• Slider One

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የፍሬገነት ህልም … ፍሬገነት ኪዳን ለሕፃናት ትምህርት ቤት….

የወጣት ፍሬገነት የዘወትር ህልም በችግር ምክንያት የትምህርት ቤትን ደጃፍ መርገጥ ያልቻሉ ሕፃናትን የሚያስተምር ትምህርት ቤት መክፈት ነበር፡፡ የዛሬ 15 ዓመት፣ በ1995 ዓ.ም አንዲት ዕለት ግን ይህን ሕልም ሊያጨናግፍ ያለ ክስተት ሆነ - በወቅቱ በሚኒያፖሊስ ከተማ ነዋሪ የነበረችው ፍሬገነት የምታሽከረክረው መኪና ከፖሊስ ከሚሸሽ እፅ አዘዋዋሪ መኪና ጋር ተጋጭቶ ፍሬገነት ለሕልፈተ በቃች…

ፍሬገነት በአደጋው ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አጠናቃ ገና ሁለት ወሯ ነበር፡፡ ብቸኛ ልጃቸውን በሞት የተነጠቁት ወላጆች ግን የፍሬገነትን ሕልም እውን ለማድረግ ተነሱ፡፡

ለዚህም የዛሬ 13 ዓመት የፍሬገነት ወላጆች 30 የችግረኛ ቤተሰብ ልጆችን የሚያስተምረውን “ፍሬገነት ኪዳን ለሕፃናት ትምህርት ቤት”ን አቋቋሙ…አሁን ላይ ትምህርት ቤቱ 335 ልጆችን የትምህርት ቁሳቁስ እየሰጠ፣ ዩኒፎርም እያለበሰ እና እየመገ ያስተምራል! ትምህርት ቤቱ ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ 4ኛ ክፍል የሚያስተምር ሲሆን፤ ከዚያን በኋላ ያሉትን ክፍሎች ምግብ ማብላቱም ሆነ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፉ ሳይለይ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ያደርጋል…

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው የህዳሴ ግድብ በታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገሮች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ካለ የሚያጠናው ድርጅት ባቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በአዲስ አበባ መነጋገራቸው ተሰማ

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው የህዳሴ ግድብ በታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገሮች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ካለ የሚያጠናው ድርጅት ባቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በአዲስ አበባ መነጋገራቸው ተሰማ፡፡ሦስቱ ሀገራት አጥኚ ቡድኑ ያቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላይ ከግንቦት 3 እስከ 6 በአዲስ አበባ መነጋገራቸውን በውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ አጥናፌ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

ንግግሩ በሚያዝያ ወር በግብፅ ካይሮ ለ4 ቀናት ተካሂዶ የነበረው ውይይት የተከተለ መሆኑን ሰምተናል፡፡ሦስቱ ሀገራት አጥኚ ቡድኑ ባቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላይ በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ያደረጉት ውይይት ቴክኒካል ወይም ሙያዊ ጉዳዮች የተነሱበት መሆኑን አቶ ተሾመ ተናግረዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገሮች ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ካለ የሚያጠናው አጥኚ ቡድን ያቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ላይ የሚካሄደው ንግግር ወደፊትም እንደሚቀጥል ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡ከአባይ ተፋሰስ ሀገሮች አንዷ የሆነችው ግብፅ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በወንዙ ላይ ያለኝን ጥቅም ይነካብኛል የሚል ኃሣብ ያላት ሲሆን ኢትዮጵያ በበኩሏ የግድቡ መገንባት የግብፅንም ሆነ የታችኛውን የወንዙ ተፋሰስ ሀገሮች ጥቅም የሚነካ አይደለም ስትል በተደጋጋሚ መናገሯ ይታወሣል፡፡

ንጋቱ ሙሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የአማራ ክልል እስከ 8ኛ ክፍል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሰጡ የነበሩ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ወደ አማርኛ ቋንቋ ሊመልሳቸው ጥናት እያደረገ መሆኑ ተሰማ

የአማራ ክልል እስከ 8ኛ ክፍል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሲሰጡ የነበሩ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ወደ አማርኛ ቋንቋ ሊመልሳቸው ጥናት እያደረገ መሆኑ ተሰማ፡፡የሳይንስ ትምህርቶቹ ከ10 ዓመታት በፊት ነበር በእንግሊዘኛ ቋንቋ እንዲሰጡ የተደረገው፡፡ሆኖም ተማሪዎች በአግባቡ ተረድተውት ስኬታማ የመሆናቸው ነገር አጠራጣሪ ነው የሚሉት የክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዋ ዶክተር ሂሩት ካሳው ቢሯቸው ስለ ጉዳዩ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር እየሰራበት ነው ብለዋል፡፤

ወደ እንግሊዘኛ ሲቀየር መጀመሪያውኑ በጥናት የተደገፈ አልነበረም የሚሉት ኃላፊዋ አሁን ወደ አማርኛ ለመመለስ ጥናት ውስጥ ያስገባቸውን ምክንያት ነግረውናል፡፡የክልሉ ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ሲገቡ ቀጥታ እንግሊዘኛ ቋንቋ ጋር መገናኘታቸው ተፅእኖ አያሳድርባቸውም ወይ ተፎካካሪ የመሆን አቅማቸውንስ አይፈታተንም ወይ ምን ያክል ታስቦበታል ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ የሌሎች ክልሎችን ልምድ ጠቅሰው ስኬታማ እንደሚሆን ነግረውናል፡፡

የአማርኛ ቋንቋ የምርምር የማስተማርያና መማሪያ ቋንቋ የመሆን ሙሉ አቅም እንዳለው የሚናገሩት ዶክተር ሂሩት አንዳንድ ቋንቋው ውስጥ የሌሉ የሳይንስ ቃላትን ተመራምሮ ከአማርኛ ጋር የማስማማቱንና የማዋደዱን ስራ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የቋንቋ ማበልፀጊያ ተቋም ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ምርምር አካዳሚ የሳይንስ መዝገበ ቃላትና የሙያ ቃላት እንዳለ ያስታወሱት ዶክተር ሂሩት በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ ፅንሰ ሃሳቦችን ማካተት ባለመቻሉ ለአሁኑ የትምህርት ደረጃ እንዲበቃ የቴክኖሎጂና የምርመራ ቋንቋ እንደሆነ ይሰራል ብለዋል፡፡

ከመጀመሪያ ደረጃም በላይ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር በሰፊው እንዲያገለግል እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡ከዚህ በተጨማሪ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ለግዕዝ ቋንቋ በቀጣይ ዓመት የትምህርት ክፍል ሊከፍትለት እንዳሰበ ያገኘናቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ምስክር አወል
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ግንቦት 7፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • ቀይ መስቀል ከእግር ጉዞ ፕሮግራም 1 ሚሊዮን ብር አገኘሁ አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የድንገተኛ አደጋዎችና ህመሞችን ለመከላከል እና የሚደርሰውን የጉዳት መጠን ለመቀነስ እንዲያስችል ባለሙያዎችን የሚያሰለጥን ተቋም ተከፈተ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የአማራ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመመለስ ሊያስተምር እያስጠና መሆኑ ተሰማ፡፡ (ምስክር አወል)
 • በምዕራብ አዲስ አበባ የውሃ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል ተባለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማችሁ ውስጥ የሚገኝ የኤድስ ህሙማን ነፃ የተጓዳኝ ህመም ህክምና የምታገኙበትን ቦታ ልጠቁማችሁ ይላችኋል፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • በታላቁ ህዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች የሚደርሰው ጉዳት መኖር አለመኖሩን ያጠናው ኩባንያ የመጀመሪያውን ሪፖርት አዲስ አበባ ላይ አቀረበ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የሚቀጥራቸው የሂሣብ ግዢና ንብረት ባለሙያዎች እረግተው እንደማይቀመጡለት ተናገረ፡፡ (ህይወት ፍሬስብሃት)
 • የአፍሪካ ሀገራት በ2030ና በ2063 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የልማት ዕቅድ አጀንዳዎቻቸው ላይ የሚነጋገሩበት አህጉራዊ ጉባዔ ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ይከፈታል ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • ቅዳሜና ዕሁድ ባጋጠሙ የመኪና አደጋዎች በሰው አካል ላይ ጉዳት አደረሰ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)      
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሳውዲ አረቢያ ሀገሯን ጥለው እንዲወጡ የሰጠችውን ቀነ ገደብና ውሣኔውን በተመለከተ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ተቋሞች እንደሚጠበቀው እያሳወቁ አይደለም ተባለ

ሳውዲ አረቢያ ሀገሯን ጥለው እንዲወጡ የሰጠችውን ቀነ ገደብና ውሣኔውን በተመለከተ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ተቋሞች እንደሚጠበቀው እያሳወቁ አይደለም ተባለ፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን የኤሌክትሮኒክስም ሆነ የህትመቱ ተገቢውን ቦታ ሰጥቶ ህዝቡ እንዲያውቀው እያደረገ አይደለም ብለዋል፡፡

በሳውዲ አረቢያ ከ250 ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያዊያን ዘንድሮ ወደ ሀገራቸው ይመጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ከ20 ሺ የማይበልጡ ዜጎች የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡በአሁን ጊዜ በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገር ቤት ለማስመለስ ከአይ.ኦ.ኤምና ከሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ መለስ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው በተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዲመለሱ ተገቢውን ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በጊዜ ገደቡ ውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያዊያኑ መመለስ ካልቻሉ ከዚያ በኋላ የሚደርስባቸው ነገር በጣም አስከፊ ስለሚሆን ያንን በተመለከተም ለዜጐች ማስተማር የመገናኛ ብዙሃን ድርሻ ነው ብለዋል፡፡በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ከ500 ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያዊያን በህገ-ወጥ መንገድ ይኖራሉ ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ሳውዲ በሰጠችው የምህረት ጊዜ ተጠቅመው የሚመጡ ሰዎች ከ250 ሺ ቢልቁ እንጂ አያንሱም ብሎ ገምቷል፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ዛሬ በሰጠው መግለጫው ላይ በተለያዩ ሀገራት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችንና ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት ያላትን ቦታና የአራት ወራት ሪፖርትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኔነህ ሲሳይ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ካለበት ፅኑ ችግር በፍጥነት እንዲወጣና የተሻሻለ ተቋም ሆኖ እንዲቀርብ የህዝብ እንደራሴዎች ኃሣባቸውን አቀረቡ

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ካለበት ፅኑ ችግር በፍጥነት እንዲወጣና የተሻሻለ ተቋም ሆኖ እንዲቀርብ የህዝብ እንደራሴዎች ኃሣባቸውን አቀረቡ፡፡የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ ላይ ኮርፖሬሽኑን በተመለከተ ባለፈው ሣምንት ማብቂያ ላይ የተሰጡትን የእንደራሴዎች ኃሣብ ጨምቆና መርምሮ የውሣኔ ኃሣቡን እንዲያቀርብ ለባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኃላፊነቱን ሰጥቶ ነበር፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አሁን ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ የተመለከተ አጭር ማብራሪያ ካቀረበ በኋላ ኮርፖሬሽኑ በአስቸኳይ እንዲያስተካክላቸው ያላቸውን ነጥቦች ዘርዝሮ የውሣኔ ኃሣቡን አሳልፏል፡፡በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በምሰራቸው ሥራዎች ምክንያት የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችና ከተቋሙ ውጪ ባሉ ሰዎች ይደርስብኛል የሚለውን ጣልቃገብነትና ጫና ተቋቁሞ ራሱ ያወጣውን ኤዲቶሪያል ፖሊሲና መርህ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት የውሣኔ ኃሣብ ተሰጥቶታል፡፡

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት ቁጥጥር ያለ ተቋም እንደመሆኑ የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ እንዲችል ህገ-መንግሥቱንም እንዲያከብር ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል፡፡ኮርፖሬሽኑ ሲገመገምና ሲፈተሽ የመንግሥትንም ሆነ የህዝብን ፍላጐት ማርካት እንደተሣነው ቋሚ ኮሚቴው ያገኛቸው አስተያየቶች እንደጠቆሙት አስታውሶ ይህን አስቸጋሪ ልማዱን እንዲያስወግድ የውሣኔ ኃሣቡን ለኮርፖሬሽኑ አቅርቧል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ግንቦት 3፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የሳውዲ አረቢያ መንግሥት ከአገሬ ውጡልኝ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቅጣት ሳያገኛቸው ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ መገናኛ ብዙሃን ለጉዳዩ በቂ ሽፋን እንዲሰጡት ተጠየቁ፡፡ (የኔነህሲሣይ)
 • የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በምሰራቸው ሥራዎች ምክንያት ከመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንትና ከተቋሙ ውጭ ባሉ ሰዎች ይደርስብኛል የሚለው ጫና እንዲቋቋምና የኤዲቶሪያል ፖሊሲውን እንደ መርህ ማድረግ አለበት የሚል የሕዝብ እንደራሴዎች ውሣኔ ኃሣብ አቀረቡ፡፡ (ሕይወትፍሬስብሃት)
 • 10ኛው አዲስ ቻምበር አለም አቀፍ ልዩ የግብርና እና የምግብ ንግድ ትርኢት ዛሬ ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይከፈታል ተባለ፡፡ (ንጋቱሙሉ)
 • የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የግብርና ኬሚካል የማምረት ውጥን ይዘዋል ተባለ፡፡ (ንጋቱሙሉ)
 • አፍሪካ ከአውሮፓ አህጉር እኩል የሃይድሮ ፓወር የኤሌክትሪክ ብርሃንን የማመንጨት ተፈጥሯዊ የውሃ ሃብት ቢኖራትም ለማምረት የቻለችው እጅግ ጥቂት ነው ተባለ፡፡ (የኔነህሲሣይ)
 • የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች የጥጥ አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል ተባለ፡፡ (ወንድሙኃይሉ)
 • በዘመናዊ መጓጓዣ ሎጅስትክ ቅልጥፍና ላይ የሚያተኩር ቋሚ ኤግዚቢሽን ለተመልካቾች ዕይታ ሊበቃ ነው፡፡ (ምህረትስዩም)
 • 706 ደረጃዎች በብሄራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት መፅደቃቸው ተሰምቷል፡፡ አዲስ የወጣው መመሪያ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር አንድም ምርት ያለምልክት ወደ ገበያ አይወጣም ተብሏል፡፡ (ምሥክርአወል)

 

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 9 ወራት 49 አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈቱንና ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞቹ ቁጥር 15 ሚሊዮን ደርሰውልኛል አለ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 9 ወራት 49 አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈቱንና ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞቹ ቁጥር 15 ሚሊዮን ደርሰውልኛል አለ፡፡ንግድ ባንክ የ2009 ዓ.ም የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ በላከልን አጭር መግለጫ ባለፉት 9 ወራት የውጭ ምንዛሬ እንቅስቃሴው 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቱን ይናገራል፡፡

በግማሽ ዓመቱ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 438 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱንና የ9 ወሩ የትርፍ መጠን ከታክስ በፊት 11 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖልኛል ብሏል፡፡ተቀማጭ ገንዘቡም ወደ 347 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ማደጉን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

1 ሺ 186 ቅርንጫፎች አሉኝ የሚለው የንግድ ባንኩ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ደንበኞች ቁጥር 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ደግሞ ከ20 ሺ በላይ ከፍ ማለታቸውን ተናግሯል፡፡የኤቲኤም ማሽኖች ቁጥር 1 ሺ 335፣ የፖስ ማሽኖች ቁጥር 6 ሺ 696 ማድረስ መቻሉን ንግድ ባንኩ ከላከልን መግለጫ ተመልክተናል፡፡

ምስክር አወል

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ግብርና ግብዓቶችን በቅርብ እንዲያገኙ መጪውን ትውልድ መመገብ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ተጨማሪ የማከፋፈያ ማዕከል መክፈቱ ተሰማ

አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ግብርና ግብዓቶችን በቅርብ እንዲያገኙ መጪውን ትውልድ መመገብ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ተጨማሪ የማከፋፈያ ማዕከል መክፈቱ ተሰማ…አዲስ አበባ ከሚገኘው ከአሜሪካ ኤምባሲ ሸገር ዛሬ እንደሰማው በአሜሪካ አለም አቀፍ ትብብረ USAID በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፌርሜሽን ኤጀንሲና በሌሎች መሥሪያ ቤቶች ትብብር የእርሻ ግብዓቶች ማከፋፈያ ማዕከሉ የተከፈተው በካኮ መሆኑን ነው፡፡

ምርጥ ዘር ኬሚካሎችና ማዳበሪያ መሰል ለእርሻ ሥራ የሆኑ ግብዓቶችን የአነስተኛ ማሳ ገበሬዎች በቀላሉ ማግኘት ስለማይችሉ በአካባቢያቸው የማከፋፈያ ማዕከላቱ መከፈታቸው የምግብ ዋስትናን ለመጠበቅ ድርሻ አለው ተብሏል፡፡መጪውን ትውልድ መመገብ ኢትዮጵያ የእርሻ አገልግሎት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ በግብርና በሚታወቁ ክልሎች በአማራ 6፣ በኦሮሚያ 5፣ በደቡብ 4 እና በትግራይ 3 አካባቢዎች ተወዳድረው ለተመረጡ እስከ 50 ሺ የአሜሪካን ዶላር ካፒታል ከሚያስፈልጋቸውና የተወሰነውን ከሚሸፍኑ ሥራ ፈጣሪ ሰዎች ጋር በመተባበር ማዕከላትን መክፈቱን ሰምተናል፡፡

መጪውን ትውልድ መመገብ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የተመደበለት የአለም አቀፍ የርሃብና የምግብ ዋስትና መርሃ-ግብር ሲሆን የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መሠረት ለሆነው ግብርና የሚያደርገውን ድጋፍ ዘላቂ ለማድረግ ፕሮጀክቱ የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡በባኮ የተከፈተውን የግብርና ግብዓቶች ማከፋፈያ ማዕከልን በባለቤትነት የምታስተዳድረው በሥራ ፈጣሪነቷ ከአካባቢው የተመረጠች ሴት አርሶ አደር ነች ተብሏል፡፡

የኔነህ ሲሣይ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ግንቦት 4፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • መጪውን ትውልድ መመገብ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አዲስ የግብርና ምርት ማከፋፈያ ከፈተ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግማሽ አመቱ ጠቅላላ ሀብቱ 438 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናገረ፡፡ (ምሥክር አወል)
 • የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ያወጣኋቸውን ደረጃዎች ማወቅ ለምትፈልጉ ድረ ገፄ ላይ አስፍሬያቸዋለሁ ተመልከቱት ብሏል፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • የግብረ ሰዶም ጥቃት የፈፀመው ተከሣሽ በእሥራት ተቀጣ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 9 ወራት 49 አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈቱንና ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞቹ ቁጥር 15 ሚሊዮን ደርሰውልኛል አለ፡፡ (ምስክር አወል)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ለዛ የምሳ ሰዓት ፕሮግራም ግንቦት 1፣2009

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (1 Comment)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers