይ ከ8 እስከ 12 ቀናት የሚደርስ ተጨማሪ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት ለአገሪቱ እንግዳ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን የጥራት ደረጃ መፈተሹ ችግር ሆኖብኛል አለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • በአዲስ አበባ የፍጥነት ወሰን መቆጣጠሪያ ራዳር ሥራ ላይ ሊውል ነው፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ያለፈው የበጀት ዓመት እጅግ የተሳካ ተግባር ያከናወንኩበት ነበር አለ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ ዘንድሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጐች አገልግሎት መስጠቱ ተናገረ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • ሰቆጣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የብረት ማዕድን እንዲያመርት ፍቃድ ተሰጠው፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር የክፍያ አገልግሎት ስምምነት ተፈራረመ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Leza Vote Banner
Sheger 102.1 AudioNow Numbers