• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

መጋቢት 24፣ 2012/ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መወሰኑ ነው

ይሁንና የግል ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው የሚያዚያ ወር ክፍያን እንዲከፍሉ በማስታወቂያ ጥሪ በማድረግ ላይ እንደሆኑ እየታየ ነው፡፡ይህን ተከትሎም ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የእንተሳሰብ መልዕክት እንዳስተላለፉ ተሰምቷል፡፡ በየነ ወልዴ ይኽ ጉዳይ እንዴት ይታያል ሲል የሚመለከታቸውን አነጋግሯል፡፡
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣ 2012/ ከለይቶ ማቆያ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የወጣ ግለለሰብ ስለመኖሩ ጥቆማ በመድረሱ እርምጃ ለመውሰድ የፌደራል ፖሊስ የማጣራት ስራ ጀምሯል

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ከለይቶ ማቆያ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የወጣ ግለለሰብ ስለመኖሩ ጥቆማ በመድረሱ እርምጃ ለመውሰድ የፌደራል ፖሊስ የማጣራት ስራ ጀምሯል ሲሉ ተናገሩ፡፡ጉዳዩ እውነት ከሆነ ከባድ ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው፡፡ ለይቶ ማቆያ በተደረጉ ሆቴሎች ላይም ቁጥጥራችንን እናበረታለን ብለዋል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣2012 / በኤርትራ ትናንት (March 31) እና ዛሬ (April 1) በተካሄዱ ምርመራዎች ሦስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ መሆናቸው መረጋገጡን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ተናገረ

ከሕሙማኑ ሁለቱ፤ የ32 ዓመት ወንድ እና የ52 ዓመት ሴት ሀገሪቱ በመንገደኛ በረራዎች ላይ እግድ ከመጣሏ በፊት ከባህር ማዶ ወደ ኤርትራ እንደገቡ ሚኒስቴሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።ሦስተኛዋ ታማሚ የ13 ዓመት ልጃገረድ ስትሆን፣ ከውጭ ሀገር ከመጣች እናቷ ቫይረሱ የተላለፈባት መሆኗን መግለጫው ጠቅሷል። እናትየውና የቤተሰቧ አባላት ባለፈው ሳምንት በለይቶ ማቆያ ተወሽበው እንደቆዩ የሚኒስቴሩ መግለጫ ተናግሯል።

ይህም በኤርትራ እስከዛሬዋ ዕለት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡትን ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 18 አድርሶታል።ሁሉም ሕሙማን አስፈላጊው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የጤና ሚኒስቴሩ መግለጫ ጠቁሟል።

ዘከሪያ መሐመድ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣2012/ አትክልት ተራ ወደ ጃንሜዳ እንዲዛወር ተወሰነ

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከከተማው የፀጥታ አካላት ጋር አትክልት ተራ አካባቢ እየታየ ባለው መጨናነቅ ዙሪያ ተወያይተዋል።ቦታው የከተማዋ ከፍተኛ የአትክልት ምርት ማከፋፈያ ሲሆን ከፍተኛ የሰው ጭንቅንቅ በየእለቱ የሚታይበትና ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘም ለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑ ተገምግሟል።

ስለሆነም ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የአትክልት ግብይቱ በጊዜያዊነት ወደ ጃንሜዳ እንዲዘዋወር ተወስኗል።አትክልት ተራ ለጊዜው ለነጋዴዎቹ እንደ እቃ ማስቀመጫ(ስቶር) ብቻ እንዲያገለግል ተወስኗል።ጃንሜዳ ቦታው ሜዳማ እንደመሆኑ ለእንቅስቃሴ ምቹ መሆኑና ለቁጥጥር አመቺ መሆኑ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው የአትክልት ግብይቱ ወደ ጃንሜዳ እንዲዘዋወር የተደረገው።

ህይወት ፍሬስብሀት
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣ 2012/ የዳቦ ዋጋ በሚጨምሩና ግራም በሚቀንሱ ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስጠነቀቀ

ከሰሞኑ አንዳንድ ዳቦ ቤቶች ያለምንም ምክንያት የዳቦ ዋጋ ሲጨምሩና ግራም ሲቀንሱ መታየቱን ከደረሱኝ መረጃዎች አውቄያለሁ ብሏል ቢሮው፡፡በመሆኑም ምንም ዓይነት የአቅርቦት እጥረት በሌለበት በዚህ ወቅት በእንዲህ ዓይነት ድርጊት መሳተፍ በህግ የሚያስጠይቅ ነው አላልፋችሁም ሲል አስጠንቅቋል፡፡

ከዚህ በኋላ በሚደረገው ክትትል በድርጊቱ ሲሳተፉ የማገኛቸው ዳቦ ቤቶች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል ባወጣው መግለጫ ተናግሯል፡፡

ማህሌት ታደለ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣ 2012/ በአዲስ አበባ ታክሲና ባጃጆችን ስራ ሊያስቆም እንደሚችል የከንቲባ ፅህፈት ቤት አስጠነቀቀ

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በከተማዋ የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተሽከርከሪዎች ትርፍ ከመጫን እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡አውቶሰብሶችም በወንበር ልክ ብቻ እንዲጭኑ መደረጉ ይታወቃል፡፡ይሁንና የከተማ አስተዳደሩ አደረግሁት ባለው ቁጥጥር ታክሲዎችና ባጃጆች ትርፍ እየጫኑ መሆኑን ታዝቤያለሁ ብሏል፡፡

ስለሆነም በፍጥነት የማያስተካክሉ ከሆነ የነዋሪውን ጤንነት ለመጠበቅ ሲባል ባጃጆችንና ታክሲዎችን ከስራ ውጭ ለማድረግ እንደሚገደድ የከንቲባ ፅ/ቤት አስጠንቋል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣ 2012/ ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት ፍላጎትን ታሳቢ በማድረግ እየቀረቡ ያሉ የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄዎችን እየመረመርኩ ነው አለ

ኢትዮ ቴሌኮም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተወሰደውን በቤት ውስጥ የመቀመጥ እርምጃ ተከትሎ የሚፈጠረውን ከፍተኛ የቴሌኮም አጠቃቀምና የኢንተርኔት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ እየቀረቡ ያሉ የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄዎችን እየመረመርኩ ነው አለ፡፡

ተህቦ ንጉሴ

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣ 2012/ የጤና ሚኒስቴር ለህክምና ባለሞያዎች የእናት አገር ጥሪ አቀረበላቸው

በኢትዮጰያ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እችል ዘንድ እገዛችሁ ያስፈልገኛል ሲል የጤና ሚኒስቴር ለበጎ ፈቃደኞች ጥሪ አቅርቧል፡፡በጤና ሙያ ተመርቃችሁ ወደ ስራ ያልገባችሁ ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የምትሰሩ የጤና ባለሞያዎች ፣ በጡረታና በተለያዩ ምክንያቶች ከስራ የተገለላችሁ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና በመንግስትና በግል ትምህርት ተቋማት ያላችሁ የጤና ተማሪዎች አብራችሁኝ እንድትሰሩ እሻለሁ ብሏል፡፡የኮሮና ወረርሽኝ እየከፋ ከመጣ እንዲህ ያሉ ባለሞያዎች በብዛት ያስፈልጉኛል ያለው ሚኒስቴሩ ከነገ ጀምሮ በድረገፄ ላይ ተመዝገቡ ብሏል፡፡

ቴዎድሮስ ብርሃኑ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣ 2012/ በትግራይ ክልል የሚገኙ ባለሀብቶች ሆቴሎቻቸውንና መኖሪያ ቤታቸውን ለኮሮና ቫይረስ መከላከል ስራ መስጠታቸው ተሰማ

በዞኑ ከሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ውጪ ለኮሮና ለይቶ ማቆያ ቦታ የተዘጋጀ ባለመሆኑ የበሽታውን መከላከል ስራ ፈታኝ አድርጎታል ሲሉ የትግራይ ደቡባዊ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ሀላፊ ወ/ሮ ሙሉ ካልአዩ ተናግረዋል፡፡በዞኑ የሚገኙ ሶስት ባለሀብቶች ለዚሁ መፍትሄ እንዲሆን ሆቴላቸውንና መኖሪያ ቤታቸውን በፈቃደኝነት እንደሰጡ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሁለቱ ባለሀበቶች በአጠቃላይ 70 አልጋዎች ያሏቸውን ሆቴሎች ለኮሮና መከላከያ ያስረከቡ ሲሆን አንድ ባለሀብት ደግሞ መኖሪያ ቤታቸውን ማስረከባቸው ተናግረዋል፡፡በተጨማሪም ግለሰቦቹ የእጅ መታጠቢያ ሳሙናና የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ድጋፎች አድርገዋል ተብሏል፡፡እንዲሁም ኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው ቶሚ ኢንተርናሽናል ሆቴል ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ 44 ክፍሎች ያሉት ሆቴሉን ለመንግስት አስረክቧል፡፡

ምህረት ሥዩም
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣ 2012/ የኮሮና ቫይረስ የማገርሸት ባህሪ ስላለው ሰዎች አንዴ ላለመያዝ ብቻም ሳይሆን ዳግም ላለመለከፍም ጭምር በማሰብ ጥንቃቄያቸው ላይ ሊበረቱ እንደሚገባ ተነገረ

የኮሮና ቫይረስ የማገርሸት ባህሪ ስላለው ሰዎች አንዴ ላለመያዝ ብቻም ሳይሆን ዳግም ላለመለከፍም ጭምር በማሰብ ጥንቃቄያቸው ላይ ሊበረቱ እንደሚገባ ተነገረ፡፡ሸገር ያነጋገራቸው የህክምና ባለሞያ ዶ/ር ናትናኤል በኩረፂዮን እንደተናገሩት ከሆነ የኮሮና ቫይረስ እንደማንኛውም የጉንፋን በሽታ ዓይነት መገለጫ አለው ብለዋል፡፡

አንዴ በቫይረሱ ለተያዘ ሰው የሚሰጠው ህክምና በሽታ የመከላከል አቅሙን እንዲጨምር የሚያደርግለት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ስለሆነም ህብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ ራሱንና ሰዎችን መጠበቁ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሆነ በማሰብ እንደሚጠበቀው ከቤት ባለመውጣት ፣ ከወጡም ርቀትን በመጠበቅና እጅን አብዝቶ አሽቶ ከመታጠብ እንዳይቦዝን ተመክሯል፡፡

ቴዎድሮስ ብርሃኑ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መጋቢት 23፣ 2012/ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ-“በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ሁለት ጉልህ ፈተናዎች ገጥመውናል፤ አንደኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ራሱ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን የተመለከተ ጉዳይ ነው”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የሕዳሴ ግድብ መሠረት የተጣለበትን 9ኛ ዓመት በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፣ “በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ሁለት ጉልህ ፈተናዎች ገጥመውናል፤ አንደኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ራሱ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን የተመለከተ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡

በሀገራችን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ዛሬ በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም፣ በሚቀጥሉት ሳምንታት ሊያሻቅብ እንደሚችል፣ ምናልባትም ሞት ሊጋጥምም ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከአዲስ አበባ አልፎ በክልል ከተሞችም እየታየ ያለው ይህ በሽታ፣ ለቁጥጥር እንዳያስቸግርና አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው መንደሮች እንዳይገባ ሁላችንም መረባረብ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከምትጠነቀቅላቸውና በስስት ከምታያቸው ጸጋዎቿ ሁለተኛው የሕዳሴ ግድባችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የሕዳሴ ግድባችን ከዕለት ጉርሳችን ቀንሰን በተባበረ ክንድ እየገነባን እዚህ ያደረስነው ብቻ ሳይሆን፣ የማድረግ ዐቅማችንን ያሳየንበት ትልቁ ጸጋችን ነው ብለዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው፣ “ለግድባችን ከፍ ያለ ግምት የምንሰጠው አንድም የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ ሁለትም የትሥሥራችን ገመድ በመሆኑ ጭምር ነው” ካሉ በኋላ፣ “የፊታችን ክረምት ግንባታው ተገባድዶ የውኃ ሙሌት እንጀምራለን” ብለዋል፡፡

“የኮሮና ወረርሽኝ በዚህ ወቅት መከሠቱ ትኩረታችንን ቀንሶ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችንን በማጓተት ቀላል የማይባል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ግልጽ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “በወረርሽኙ ምክንያት ተዘናግተን የግድብ ባለቤት የመሆን ጉዟችን ማዝገም የለበትም” ብለዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ “እስከዛሬ አሳድገን አሳድገን ፍሬውን ለማየት የጓጓንለት ልጃችንን፣ አሁን በተጋረጠብን አደጋ ምክንያት ፍሬውን ከማየት መገታት የለብንም” ብለዋል፡፡“ቤት በመቀመጥና ቶሎ ቶሎ ንጽሕናችንን በመጠበቅ የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል በአንድ በኩል፤ የሕዳሴ ግድባችን ግንባታው ተጠናቅቆ በቶሎ የውኃ ሙሌቱ እንዲጀመር በዐቅማችን መዋጯችንን መላክ በሌላ በኩል ከሁላችንም ይጠበቃል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል ቤት ውስጥ መቀመጥ አስቸጋሪ ሊሆንና፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሳራዎችን ሊያደርስ እንደሚችል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሌላ መልኩ ከታየ ግን ይሄን አጋጣሚ ለመልካም ተግባራት ማዋል እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡

“ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅር የሚሰጡበት፤ ባለትዳሮች ስለ ሕይወታቸው በሰፊው የሚያቅዱበት፤ እንዲሁም ማንበብ የሚፈልጉ ሰዎች ጊዜ ወስደው እንዲያነብቡ፤ የሚጽፉ ሰዎች ጊዜ አግኝተው እንዲያሰላስሉ፣ የሚመራመሩ ሰዎች እንዲመራመሩ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል” ብለዋል፡፡“በዚህ መልኩ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ውጭ ከመውጣት ተቆጥበው ቤታቸው የሚያሳልፉ ዜጎቻችን ራሳቸውንና ሌሎችንም ከክፉው ወረርሽኝ ከማዳን በዘለለ፣ ወረርሽኙ አልፎ ሁሉም ነገር ሲረጋጋ ብዙ መልካም ነገሮችን ማትረፋቸው አይቀርም” ብለዋል፡፡

ኮሮናን ለመከላከልም ሆነ ግድቡን ለማጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ በማሸነፍ ወኔ መነሣት አለበት ብለዋል።የኮሮና ሥርጭትን ለመግታት ከሰዎች ንክኪ ርቀታችንን በመጠበቅና ራሳችንን መግዛት እንደሚገባን ሁሉ፤ ከሌሎች ሀገራት ርዳታ ለመዳን ለግድባችን ግንባታ ቦንዳችንን መግዛት ይጠበቅብናል፡፡በዚህ መልኩ በመጪው ወራት ውስጥ በዝቅተኛ የጉዳት ሰለባ ኮሮናን ከሀገራችን አጥፍተን፤ በአፋጣኝ ሕዳሴ ግድባችንን የመጀመሪያውን የውኃ ሙሌት አጠናቅቀን ሁላችንም ስኬታችንን ለማየት እንደምንበቃ አልጠራጠርም ብለዋል፡፡

ዘከርያ መሐመድ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers