• Slider One

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ታሪክን የኋሊት፣ ጥር 15፣2009

በጥፋት ተወዳዳሪ የሌለው የመሬት ነውጥ

በዓለም ላይ ለቁጥር የበዙ ርዕደ መሬቶች ደርሰዋል፡፡

በታሪክ ተመዝግበው ከሚገኙት በቻይና የደረሰውና የሻንዚው ርዕደ መሬት የሚባለው በአጥፊነታቸውና አውዳሚኒታቸው ከሚጠቀሱ የመሬት ነውጦች አንዱ ነው፡፡

የሻንዚ ርዕደ መሬት የደረሰው የዛሬ 461 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡

የርዕደ መሬቱ መነሻ ስፍራ የሻንዚ ግዛት ቢሆንም ሄናን፣ ጋንሱ፣ ሻንዶንግ፣ ሁቤይ፣ ሁናን፣ ጂያንግሱና ሌሎችንም ግዛቶች መትቷል፡፡

በዘመኑ የርዕደ መሬት መለኪያ ባይኖርም ነውጡ የከባድ ከባድ እንደነበረ ይገመታል፡፡

የመስኩ ጠበብት ከአንዳንድ ቅሬት መረጃዎች በመነሳት ነውጡን በርዕደ መሬት መለኪያ 7 ነጥብ 9 እንደሚደርስ አስልተውታል፡፡

ርዕደ መሬቱ በአገሪቱ በ800 ኪሎ ሜትር መጠነ ዙሪያ ያለን ስፍራ አካሏል፡፡

ከንዝረት ማዕከሉ እስከ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ያሉ አካባቢዎች ክፉኛ ተርገፍግፈዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎችም ርዕደ መሬቱ ያስከተላቸው የመሬት መሰንጠቆች እስከ 20 ሜትር ጥልቀት ያላቸውን ገደሎች ፈጥረዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ታሪክን የኋሊት፣ጥር 12፣2009

የአሜሪካው በዓለ ሲመት

አሜሪካ ከመጀመሪያው ፕሬዝዳቷ ከጆርጅ ዋሽንግተን አንስቶ ፕሬዝዳንታዊ በዓለ ሲመት ስታከናውን ቆይታለች፡፡

ጥር 12ን መደበኛ የፕሬዝዳታዊ በዓለ ሲመት ቀን በማድረግ ስራ ላይ ካዋለችው 84 ዓመታት አስቆጥራለች፡፡

በአሜሪካ ህገ-መንግስት መሰረት ማንኛውም ተመራጭ ፕሬዝዳንት ቃለ መሐላ መፈፀም አለበት፡፡

በዳግም ምርጫ ቢቀናው እንኳ ይሄን ስርዓት አያስተጓጉልም፡፡

የበዓለ ሲመቱ ስነ-ስርዓትም የዚሁ ተያያዥ አካል ነው፡፡

ከ228 ዓመታት በፊት የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳት ጆርጅ ዋሽንግተን ቃለ መሐላ በመፈፀም በዓለ ሲመታቸውን ያከናውኑት በመጋቢት ወር 3ኛ ሳምንት መጨረሻ ነበር፡፤

ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት እስከ ፕሬዝዳት ፍራንኪሊን ዴላኖ ሩዝቬልት የአስተዳደር ዘመን መጀመር ድረስ የካቲት 25 ቀን ቋሚ የበዓለ ሲመት ዕለት ሆኖ ቆየ፡፡

በነዚህ ጊዜያት የካቲት 25 ቀን እሁድ ዕለት ከዋለ በዓለ ሲመቱ በማግስቱ የካቲት 26 የሆነባቸውም አጋጠሚዎች ነበሩ፡፡

አራት ጊዜያትም በዓለ ሲመቶች በየካቲት 26 ቀን ተከናውነዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ታሪክን የኋሊት፣ጥር 10፣2009

ለ3 ዓመታት የዘለቀው የሌሊንግራዱ ከበባ

በዓለማችን የጦርነት ታሪክ የበረከቱ ከተሞች አሠቃቂ ከበባ ገጥሟቸዋል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የሩሲያዋ የዛን ጊዜዋ ሌኒንግራድ የዛሬዋ ሴንትፒተርስበርግ የገጠማት ከበባ በአሠቃቂነቱ ከመጀመሪያው ረድፍ የሚሰለፍ ነው፡፡

ሌኒንግራድ ከአሠቃቂው የ3 ዓመታት ገደማ ከበባ መተንፈሻ ቀዳዳ ያገኘችው የዛሬ 73 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡

ሶቪየት ህብረትን የወረረው የናዚ ጀርመን ኃይል ሌኒንግራድ ለመድረስ ከሁለት ወር ተኩል በላይ ጊዜ አልጠየቀውም፡፡

ያም ሆኖ የሶቪየቱ ቀይ ጦርና የከተማዋ ነዋሪዎች ናዚዎች ወደ ሌኒንግራድ እንዳይዘልቁ የሞት የሽረት ትግልና ትንቅንቅ አደረጉ፡፡

ናዚዎቹ ከበባውን ከማጠናከራቸውም በተጨማሪ በከተማዋ ላይ የከባድ መሳሪያ ውርጅብኛቸውን ማውረዱን እንደ ዋነኛው የጦር ስልት ተከተሉ፡፡

የከተማዋ ተከላዮችም እጅ መስጠት የማይሞከር ነው አሉ፡፡ የግንባር ስጋ ሆኑ፡፡

ጦርነቱ ብቻ ሳይሆን ከበባው በከተማይቱ ላይ አሠቃቂ ሞት ደግሶ ሠፈረባት፡፡

ያኔ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች የነበራት ሌኒንግራድ የምግብ ክምችቷ የተሟጠጠው ገና በከበባው የመጀመሪያ ወራት ነበር፡፡

 የቀረችዋን በነፍስ ወከፍ በቀን 250 ግራም ምግብ በራሸን ማከፋፈል ተጀመረ፡፡

የነፍስ ወከፍ የምግብ ድርሻው መጠን በቀን ወደ 150 ግራም አሽቆለቆለ፡፡

ሁኔታው እየከፋ ሲመጣ ይሄም ከነጭራሹ ቀረ፡፡ የቧንቧዎች ውሃ ነጠፈ፡፡

ጦርነቱ በራሱ ነፍስ ነጣቂ ነበር፡፡ ጦርነቱን ረሃብ አገዘው፡፡ የአቅም መዳከም የሕዝቡን ጤና ደቆሰው፡፡ ሞት አክሊሉን ደፋ፡፡

ከበባ፣ ጦርነት፣ ረሃብና ጤና ማጣት በተረባረቡበት ሕዝብ ላይ ጨካኙ የሩሲያ ክረምት የአሠቃቂው ትዕይንት አጋዥ ሆነ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ታሪክን የኋሊት፣ጥር 9፣2009

የበረሃው መዓበል

በኢራቅ ተይዛ የነበረቸውን ኩዌትን ነፃ ለማውጣትና ሳውዲ አረቢያን ከጥቃት ለመከላከል አሜሪካ መራሹ የበረሃው ማዕበል ዘመቻ የተጀመረው የዛሬ 26 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡

ኢራቅ ኩዌትን ወርራ ለመያዝ እስከተቃረበችበት ጊዜ ለ10 ዓመታት ያህል ከኢራን ጋር ደምሳሽና ጥሪት አስጨራሽ ጦርነት ስታካሂድ ቆየች፡፡

በጦርነቱ ዘመን እንደ ሳውዲ አረቢያና ኩዌት ካሉ ሱኒ መንግስታት የተበደረችው በብዙ ቢሊዮን ዶላሮች ዕዳ ተጫናት፡፡

የዘመኑ የኢራቅ መሪ ሳዳም ሁሴን በዕዳ ጫናው በትከፍላለህ አልከፍልም ከጎረቤቶቻቸው ጋር አተካሮ ውስጥ ገቡ፡፡

ሳዳም ሁሴን ጎረቤቶቻቸውን አልከፍልም አፍንጫችሁን ላሱ አሏቸው፡፡

ድርድሮች ፍሬ አልባ ሆኑ፡፡

ቅራኔው እየተካረረ መጣ፡፡

በዚያ ላይ ሳዳም ኩዌት ከሩሜይላ የነዳጅ መገኛ ስር ለስር እየዘረፈችን ነው ሲሉ ውዝግቡን አካረሩ፡፡

ሳዳም ጦር አውርዳቸውን ተያያዙት፡፡

ከዛቻ አልፈው ትንሿን ጎረቤታቸውን ኩዌትን ወርረው ያዟት፡፡

ሳይዋረዱ ኩዌትን ለቀው እንዲወጡ በማስጠንቀቂያ ላይ ማስጠንቀቂያ ተነባበረባቸው፡፡

የፀጥታው ምክር ቤትም ብርቱ ትዕዛዝን ያዘለ ውሳኔ አሳለፈባቸው፡፡

ሳዳም ቁብም አልሰጣቸውም፡፡

ኩዌትን ለቀህ ውጣ የሚሉኝ የታሪክ መሐይሞች ናቸው ሲሉ ወረፏቸው፡፡

በኦቶማን ቱርኮች ዘመን የኢራቋን ባስራ ግዛት የሚያስተዳድረው ኢሚር ኩዌትን ጠቅልሎ ይገዛ እንደነበር ታሪክን መለስ ብሎው እንዲመለከቱ አስታወሱ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ታሪክን የኋሊት፣ጥር 5፣2009

የቢያፍራው ጦርነት

ናይጄሪያ ከ50 ዓመታት በፊት ነፃነቷን ብትቀዳጅም ብሔራዊ አንድነቷ ስጋት የተደቀነበት ገና 10ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን ለማክበር ሳትበቃ ነበር፡፡

የቢያፍራው የመገንጠል ንቅናቄ የቢያፍራውን ጦርነት ወለደ፡፡

ከ3 ዓመታት ያህል ደም አፋሳሽና እልህ አስጨራሽ ውጊያ በኋላ የናይጄሪያ ፌዴራላዊ ኃይል ባለድል ሆነ፡፡

የቢያፍራ ተገንጣዮች እጅ ሰጡ፡፡

ይሄ ከሆነ ዛሬ ልክ 47ኛ ዓመቱን ደፈነ፡፡

የያኔዋ አዲስ አገር ናይጄሪያ በርካታ ተቃርኖዎች የሚፋተጉባት ነበረች፡፡

በዚህ ላይ በደቡብ ምስራቅ አካባቢዎቿ የነዳጅ ዘይት መገኘት የሐብት ክፍፍሉ ጉዳይ ቅራኔውን አጦዘው፡፡

የብሪታንያ፣ የኔዘርላንድስ፣ የፈረንሳይና የጣሊያን ኩባንያዎች የናይጀሪያን የነዳጅ ፀጋ ለመቀራመት የጀመሩት ግብግብ የቢያፍራን ግዛት የመገንጠል ፍላጐት አናረው፡፡

የቅኝ አገዛዙ ዘመን እርሾም ቅራኔውን አብላላው፡፡

የአገሪቱን ደቡብ ምስራቃዊ አውራጃዎች ከልለው የቢያፍራ ግዛት ያሉት የኢግቦ ጐሳዎች በኮሎኔል ኦደሚጐ ኦጁኩ መሪነት ግዛቲቱን ከተቀረችው ናይጄሪያ ነጥለናል፤ ራሳችንን የቻልን ነፃ አገር ነን አሉ፡፡

የራሳቸውን አካባቢያዊ ሠራዊት መሠረቱ፡፡

የናይጀሪያ ፌዴራላዊ መንግስት ቢያፍራዎች መገንጠሉን እንዲተዉ ቢያግባባ ቢማፀንም ሰሚ አላገኘም፡፡

ግንጠላውን ለማክሸፍ ጦሩን ወደ ቢያፍራ አዘመተ፡፡

ግጭቱ ስር እየሰደደ አድማሱ እየሰፋና እልቂቱን እያበዛው ሄደ፡፡

ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቦታቸውን ለወታደራዊ እልህ እየለቀቁ መጡ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Leza Vote Banner
Sheger 102.1 AudioNow Numbers