• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ሸገር ወሬዎች እና ልዩ ወሬዎች

መጋቢት 11፣2011/ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሒሳብ ምርመራ የተገኘበትን በመቶ ሚሊየን ብር የሚቆጠር ግኝት ለማስተካከል እየሰራሁ ነው አለ፡፡

የማስተካከያው እርምጃው ግን የሂሳብ ጉድለቱን ባገኘው መስሪያ ቤት ሳይረጋገጥ ተቀባይነት አይኖረውም ተብሏል፡፡በፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በ2009 በተደረገው የሒሳብ ምርመራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመቶ ሚሊየን የሚቆጠር ብር ጉድለት አግኝቻለሁ ብሏል፡፡

በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የስራ ሀላፊዎች ጠርቶ በእያንዳንዱ ግኝት ላይ ስለወሰዱት የማስተካከያ እርምጃ ጠይቋቸዋል፡፡የስራ ሀላፊዎቹ በምክር ቤቱ ተገኝተው ዛሬ በሰጡት መልስ የስራ መርሃ ግብር ወጥቶ በኦዲት ግኝቱ ላይ የማስተካከያ እርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል፡፡

ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ በሒሳብ ምርመራ አግኝቸዋለሁ ካለው ጉድለት መካከል ሁለተኛው የዲያስፖራ በዓል ዝግጅት ላይ የወጣ የ7 ሚሊዮን ብር ወጪ ማስረጃ አልቀረበበትም፡፡ለ28ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወጪ ተደርጓል የተባለ 14 ነጥብ 9 ሚሊየን ብርም ማስረጃ ያልቀረበበት ነው ተብሏል፡፡ከበጀት አስተዳደር መምሪያ ውጪ በጀት ስለመኖር አለመኖሩ የሚያረጋግጥ ስምና ፊርማ ሳይኖርም 183 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ለአፍሪካ ህብረት አባል አገራት መዋጮ ክፍያ በሚል ወጪ ተደርጓል ይላል የኦዲት ግኝቱ፡፡የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በጀትን በእቅድ ከመምራትና ወጪዎችን በትክክል ከመመዝገብ አኳያ ጉድለት አለበት የሚል ወቀሳም ከቋሚ ኮሚቴው ቀርቦበታል፡፡እንደምሳሌም በ2009 በጀት አመት ከአጠቃላይ በጀቱ ጋር ሲነፃፀር በድምሩ 330 ሚሊየን ብር ከበጀት ብልጫ ያለው ገንዘብ ወጪ እንደተደረገ ተመዝግቧል ተብሏል፡፡የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች ግኝቶቹን ለማስተካከል ስራ ጀምረናል ብለዋል፡፡

የኦዲት ግኝቱ የገዘፈው ግን ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ሕግ ጋር የማይጣጣም ህግ ባላቸው የተለያዩ አገራት የሚገኙ 60 ሚሲዮኖቻችንን ሒሳብ ስለምናስተዳድር ነው የሚል ሀሳብም አቅርበዋል፡፡የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ግን የሂሳብ ጉድለቱ በአገር ውስጥ የሚደረጉ ግዢዎችንም የሚያካትት ነው በሚል ሀሳባቸውን ሳይቀበሏቸው ቀርተዋል፡፡ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል እየወሰድኩ ነው የሚለው እርምጃ በዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ እስካልተረጋገጠ ድረስም ተቀባይነት እንደማይኖረው በቋሚ ኮሚቴው አባላት ተነግሯቸዋል፡፡

ትዕግስት ዘሪሁን

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers