• Slider One

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

በቀጣዮቹ ቀናት በሀገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች ከባድ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ አድርጉ ሲል የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ተናገረ

በቀጣዮቹ ቀናት በሀገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች ከባድ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ አድርጉ ሲል የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ተናገረ፡፡ዝናብ ሰጪ ገፅታዎች እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ ኤጀንሲው ተናግሯል፡፡

ከባድ ዝናብ ያስተናግዳሉ ከተባሉት የአገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ አዲስ አበባን  ጨምሮ ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ምዕሪብና ሰሜን ሸዋ፣አርሲና ባሌ በኦሮሚያ አካባቢዎች የተካተቱ ሲሆን ለ7 ቀናት ያህል ከባድ የዝናብ መጠን ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኤጀንሲው አሳስቧል፡፡

የመኸር ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖራቸው ይችላል ተብሏል፡፡የሚጥለው ከባድ ዝናብ ሰብሎች እንዳያበላሽ አርሶ አደሩ ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባውም ኤጀንሲው ተናግሯል፡፡

ምህረት ስዩም
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሐምሌ 7፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

 • በመጪዎቹ ሰባት ቀናት ውስጥ አዲስ አበባን ጨመሮ የኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ከባድ ዝናብ ያገኛቸዋል ተባለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ከሳውዲ አረቢያ ለመመለስ ከተመዘገቡት ውስጥ ግማሽ ያህሉ እንኳ ወደ ኢትዮጵያ አልመጡም ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • በአዲስ አበባ ሴተኛ አዳሪዎች በብዛት እየተገኙ ያሉት ከዚህ ቀደም የከተማ ዳር እየተባሉ በሚጠሩት አካባቢዎች ሆኗል ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • የተተመነባቸው የቀን ገቢ ግምት እንዲስተካከልላቸው አቤት ካሉ ነጋዴዎች መካከል 73 በመቶዎቹ ግምቱ እንደፀናባቸው ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱ ተናግሯል፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • በኦሮሚያ ክልል 43 ሺ ነጋዴዎች ያለፈቃድ ሲነግዱ ነበር ተባለ፡፡ (ንጋቱ ረጋሣ)
 • በአዲስ አበባ 31 የግል ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናችሁ ተብለው ፈቃዳቸውን ተነጠቁ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • በተያዘው አመት በአማራ ክልል በደረሰው የመኪና አደጋ ከ900 በላይ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተሰማ፡፡ (ምሥክር አወል)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ባለፉት 25 ዓመታት፣ ለሀገሪቱ የሚዲያ እንቅስቃሴ የላቀ አስተዋፅኦ አድርገዋል ላላቸው አክብሮት ሊሰጥ ነው

የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ባለፉት 25 ዓመታት፣ ለሀገሪቱ የሚዲያ እንቅስቃሴ የላቀ አስተዋፅኦ አድርገዋል ላላቸው አክብሮት ሊሰጥ ነው፡፡ካውንስሉ ባለፉት ዓመታት በርካታ ውጣ ወረድ አልፏል፣ ለሚለው የኢትዮጵያ ሚዲያ፣ የላቀ አስተዋፅኦ አድርገዋል፣ ብሎ አክብሮት የሰጣቸው፣ ለአቶ ክፍሌ ወዳጆና ለአቶ አማረ አረጋዊ ነው፡፡

አቶ ክፍሌ ወዳጆ በኢትዮጵያ የፕሬስ ሕግ ሲረቀቅ ከመሠረታዊ መንፈስ እንዳይዛባ በብርቱ መታገላቸው ተነግሮላቸዋል፡፡ ቀድሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በኋላም በስደት ቆይተው ከተመለሱ በኋላ ኃሣብን የመግለፅ፣ የመናገር፣ የመፃፍ ፣ የመሰብሰብና የመሳሰሉትን የተመለከተ ድንጋጌዎች፣ የሚገባቸውን ሥፍራ እንዲያገኙ በፅኑ ተከራክረዋል ተብሏል፡፡

አቶ አማረ አረጋዊ የሪፖርተር ጋዜጦችንና መፅሔት መስረተው ከ20 ዓመታት በላይ የሚዲያ እድገት እንዲጐላ ብዙ መስራታቸው ተጠቅሶላቸዋል፡፡ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መምሪያ ኃላፊነት የሰሩት አቶ አማረ አረጋዊ፣ የፕሬስ ነፃነትን የሚመለከቱ ደንቦች ሲረቀቁም በተደረገው ውይይት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ታውቆላቸዋል፡፡

ለሚዲያ ባለሙያዎች አክብሮት መስጠት የወደፊቱን መንገድ ለማመቻቸት እንደሚረዳ የሚዲያ ካውንስሉ አምኖበታል፡፡ የአክብሮት መስጠቱ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ አመሻሽ ላይ በሂልተን ሆቴል ይከናወናል፡፡

እሸቴ አሰፋ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢትዮጵያ ደርሳበታለች ለተባለው የእድገት ደረጃ ልክ ተጠቃሚ መሆን አለመሆናቸውን

ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢትዮጵያ ደርሳበታለች ለተባለው የእድገት ደረጃ ልክ ተጠቃሚ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥናት ማካሄዱን የማህበራዊ ጥናት መድረክ የተሰኘው የጥናትና ምርምር ተቋም ለሸገር ተናግሯል፡፡ከአውሮፓ ህብረት ሲቪል ሶሳይቲ ድጋፍ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በተደረገው ጥናት መሠረትም ለተለያየ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ሀገሪቱ በደረሰችበት የምጣኔ-ሐብት እድገት ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ በጥናት መረጋገጡን የተቋሙ ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ዶክተር ምህረት አየነው ነግረውናል፡፡

ተገኘ በተባለው የኢኮኖሚ እድገት ከሌላው እኩል ተጠቃሚ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም ኑሯቸው እንዲሻሻል መንግሥት የትኞቹን ፖሊሲዎቹን ማሻሻል ይገባዋል? ከማንስ ምን ይጠበቃል? ስለሚለው ጉዳዩ ከሚያገባቸውና ከምሁራን ጋር እንደተመከረበትም ሰምተናል፡፡

የጥናቶቹ ውጤትና ከምክክሩ የተገኙ ኃሣቦችም ለመንግሥት ፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ይወጣል ያልኩትን ሎተሪ እስከ ሐምሌ 13 ያራዘምኩት በሎተሪዎች መደራረብና በጊዜ ማነስ ሰበብ ነው አለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ይወጣል ያልኩትን ሎተሪ እስከ ሐምሌ 13 ያራዘምኩት በሎተሪዎች መደራረብና በጊዜ ማነስ ሰበብ ነው አለ፡፡የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ቴዎድሮስ ነዋይ ለሸገር ሲናገሩ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ይወጣል ካልነው ቶምቦላ ጐን ለጐን የህዳሴው ግድብ ቶምቦላ በመምጣቱ የተፈለገውን ያህል ትኬት ስላልተሸጠልን ነው የእጣውን መውጫ ወደ ሐምሌ 13 2009 ያራዘምነው ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ያልተሸጡ ትኬቶችን ቀላቅሎ ያወጣቸዋል የሚባልም ሐሜት አለ ይህ እንዳይመጣ ነው በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የእጣ አወጣጡን የምናስተላልፈው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ በተለይ እድለኞች ሎተሪ በሚደርሳቸው ጊዜ መንግሥት ብዙ ገንዘብ ይወስድባቸዋል፣ የተለያዩ ድርጅቶችም ለልማትና ለበጎ አድራጐት እያሉ በአስተዳደሩ ጊቢ ሆነው ገንዘብ አምጡ እያሉ ያጨናንቋቸዋል ሲባል ሰምተናል፤ ይህ ግን ትክክል አይደለም ብለዋል አቶ ቴዎድሮስ፡፡

መንግሥት ከ1 ሺ ብር በላይ ከሆኑ ሽልማቶች 15 በመቶውን ብቻ ነው የሚወስደው ሲሉም ተናግረዋል፡፡አሁን በህዳሴው ቶምቦላ መደራረብ ምክንያት የዕጣ መውጫ ጊዜው እንደተራዘመው ቶምቦላ ከ12 ዓመታት በፊት ባለመረጋጋት ሰበብ የአንድ ቶምቦላ ማውጫ ጊዜን አራዝመን ነበር ሲሉ አቶ ቴዎድሮስ አስታውሰዋል፡፡

ወንድሙ ኃይሉ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሐምሌ 6፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • ኢትዮጵያ 16 በመቶ ዜጎቿ ጫት ቃሚ ሆነውባታል ተባለ፡፡ (ንጋቱ ሙሉ)
 • የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ባለ አነስተኛ ገቢ ዜጐች የምጣኔ-ሐብታዊ ዕድገቱ ተጠቃሚነታቸው እምብዛም መሆኑን በጥናቴ አረጋግጫለሁ አለ፡፡ (ትዕግሥት ዘሪሁን)
 • የቶምቦላ መውጫ ጊዜ የተራዘመው በሌሎች ሎተሪዎች መደራረብ ምክንያት ነው ተባለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • ኢትዮ ቴሌኮምን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ አክስረዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በገንዘብ እና በእሥራት ተቀጡ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • ብሪታንያ በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የቤተሰብ ምጣኔ ስራዎች የ90 ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ አደረገች፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በድርቅ ጉዳት ለገጠማቸው ወገኖች የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላዘጋጅ ነው አለ፡፡ (ወንድሙ ኃይሉ)
 • የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተፋጠነ ፍትህ የሚገኝበትን መላ እያጠና መሆኑን የፍርድ ቤቱ የበላይ ተናገሩ፡፡ (ምህረት ስዩም)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ለዛ የምሳ ሰዓት ፕሮግራም ሐምሌ 4፣2009

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲስ የቡና ግብይት ሥርዓት ጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲስ የቡና ግብይት ሥርዓት ጀመረ፡፡አዲሱ ስርዓት የቡና ምርት ወደ መጋዘን ሳይገባ በጥብቅ በተከለለ ማቆያ በመኪና ላይ እንዳለ መሸጥ የሚያስችል ነው፡፡ግብይቱ የሚካሄደው የምርቱንና የምርቱን ባለቤት ማንነት ባስጠበቀ መልኩ እንደሆነ ምርት ገበያው ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ተገኝተን ሰምተናል፡፡

አዲሱ ስርዓት ያለአገናኝ አባል በቀጥታ መገበያየት ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ የህብረት ሥራ ማህበራትና የንግድ ድርጅቶችም የግብይት መድረክ አዘጋጅቷል ተብሏል፡፡ግብይቱን ማካሄድ የሚፈልጉ ግለሰቦች፣ የህብረት ሥራ ማህበራትና የንግድ ድርጅቶች አስፈላጊ መመዘኛዎችን እንዲያሟሉ በማድረግ በቀጥታ እንደሚሣተፉ ተነግሯል፡፡የግብይት ሥርዓቱ ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም አንስቶ ሥራ ላይ እንደዋለም ሰምተናል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲሱን የግብይት ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ተናግረዋል፡፡የመኪና ላይ ግብይትን ለማካሄድ እንዲረዳ ስለአዲሱ የግብይት ሥርዓት ለሚመለከታቸው ሥልጠና ሰጥተናልም ብለዋል፡፡

አዲሱን የግብይት ሥርዓት ውጤታማነት ለማረጋገጥ የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውም ተነግሯል፡፡የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ተደርጎበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደፀደቀም አቶ ኤርሚያስ አስታውሰዋል፡፡ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተለይቶ እራሱን ችሎ ተቋቁሞ የነበረው የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የመጋዝን አገልግሎት ድርጅት ተመልሶ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር እንዲዋሃድ የአደረጃጀት ማሻሻያዎች ተደርገዋልም ብለዋል፡፡

አዲሱ የግብይት ሥርዓት የቡና የወጪ ንግድን ለማሳደግ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ንጋቱ ረጋሣ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የከተማዋ ነዋሪዎች የገባው ክረምት ሊያደርሰው ከሚችለው አደጋ እራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የከተማዋ ነዋሪዎች የገባው ክረምት ሊያደርሰው ከሚችለው አደጋ እራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡ባለሥልጣኑ ዛሬ ጋዜጠኞችን ጠርቶ ሲናገር እንደሰማነው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቤተል አካባቢ በንብረት ላይ ከደረሰ መለስተኛ ጉዳት ውጪ ክረምቱ ከገባ በሰው ህይወት ላይ በጐርፍ ምክንያት የደረሰ አደጋ እስካሁን አልተመዘገበም ብሏል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር አማኑኤል ረዳ የከተማው ነዋሪ ከመንግሥት ጋር በመተባበር የውሃ ቦዮችን በማፅዳት ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ባለመንቀሣቀስ ወንዝ ዳርቻ ያሉ አስቀድመው በመዘጋጀት ሊተባበሩ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል ብለዋል፡፡ባለፈው መጋቢት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የጨረሰው ቆሼና የእንጦጦ አካባቢ የመሬት መንሸራተት ሊያጋጥማቸው ይችላሉ የተባሉ ቦታዎች ናቸው፡፡

የባለፈው ዓይነት አስከፊ አደጋ እንዳይከሰት ባለሥልጣኑና መንግሥት የሰራቸውን ቅድመ ሥራዎች የተጠየቁት ኮማንደር አማኑኤል ኮሚቴ ተቋቁሞ በወንዝ ዳርቻና በሚያሰጉ ቦታዎች ያሉ ሰዎች ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር እየተሰራ ነው ፤ ነገር ግን ነዋሪዎች ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሲሆኑ አይታይም ብለዋል፡፡ከሣምንት በፊት በጐርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች እንዳሉ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል፤ ምንም ሰው አልሞተም ማለት የመረጃ ግጭት አይፈጥርም ወይ? ብለን የጠየቅናቸው ኮማንደሩ በጐርፍ መወሰድና ወንዝ ገብቶ መሞት የተለዩ ናቸው፤ የሞት አደጋ አልተከሰተም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ነዋሪዎቹ በክረምት ከሰል ሲጠቀሙ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ አስበው ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡አሽከርካሪዎችም በክረምቱ ፍጥነታቸውን ቀንሰው በማስተዋል እንዲያሽከረክሩና እራሳቸውንና ንብረታቸውን ከሚደርስ አደጋ ጠብቁ ብለዋል፡፡

ምህረት ስዩም

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ሐምሌ 5፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ክረምቱን ተጠንቀቁ ብሏል፡፡ (ምስክርአወል)
 • ኢትዮጵያ ለዘንድሮው ክረምት 3 ነጥብ 62 ቢሊዮን ችግኞችን ትተክላለች ተባለ፡፡ ባለፉት 3 አመታት ከተተከሉት ውስጥ 78 በመቶዎቹ ፀድቀዋል ተብሏል፡፡ (ምሥክርአወል)
 • የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲስ የቡና ግብይት ስርአት ጀመረ፡፡ በአዲሱ የቡና ግብይት ምርቱ መጋዘን ሳይገባ በማቆያና በመኪና ላይ እንዳለ መሸጥ ያስችላል ተብሏል፡፡ (ንጋቱረጋሣ)
 • የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ በድርቅ ተጐጂ አካባቢዎች ለማደርገው ድጋፍ እጅ እያጠረኝ ነው አለ፡፡ መንግሥት በበኩሉ የዮኒሴፍ ሪፖርት ጊዜው ባለፈበት መረጃ ላይ ተንተርሶ የወጣ ነው ብሏል፡፡ (ንጋቱሙሉ)
 • በአዲስ አበባ መስተዳደር በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የኦዲት ሪፖርት ግኝት ትላንት ይፋ ሆነ፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች በ100 ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሳያወራርዱ ተገኝተዋል፡፡ (ዮሐንስየኋላወርቅ)
 • አዲስ አበባ ከግብር ከፋዮቿ የምትሰበስበው የገቢ መጠን ከአመት አመት እየጨመረ መጥቷል ተባለ፡፡ (ምህረትስዩም)
 • የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ አመት 3ኛ መደበኛ ጉባዔ በዛሬ ውሎው በፍትህ አተገባበሩ ላይ መክሯል፡፡ (ምህረትስዩም)
 • በፖላንድ ክራካኦ ከተማ በተደረገው 41ኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የኦሞ ሸለቆ ቅርስን በሚመለከት የተዘጋጀው ረቂቅ ውሣኔ የኢትዮጵያን ጥቅም እንዲያስጠብቅ ተደርጓል ተባለ፡፡ (የኔነህሲሣይ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በአዲስ አበባ የተካሄደው የቀን ገቢ ግምት ላይ ቅሬታ አለኝ የሚል ቅሬታ አቅራቢ በቡድን ሳይሆን በተናጥል ቅሬታውን ማሰማት ይችላል ተባለ

በአዲስ አበባ የተካሄደው የቀን ገቢ ግምት ላይ ቅሬታ አለኝ የሚል ቅሬታ አቅራቢ በቡድን ሳይሆን በተናጥል ቅሬታውን ማሰማት ይችላል ተባለ፡፡በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አራተኛ ዓመት ሦስተኛ መደበኛ ጉባዔ በምክር ቤቱ አባላት በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ የታክስ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ነፃነት አበራ ዛሬ መልስ ሲሰጡ አርፍደዋል፡፡

የቀን ገቢ ግምቱ ከመካሄዱ በፊት የምክር ቤት አባላትና የነጋዴው ማህበረሰብ ተወያይቶበት ነው ወደ ሥራ የተገባው ነገር ግን በግምቱ ወቅት እቃ በማሸሽና በሌሎችም ችግር የፈጠሩብን ነጋዴዎች ነበሩ፤ ይህም ተቀራርበን ባለመሥራታችን የተፈጠረ በመሆኑ መሥሪያ ቤቱ እንደ ማስተካከያ ይወስደዋል ብለዋል፡፡

የቀን ገቢ ግምቱ የማይመለከታቸውና በአነስተኛ የጉሊት ንግድ የሚተዳደሩ የንግድ ማህበረሰቦች በግምቱ ተካተዋል፣ ይህም በርካታ ቅሬታን አስነስቷል ተብለው የተጠየቁት ወ/ሮ ነፃነት ግምቱ የሚመለከታቸውና የሚያገኙት የቀን ገቢ መጠን ተመጣጣኝ ሆኖ በመገኘቱ የተካተቱ እንጂ ሁሉም አነስተኛ ጉሊት ነጋዴ በግምቱ አልተካተተም አሰራሩ ፍትሃዊ ነበር ብለዋል፡፡

የቀን ገቢ ግምቱ ከመካሄዱ በፊትም ቅሬታ ሊነሳ እንደሚችል በመሥሪያ ቤቱ ይታወቃል፣ አሁንም የሚነሱትን ማንኛውም ከግብር ጋር የሚያያዙ ቅሬታዎች ለመፍታት ቅሬታ አቅራቢዎች በቡድን ሳይሆን በተናጥል መሥሪያ ቤቱ እያስተናገደ ነው ብለዋል፡፡

በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ቅሬታ ያላችሁ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ 15 ድረስ፣ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 15 እስከ ሐምሌ 30 እንዲሁም የደረጃ ሀሌታው “ሀ” ግብር ከፋዮች ከነሐሴ 1 እስከ 30 ቅሬታችሁን ማስገባት ትችላላችሁ ተብላችኋል፡፡

ምህረት ስዩም
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers