• Slider One

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ታሪክን የኋሊት፣ጥር 2፣2009

የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት

አሜሪካ እንደ አገር ከቆመች በኋላ ከአንድ ምዕተ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ የመበታተን ስጋት ተጋርጦባት ነበር፡፡

አንድነቷ ፈተና ላይ ወደቀ፡፡

ያኔ ባሪያ አሳዳሪነት የሰሜንና የደቡብ ግዛቶች የልዩነት መነሻ ሆነ፡፡

ባሪያ አሳዳሪነትን እንደ ልዩ ምጣኔ ሐብታዊ ጠቀሜታ ያዩት ደቡባዊ ግዛቶች ለስርዓቱ መቀጠል ሽንጣቸውን ገትረው ቆሙ፡፡

አብዛኞቹ ሰሜናዊ ግዛቶች ባርነት መወገድ አለበት አሉ፡፡

ሰባት የባሪያ አሳዳሪ ስርዓት ደጋፊ ደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶች አንድ በአንድ በየፊናቸው ከሕብረቱ ተነጥለናል ማለቱን ተያያዙት፡፡

ደቡባዊቷ የፍሎሪዳ ግዛት ከአሜሪካ ህብረት ተነጥዬ ራሴን የቻልኩኝ ነኝ ብላ የተለየችው የዛሬ 155 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡ 

ደቡብ ካሮላይና፣ ሚሲሲፒ፣ አላባማ፣ ሉዊዚያና፣ ጆርጂያና ቴክሳስም በተመሳሳይ የመነጠል መንገድ ተጓዙ፡፡

ባርነት መቅረት የለበትም ብለው የቆረጡ ግዛቶች ራሳቸውን ከአሜሪካ ፌዴራላዊ ህብረት በመለየት ኮንፌዴራላዊ ጥምረት ፈጠሩ፡፡ ጀፈርሰን ዴቪስን ፕሬዝዳንት፤ ማዕከላቸውን አላባማ በማድረግ የተነጠለውን ኮንፌዴራላዊ መንግስት መሠረቱ፡፡

የፀረ ባርነት አቀንቃኙ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን የአንድነቱን ደጋፊ የሰሜን ግዛቶች አስተባብረው ለፌዴራላዊ ኅብረት በፅናት ቆሙ፡፡

መነጣጠሉ ከተጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ የህብረቱ ኃይሎች ይዞታ በሆነው በፎርት ሳምተር ደቡባዊያኑ ያስጮኋት ጥይት የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ማስጀመሪያ ፊሻካ ሆነች፡፡

ከፎርት ሳምተሩ ግጭት በኋላ አርካንሳስ፣ ሰሜን ካሮላይና ቴኔሲና ቨርጂኒያ ተገንጣዮቹን ግዛቶች በመቀላቀል ኮንፌዴራሊስቶቹ አስራ አንድ ደረሱ፡፡

ልዩነቱ እየሠፋና ቅራኔው እየተካረረ መጣ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ታሪክን የኋሊት፣ጥር 1፣2009

የደቡብ ሱዳን ነገር…

ደቡብ ሱዳናውያን ነፃነታቸውን በወጉ ማጣጣም የሚችሉበትን ዕድል አጨናገፉት እንጂ ውድ ዋጋ የተከፈለበት ነው፡፡

2ኛው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በደቡብ ሱዳኑ የጦርና የፖለቲካ ድርጅት SPLM እና በሱዳን መንግስት መካከል አጠቃላዩ የሰላም ስምምነት የተፈረመው የዛሬ 12 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡

ሱዳን ከ57 ዓመታት በፊት ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ከመላቀቋ በፊት ባዕዳኑ ሰሜኑንና ደቡቡን በነጣጥለህ ግዛው የአስተዳደር ፈሊጣቸው ለያይተውት ኖሩ፡፡

ቅኝ ገዢዎቹ አገዛዛቸው ባከተመ ጊዜ የአገሪቱን ነፃነት ሲያረጋግጡ የወሳኝነቱን የአድራጊ ፈጣሪነቱን አረባዊ ዝርያ ላላቸው ሰሜናውያኑ ተዉላቸው፡፡

የፖለቲካው፣ የአስተዳደሩ፣ የምጣኔ ሐብቱ አድራጊ ፈጣሪዎቹ በዚህ ግባ በዚህ ውጣ ባዮቹ፣ አዛዥ ናዛዦቹ ሰሜናዊያኑ ሆኑ፡፡

ደቡቦቹ ተገፉ፡፡ ተገለሉ፡፡ ተንገዋለሉ፡፡ ከቅኝ ግዛት በመላቀቂያው የሽግግር ድርድር ወቅት ነገሬ አልተባሉም ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ ከአጠቃላይዋ ሱዳን ነፃነት ውሎ ሳያድር የመጀመሪያው የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተካሄደ፡፡

የዚያን ጊዜውን ዕልቂት ለማስቆም በተካሄደው ድርድር ከ44 ዓመታት በፊት ተፋላሚዎቹ የአዲስ አበባውን የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ታሪክን የኋሊት፣ታህሳስ 28፣2009

እማሆይ ቴሬሳ

ትውልደ አልባንያዊቱ እማሆይ ቴሬሳ በሩህሩሕነታቸውና በሰብዓዊነታቸው ዓለማችን ከምታውቃቸው የመልካምነት ተምሳሌቶች አንዷ ናቸው፡፡

እማሆይ ቴሬሳ የደግነትና የመልካምነታቸው ጫፍ ወደታየባት ሕንድ የገቡት የዛሬ 91 ዓመት በዛሬዋ እለት ነበር፡፡

እማሆይ ቴሬሳ በመጀመሪያ ሕንድ የገቡት በካቶሊክ ሚሲዮን መምህርነት ነበር፡፡

በሂማላያ ተራራ አቅራቢያ በሚገኝ መንደር ማስተማራቸውን ተያያዙት፡፡

በማስተማር ተግባር ተሰማርተው ወዲህ ወዲያ ሲሉ በሕንድ በተለይም በካልካታ ያስተዋሉት ይህ ከዚህ ያልተባለ ፍፁማዊ ድህነት ያስጨንቃቸው ጀመር፡፡

አይተው እንዳላዩ ማለፉ አላስቻላቸውም፡፡

የተራቡትን ለማብላት፣ የታረዙትን ለማልበስ፤ የትም ለወደቁት መጠጊያ፣ለታመሙት ጤና መሻት አለብኝ ብለው ቢያስቡም፤ በእጃቸው ሰባራ ሳንቲም አልነበራቸውም፡፡

እማሆይ ለተራቡት ጉርስ፣ ለታረዙት ልብስ ይሆን ዘንድ ከቦርሳቸው ቤሳ ቤስቲን ባይኖርም ቤት ከቤት፤ ከስፍራ ስፍራ ተዘዋውረው በምንዱባኑ ስም ይለምኑ ገቡ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ታሪክን የኋሊት፣ታህሳስ 27፣2009

የፕራግ ፀደይ

ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የቀድሞው ቼኮዝሎቫኪያ በዘመኑ ምሥራቃዊ ኃያል በሶቪየት ኅብረት ተፅዕኖ ሥር አዳሪ ሆነች፡፡

ከ49 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት በለዘብተኛ ፖለቲካዊ አቋማቸው ይታወቁ የነበሩ አሌክሳንደር ዱብቼክ የዘመኑ የቼኮዝሎቫኪያ ኮሚኒስቶች የፖለቲካ ማኅበር ዋና ፀሐፊ ሆነው መመረጣቸው አገሪቱ ከሶቪየቶች ተፅዕኖ ለመላቀቅ የሚያስችላት ዕድል ፈጠረ፡፡

በመላ አገሪቱ ሰላማዊ የለውጥ ንፋስ መንፈስ ጀመረ፡፡ ዱብቼክ የተለያዩ ለውጦችን ሥራ ላይ ማዋል ጀመሩ፡፡

የንግግርና ኃሳብን በነፃ የማስተላለፍ መብትን ፈቀዱ፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ተጭኖ የነበረውን ጥብቅ ቁጥጥር አላሉት፡፡

የዜጐችን የሰብዓዊ መብት እናረጋግጣለን እንደልባችሁ ተንፍሱ እነሆ ዴሞክራሲ አሉ፡፡ በእዝ ተቆፍድዶ የነበረው ምጣኔ-ሐብት ወደ ነፃ የግብይት ሥርዓት እንዲያመራ ፈር ቀደዱ፡፡

ዱብቼክ ሌሎች የለውጥ ኃሳቦችንና ማሻሻያዎችን ሥራ ላይ ለማዋል ተነሱ፡፡

ሰላማዊው የለውጥ ውጥን በታሪክ የፕራግ ፀደይ የሚል መጠሪያ ተሰጠው፡፡የዱብቼክ የለውጥ ኃሳብ በዘመኑ የሶቪየት መሪዎች ዘንድ አልተወደደላቸውም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)

ታሪክን የኋሊት፣ታህሳስ 25፣2009

ቤኒቶ ሙሶሊኒ

በ2ኛው የዓለም ጦርነትና ከዛም በፊት በሰፊው የጥፋት አሻራቸውን ካኖሩት መካከል የጣሊያን ፋሽስቶች መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ፍፁማዊ ፈላጭ ቆራጭ ገዢ መሆኑን ያወጀው የዛሬ 91 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡

ሙሶሊኒ በወጣትነቱ ልቡ ወደ ሶሻሊስታዊ ፖለቲካ አዘነበለ፡፡

የሥነ-ፅሁፍ ችሎታውን ተጠቅሞ ጦርነት አውጋዥ መጣጥፎችንና ትንታኔዎች ያቀርብ ያዘ፡፡

ለምሣሌ ከ100 ዓመታት በፊት ጣሊያን ሊቢያን ለመያዝ ታደርግ የነበረውን ሙከራ ኢምፔሪያሊስታዊ ተስፋፊነት ሲል ያብጠለጠለበት ፅሁፉ ይጠቀስለታል፡፡

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ሂደት ሙሶሊኒ የነበረበት የጣሊያን ሶሻሊስቶች የፖለቲካ ማኀበር ጦርነቱን እቃወማለሁ አለ፡፡

ሙሶሊኒም ይሄንኑ የጦርነት አውጋዥ ውሣኔ ደጋፊ ሆነ፡፡

ግን በጦርነት ተቃዋሚነቱ ብዙም አልገፋበትም፡፡

ጥቂት ቆይቶ ጦርነት አራጋቢ ሆነ፡፡

የጣሊያን ሶሻሊስቶች ከውሣኔያቸው ውጭ የሆነውን ሙሶሊኒን አታስፈልገንም ብለው ከማኅበራቸው አባረሩት፡፡

ሙሶሊኒ የፋሽስት የፖለቲካ ማኅበሩን መሠረተ፡፡

የፋሽስት የፖለቲካ ማኅበሩ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ጡንቻው ፈረጠመ አቅሙ በረታ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ...

አስተያየት ይፃፉ (0 አስተያየት)
Sheger 102.1 AudioNow Numbers