• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

መስከረም 29፣ 2012/ የህግ ታራሚዎች ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ፣ አያያዛቸውም ከአድሎዎ የፀዳ እንዲሆን ያስችላል የተባለ የፌደራል የማረሚያ ቤቶች ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀረበ

ረቂቅ ሕጉ ለሴት ታራሚዎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሶችን መንግስት እንዲያቀርብ ያስገድዳል፡፡እናቶቻቸው ጋር እስር ቤት ለሚገኙ ሕፃናትም ማቆያና መዋዕለ ሕፃናት የማሟላት ሀላፊነት በማረሚያ ቤቶች ላይ ተጥሏል፡፡በቀደመው ድንጋጌ የነበረውና ከእናቶቻቸው ጋር ወደ ማረሚያ ቤት የገቡ አመት ከመንፈቅ ላልሞላቸው ሕፃናት እንክብካቤ የሚያስፈልገውን በጀት ማሟላትም በህጉ እንደተጠበቀ ነው፡፡ረቂቅ አዋጁን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መስፍን ቸርነት እንዳሉት ተሻሽሎ የቀረበው ህግ የተጀመረውን የፍትህ ተቋማትን አሰራር ማሻሻያ የሚያበረታ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቶች የመብት ጥሰት ሲፈፀምባቸው እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው የተሻሻለው ህግ የታራሚዎች ደህንነትና መብት እንዲጠበቅ ያግዛል ብለዋል፡፡ህጉን ማሻሻል ያስፈለገባቸው ምክንያቶች ብለው ከጠቀሷቸው መካከልም በህግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎች ሰብአዊ ክብራቸውን ከሚያዋርድና አድሏዊ አያያዝ መጠበቅ ማስቻል አንዱ ነው፡፡ለታራሚዎች ሊሟሉ የሚገቧቸው የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የመኝታና የአልባሳት አቅርቦቶችም በቂና ደረጃቸውን የጠበቁ አልነበሩም የተባለ ሲሆን ወጥ የሆነ አሰራር በማበጀት ይህንን ማስተካከል እንደሚያስፈልግም ተነግሯል፡፡

በተጨማሪም ታራሚዎች ከእስር ተፈትተው ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ በቂ ክህሎት ኖሯቸው ኑሯቸውን በአግባቡ እንዲመሩ ማረሚያ ቤቶች የተለያዩ የክህሎት ማስጨበጫ ስልጠናዎችን የመስጠት ሀላፊነት በረቂቅ ህጉ ተጥሎባቸዋል፡፡ረቂቅ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት በዝርዝር እንዲፈተሸና ማስተካከያ ካስፈለገውም እንዲታከልበት ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የዛሬውን መደበኛ ስብሰባውን የጀመረው በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት የተለዩትን የምክር ቤቱን አባል ወ/ሮ ኑሪያ ኢንድሪስን በህሊና ፀሎት በማሰብ ነበር፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers