• United Bank S.C.

  ሕብረት ባንክ አ.ማ.

 • Slider Two

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

 • Sldier Three

  የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አራት አምቡላንሶችን በማሰማራት ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ በደረሰው አደጋ ምክንያት የተጐዱ 110 ዜጎችን ወደ ቢሾፍቱ ሆስፒታል ማድረሱን ተናገረ…

በማህበሩ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት 40 በጐ ፈቃደኞችንና 4 አምቡላንሶችን በቦታው በማሰማራት በአደጋው የተጐዱ ሰዎችን መርዳቱን ተናግሯል፡፡ ለተጐዱ ሰዎች የመጀመሪያ እርዳታ ከመስጠት በተጨማሪ ህይወታቸውንም ለማትረፍ ወደ ቢሾፍቱ ሆስፒታል ሲያመላልስ መዋሉን ሰምተናል፡፡

በማህበሩ የኮሙኒኬሽንና የሃብት ማሰባሰብ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ደግሰው አማኑ ለሸገር እንደተናገሩት ከአደጋው ጋር በተገናኘ በርካታ ሰዎች ከሆራ አርሰዲ ሃይቅ አካባቢ ወዳለ ጥልቅና አደገኛ ገደል የገቡ በርካቶች ነበሩ፡፡ ገደሉም አንሸራታችና በራስ ጥረት ለመውጣት አስቸጋሪ እንደነበር የተናገሩት አቶ ደግሰው የቀይ መስቀል ማህበር በጎ ፈቃደኞች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጐችን ከገደል አውጥተው ወደ ሆስፒታል አደርሰዋቸዋል ብለዋል፡፡

ትላንት በቢሾፍቱ ከተማ የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ በደረሰው አደጋና ህይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቀይ መስቀል ማህበር ማዘኑንም ለሸገር ተናግሯል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መስከረም 23፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • ትናንትና በኢሬቻ በአል ላይ በተከሰተ ግርግር የ52 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን መንግሥት ተናገረ፡፡ (ፋሲል ረዲ)
 • ፖሊሲ አውጭዎችና አስፈፃሚዎች ፖሊሲዎቻቸውን ሥራ ላይ ከማዋላቸው አስቀድሞ የሕብረተሰቡን ባህልና አኗኗር ከግምት ሊያስገቡት ይገባቸዋል ተባለ፡፡ (ምስክር አወል)
 • በኢትዮጵያ የገጠሩ ነዋሪ ከግብርናው መስክ ውጭ የሚያገኘው ገቢ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ አንድ ምሁር ተናገሩ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • በሞሮኮ ማራካሽ የተደረገው የአፍሪካ ግብርና ጉባዔ ለመጪው የአለም የአየር ጠባይ ለውጥ ጉባዔ እንደ አንድ የአፍሪካ ድምፅ የሚታይ ነው ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ከተጋረጠበት ስጋት መላቀቅ አለመቻሉ ተሠማ፡፡ (ተህቦ ንጉሴ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የ2008 የቅድመ ትንበያ ስራዬን በአግባቡ ሰርቻለሁ አለ

በተለይም በአቪዬሽን ዘርፍ ከድርጅቱ ጋር በመናበብ የሠራሁት ሥራ አጥጋቢ ነው ብሏል፡፡የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ ዛሬ ኤጀንሲው ከባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ባለው ምክክር ላይ ሲናገሩ እንደሰማነው ኤጀንሲው በጊዜ በመጠን፣ በቦታና በጥራት ትንበያዎችን በማዘጋጀት ከአየር ሁኔታ እና ጠባይ ጋር ዝምድና ባላቸው አደጋዎች ላይ ዝግጅት በማድረግ ጥሩ ሰራ ሰርቷል፡፡

የአጭር፣ የመካከለኛ እንዲሁም የረጅም ጊዜ የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን፣ ሣይንሣዊ ልኬቶችንና የትንበያ ሞዴሎችን በመተንተን የማህበረ ምጣኔ ሀብታዊ ተቋማት እንዲጠነቀቁ መክረናል ብለዋል፡፡ ኤጀንሲው የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት የአሰራር አግባቦችን በመጠቀም እየጨመረ ያለውን የአየር ትንበያ ፍላጐት ለማሳደግ በተለይም ለአቪዬሽኑ ኢንዱስትሪ የ24 ሰዓት የጠራ ትንበያ ለመስጠት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡

የአየር ንብረት ተፅዕኖ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚነካ በመሆኑ ኤጀንሲው ኃላፊነቱን በመውሰድ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በውይይት መድረኩ ላይ ሲነገር ሰምተናል፡፡የባለ ድርሻ አካላቱ ምክክር ቦሌ በሚገኘው ሞሞና ሆቴል ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል፡፡

አስፋው ስለሺ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 80 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች ጠፉብኝ ሲል UNHCR ተናገረ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የኢትዮጵያው ቢሮ እንዳለው እስከ ነሀሴ መጨረሻ 161 ሺህ 615 ኤርትራውያን በስደት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ እና የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 81 ሺህ ገደማ የሚሆኑ በስድስቱም መጠለያ ካምፓች ውስጥ የሉም ተብሏል፡፡

አቶ ክሱት ገ/እግዚአብሔር የUNHCR ቃል አቀባይ ሲሆኑ ለሸገር እንደተናገሩት በርግጥ ኤርትራውያኑ ከሌሎች ስደተኞች በተለየ ሁኔታ በከተሞች መኖር እንዲችሉ በኢትዮጵያ መንግሥት መብት የተሰጣቸው ቢሆንም እነዚህ ግን በህጋዊ መንገድ ያልወጡ ናቸው ብለዋል፡፡

UNHCR ስደተኞቹ የት እንዳሉ ፍለጋ እያደረገ መሆኑንም ሰምተናል፡፡በህጉ መሠረት ስደተኞች በስደት ከገቡ በኋላ እስከ አራት ወራት ቢኖሩም ባይኖሩም እንደ ስደተኛ ይመዘገባሉ ካዛ በኋላ የሚደረግላቸው ድጋፍ ይቋረጣል ይላሉ ቃል አቀባዩ፡፡በክረምቱ ወቅት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ስደት ቁጥሩ በአንፃራዊነት ይቀንሳል ምክንያቱ ደግሞ ወንዝ ስለሚሞላ መሻገር ስለሚያዳግት መሆኑንም አቶ ክሱት ነግረውናል፡፡

በበጋው ወቅት በአማካይ በወር እስከ 3 ሺህ የኤርትራ ስደተኛ ወደ ኢትዮጵያ ይገቡ የነበረ ሲሆን በክረምቱ ወቅት ቁጥሩ 2 ሺህ እና ከዛ በታች ይገመታል ሲሉ አቶ ክሱት ነግረውናል፡፡ኢትዮጵያ ከአለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት ጋር በትብብር 6 የስደተኛ ካምፖችን ያዘጋጀች ሲሆን አራቱ በትግራይ፣ ሁለቱ በአፋር ክልሎች ይገኛሉ፡፡

ፋሲል ረዲ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ከ39 ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው ተባለ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን የውጪ ዕርዳታው ቢቀንስብኝም በጤናው ዘርፍ ለምሰጠው አገልግሎት ላይ ከመድኃኒት አቅርቦት ችግር ባሻገር ብዙም ችግር አልገጠመኝም አለች፡፡የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን ለነፃ ታካሚዎቹ በተዘዋዋሪ ክፍያ ለምሰጠው አገልግሎት ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ ቢሰጠኝ መልካም ነው ብላለች፡፡

ቤተክርስቲያኗ ይህን ያለችው ትላንት በተጀመረውና ዛሬም በቀጠለው 7ኛው የቤተክርስቲያኒቷ አመታዊ የጤና ጉባዔ ላይ ነው፡፡የቤተ-ክርስቲያኗ የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ፕሮግራም አስተባባሪው አቶ ሽፈራው ማሞ ለሸገር እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኗ ባሏት 83 የጤና ተቋማት በነፃ እና በአነስተኛ ክፍያ ለምትሰጠው አገልግሎት ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ታደርጋለች፡፡

ይህም ህክምናውን በነፃ የሚሰጡት በጐ አድራጊዎች ደሞዝ ሳይሰጥና የአንዳንድ ቁሳቁሶች ዋጋ ሳይካተት ነው ብለዋል፡፡በተለይም ለገጠሩና ለጠረፍ አካባቢ ህብረተሰብ የጤና አገልግሎት ለሚሰጡት ባለሙያዎችም መንግሥት እንደራሱ ባለሙያዎች ስልጠና እንዲሰጥልን ወስነናል ሲሉ ነግረውናል፡፡በቤተ-ክርስቲያኒቱ እስከ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች በአመት የጤና አገልግሎት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ትሰጣለች ተብሏል፡፡

ዮሐንስ የኋላወርቅ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መስከረም 20፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

 • ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ 80 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች ጠፉብኝ ሲል UNHCR ተናገረ፡፡ (ፋሲል ረዲ)
 • የኢሬቻ በአል ላይ ከ4 ሚሊዮን በላይ ታዳሚዎች ይገኛሉ ተባለ፡፡ (ፋሲል ረዲ)
 • የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የአተት በሽታ ወንዶ ገነት አካባቢ ካለው ምልክት በስተቀር በቁጥጥር ሥር አውዬዋለሁ ብሏል፡፡ በወንዶ ገነት የታየው የበሽታ ምልክትም ምክንያቱ መታወቁን ተናግሯል፡፡ (አስፋው ስለሺ)
 • የኢትዮጵያ የዱቄት አምራቾች ማህበር የዱቄት ፋብሪካዎች የምርት ጥራታቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳ ሥራ እየሰራሁ ነው አለ፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • በትውልደ ኢትዮጵያዊው የተሰራው የኢ-ለርኒንግ አፕሊኬሽን ለአፍሪካ የትምህርት እድገት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ (ፋሲል ረዲ)
 • በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ከ39 ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው ተባለ፡፡ (ዮሐንስ የኋላወርቅ)
 • የኢትዮ ጅቡቲ ሰበታ - መኤሶ የባቡር መስመር የፊታችን ረቡዕ ይመረቃል ተባለ፡፡ (የኔነህ ሲሣይ)
 • የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከአባላቱ ጋር ዛሬ ተወያይቷል፡፡ ስለ ሠራቸው ሥራዎችም ተናግሯል፡፡ (ምህረት ስዩም)
 • ብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ የ2008 ዓ.ም ቅድመ ትንበያ ሥራ የተሣካ ነበር አለ፡፡ (አስፋው ስለሺ)
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሣት አለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ሊከፈት ነው

የጨርቃ ጨርቅና አልባሣት አለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ሊከፈት ነው፡፡ከመስከረም 24 እስከ መስከረም 27 በሚቆየው የንግድ ትርዒት ላይ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያዎች የአልባሣት፣ የቴክኖሎጂ እና የኬሚካል እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶች አቅራቢዎችና ድርጅቶች ይካፈሉበታል ተብሏል፡፡

ከአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንን ጨምሮ ከ25 አገሮች የተወጣጡ ከ180 በላይ አምራቾች የሚሣተፉበት የንግድ ትርዒት የሚካሄደው በሚሊኒየም አዳራሽ ነው፡፡ከንግድ ትርዒቱ ጋርም የተለያዩ አውደ ጥናቶች የሚቀርቡ ሲሆን በተለይም አሜሪካ ለታዳጊ አገሮች በሰጠችው ከቀረጥ ነፃ የገበያ እድል /አገዋ/ ላይ እስካሁን ምን ያህል ተጠቅመውበታል የሚለው ጥናት ይቀርብበታል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም እንደሚጐበኙ ሰምተናል፡፡

ዮሐንስ የኋላወርቅ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መስከረም ከጠባ አንስቶ 30 ሺህ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ኢትዮጵያ ገብተዋል ተባለ

መስከረም ከጠባ አንስቶ 30 ሺህ ገደማ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ተባለ፡፡ሀገሪቱ ሰላም መሆን ስላቃታት በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ዜጐችዋ ቁጥርም በአማካይ አንድ ሺህ ነው ተብሏል፡፡ከስደተኞች እና ስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ጋር በጋራ የሚሰራው UNHCR ኢትዮጵያ ባወጣው መግለጫ እንደተናገረው ስደተኞቹ በመስከረም ወር ቁጥራቸው ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡

መስከረም ከጠባ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ 29 ሺህ 769 ደቡብ ሱዳናዊያን የእርስ በርስ ግጭቱ አፈናቅሏቸው ጋምቤላ ክልል ደርሰዋል ተብሏል፡፡ከዚህ በተጨማሪም 12 ሺህ 756 ስደተኞች የተመዘገቡ እና ወደ ጄዊ፣ ኩሌና ቲርኪዲ የመጠለያ ጣቢያዎች በዳግም ሰፈራ እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡

በወሩ ጋምቤላ ክልል ከደረሱት ስደተኞች 17 ሺህ 013 የሚሆኑት በፓጋክ የመለጠያ ጣቢያ የሚኖሩ ናቸውም ተብሏል፡፡ከአዲስ መጪዎቹ ስደተኞች መካከል 3 ሺህ 188ቱ ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ህፃናቶች ናቸው፡፡ከአጠቃላዩ ስደተኞች ደግሞ 64 በመቶውን የሚሸፍኑትም እነዚሁ ህፃናት መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ከስደተኞቹ 80 በመቶ የሚሆኑት ከአፐር ናይል ግዛት የተሰደዱ ናቸው ተብሏል፡፡

የመሰደዳቸው ምክንያት ተብሎ የተዘረዘረውም ያልተረጋጋው የደቡብ ሱዳን ሁኔታም እንዲሁም ደግሞ የምግብ እጥረትና ሥራ ፍለጋ መሆኑም ተነግሯል፡፡በኢትዮጵያ 311 ሺህ የሚሆኑ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች እንደሚገኙ የUNHCR Ethiopia መረጃ ተናግሯል፡፡

ፋሲል ረዲ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

የአፍሪካ የዕድገት ሽግግርና የፍልሰተኞች ጉዳይ በሚል በአዲስ አበባ አህጉር አቀፍ ጉባኤ ሊዘጋጅ ነው ተባለ

በአዲስ አበባው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ከቀናት በኋላ ይዘጋጃል የተባለው የአፍሪካ የዕድገት ሽግግርና የፍልሰተኞች ጉዳይ አህጉራዊ ጉባዔ ፍልሰትን ለለውጥ ማዋያ በሚሆኑ ነጥቦች ላይ ይመክራል ተብሏል፡፡ የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎች አጋሮች ባዘጋጁት ጉባኤ ላይ በእውቀታቸው አንቱ የተባሉ አለም አቀፍ ምሁራን በመገኘት ፍልሰትን እንደምን አድርጋ አፍሪካ ለለውጧና እንዲሁም ለሽግግሯ ትጠቀምበት በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ የምርምር ወረቀት ያቀርባሉ ተብሏል፡፡

ለፍልሰት ህጋዊውን ጥበቃ በማድረግና ደንብ በማዘጋጀት አህጉሪቷ ብዙ የእድገት እርምጃዎችን እንድታመጣ የፍልሰትን መልካም ገፅታ ማበረታታት እንደሚገባም በጉባኤው ላይ ይነገራል መባሉንም ከአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሰምተናል፡፡ ከቀናት በኋላ በአዲስ አበባ የሚዘጋጀው የአፍሪካ የዕድገት ሽግግርና የፍልሰት ጉዳይ ጉባኤ ለፖሊሲ አውጭዎችና ለመንግሥት ኃላፊዎች የበለጠ አቅም የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡

የአፍሪካ የልማት ፕሮግራምን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው የአፍሪካ የዕድገት የሽግግርና የፍልሰት ጉባኤ ለአህጉሪቷ እድገት መሠረት የሚጥልና ህገ-ወጥ የሥራ ዝውውርንና ህገ-ወጥ ፍልሰትን የሚያስቀር ነው መባሉንም ሰምተናል፡፡በጉባኤው ላይ ለመገኘት የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ሰምተናል፡፡

የኔነህ ሲሳይ
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ዩኒቨርስቲ እንቀይራችሁ የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን አትስሙ ሲል የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ተናገረ

የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዘንድሮ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ወስደው ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተመደቡ ተማሪዎችን የተመደባችሁበትን ዩኒቨርስቲ እንቀይርላችኋለን እያሉ በድረ-ገፆችና በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚንሸራሸሩ ወሬዎች ተቀባይነት የላቸውም አለ…

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘሪሁን ዱሬሳ ለሸገር እንደተናገሩት አንድ ጊዜ ምደባ ከተደረገ በኋላ ድጋሚ ቅያሬ አይደረግም በመሆኑም እናስቀይራለን እያሉ የሚያስወሩት አላግባብ ጥቅም ፈላጊዎችና በኤጀንሲያችንም ሆነ በትምህርት ሚኒስትር እውቅና የላቸውም ብለዋል፡፡

ዶክተር ዘሪሁን በሀገራችን የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚቀበሉት ኤጀንሲው የላከላቸውን የተማሪዎች ዝርዝር ብቻ ስለሆነ ወላጆችም ሆነ ተማሪዎች በመታለል ገንዘባችሁን ያለ አግባብ እንዳትከፍሉ ተጠንቀቁ ብለዋል፡፡ ተማሪዎች መቀየር ቢፈልጉ በምን መልኩ መቀየር ይችላሉ? ብለን የጠየቅናቸው ዶክተር ዘሪሁን፣ “አንድ ጊዜ ምደባ ከተደረገ በኋላ በፍፁም መቀየር አይቻልም” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

ምስክር አወል
አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

መስከረም 19፣2009 የሸገር ወሬዎቻችን

Audio clip: Adobe Flash Player (version 9 or above) is required to play this audio clip. Download the latest version here. You also need to have JavaScript enabled in your browser.

 • ዩኒቨርስቲ እንቀይራችሁ የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን አትስሙ ሲል የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ተናገረ፡፡ (ምስክርአወል)
 • ድርጅቶችና ታላላቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አካል ጉዳተኞችን የማካተትን ፅንሰ ኃሣብ ተግባራዊ እያደረጉት አይደለም ሲል የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ተናገረ፡፡ የአካል ድጋፍ መሣሪያዎች ውድነት አካል ጉዳተኞችን ጥገኛ እያደረገ ነውም ብለዋል፡፡ (አስፋውስለሺ)
 • በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ የሰነድ መያዣ የቆዳ ውጤቶችን ለሚያመርቱ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የሚሆን የብድር የዋስትና ማስያዣ ስምምነት በሦስት ተቋማት መካከል ዛሬ ይፈረማል ተባለ፡፡ (የኔነህሲሣይ)
 • ባለፈው አመት መንግሥት ከገዛው የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ መካከል ሩብ ያህሉ ገበያ ለማረጋጋት የተገዛ ነው፡፡ ቀሪው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያህሉ ስንዴ የተገዛው ደግሞ በድርቅ ለተጐዱ እርዳታ እንዲሆን ነው ተባለ፡፡ (ትዕግስትዘሪሁን)
 • የዲኢህዴን የከፍተኛ የፓርቲው መሪዎች ግምገማ በሀዋሣ ከተማ ትላንትና ተጀምሯል፡፡ (የኔነህሲሣይ)
 • መስከረም ከጠባ አንስቶ 30 ሺህ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ኢትዮጵያ ገብተዋል ተባለ፡፡ (ፋሲልረዲ)
 • የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሣት አለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በአዲስ አበባ ሊከፈት ነው፡፡ (ዮሐንስየኋላወርቅ)
 • የኢትዮጵያ የዶሮ እርባታ እና ማቀነባበሪያ ዘርፏ እንዲያድግ ኔዘርላንድ ድጋፍ እያደረገች ነው ተባለ፡፡ (ተኅቦ ንጉሴ)
 • የአፍሪካ የዕድገት ሽግግርን እና ስደተኞችን የተመለከተ ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው፡፡ (የኔነህሲሣይ)

 

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers