ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች
የተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ዛሬ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቦ በሙሉ ድምፅ ፀደቀ
የተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ በተበታተነ መልኩ ሲተገበሩ የነበሩ የግብር ህጐችን ወደ አንድ በማሰባሰብ እና ግብር የማይከፈልባቸው የገቢ ዓይነቶች ወደ ግብር መረብ በማስገባት ወጥና ፍትሐዊ የግብር አከፋፈል ሥርዓት እንዲኖር ይረዳል ተብሏል፡፡
የገቢ ግብር አዋጁ በመሻሻሉ መንግሥት በአመት ከተቀጣሪው ህብረተሰብ ያገኝ የነበረውን 3 ቢሊየን ብር ያሳጣዋል፡፡ ይሁን እና እስካሁን ግብር የማይከፈልባቸው የሥራ ዘርፎችም ወደ ግብር ከፋይነት በማስገባት ከተቀጣሪው የሚታጣውን ገንዘብ የሚያካክስ አንቀፅ በአዋጁ ታክሎበታል፡፡
በሌላ በኩል አዋጁ ከግብር ነፃ ያደረጋቸው የሥራ አይነቶችም አሉ፡፡ ከግብር ነፃ ከተባሉት መካከል በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የሚቀጥሯቸው ሰራተኞች እንደሚገኙባቸው ሰምተናል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቋሚነት በቋሚ ኮሚቴ የሚሰሩ አባላት የምርጫ ዘመን ቆይታቸውን አጠናቀው ሲሰናበቱ ለመቋቋሚያ የሚሰጠው ገንዘብ ከግብር ነፃ አለመሆኑ ግን በአንዳንድ አባላት ዘንድ ጥያቄ አስነስቶ ነበር፡፡
የገቢ ግብር አዋጅ መፅደቅ ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ እድገቷ የሚመነጨውን ገቢ በመሰብሰብ ሀገራዊ ወጪዋን በራሷ አቅም ለመሸፈን ያስችላታል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የፍትህና አስተዳደር ጉዳዬች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡትን የታክስ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅንም አፅድቋል፡፡
በተጨማሪም 16 የጠቅላይ ፍርድ ቤት እጩ ዳኞችን ሹመትም በሙሉ ድመፅ አፅድቋል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን