• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ታሪክን የኋሊት መስከረም 10፣2010

ፖርቹጋላዊው አሳሽ ፈርዲናንድ ማጂላን

ፖርቹጋላዊው አሳሽ፣ ፈርዲናንድ ማጂላን፣ ምዕራባዊውን የባሕር መስመር ተከትሎ፣ ከአትላንቲክ ወደ ሰላማዊ ውቅያኖስ በማቋረጥ ፋና ወጊ ነው፡፡

ማጄላን፣ 270 ባሕረኞችን ያካተተና አምስት መርከቦችን ያቀፈውን አካል እየመራ፣ ለታላቁ ተልዕኮ፣ ከስፔን ባሕር ዳርቻ የተነሳው የዛሬ 498 ዓመት በዛሬው እለት ነው፡፡

አሳሹ፣ ውጥኑን ለዘመኑ የስፔን ንጉስ ቻርልስ አምስተኛ አሳውቃቸው፡፡

ንጉሱም እንዳልከው ይሁን አሉት፡፡

አምስት መርከቦችንና አስፈላጊ ቁሳቁሶችና ስንቅም ፈቀዱለት፡፡

ከፖርቱጋል፣ ከስፔን፣ ከጣሊያን፣ ከጀርመን፣ ከግሪክ ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ የተውጣጡ 270 ባሕረኞች፣ ለታላቁ የባሕር መስመር አሰሳ ተሰለፉ፡፡

በመጀመሪያ ጉዟቸው፣ ካናሪ ደሴት ደርሰው፣ ወደ ምዕራብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ፣ ተሻገሩ፡፡

ኬፕቬርዴን አገኙ፡፡

ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በማምራት፣ ብራዚል ደረሱ፡፡

ወደ ላቲን አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍም አቆለቆሉ፡፡

ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በአድካሚና አታካች ፈተናዎች ተሞላ፡፡

በላቲን አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍ፣ የአየሩ ቅዝቃዜ የሚያንዘፈዝፍና አጥንትን የሚሠረስር ነበር፡፡

በዚያ ላይ የሚበላና የሚጠጣው ተሟጠጠ፡፡

 

ከጠኔው መበርታት የተነሳ፣ ባሕረኞቹ የእቃ መቋጠሪያ፣ የቆዳ ጠፍር ሳይቀር እስከመብላት ተገደው ነበር፡፡

መከራውና ችግሩ ሲበዛ፣ ማጂላን ከተወሰኑት ባሕረኖች ተቃውሞ ገጠመው፡፡

አመፅም ተነሳበት፡፡

አመፅ ካነሳሱት ከአምስቱ የመርከብ አዛዦች መካከል፣ አንዱን  በሞት ቀጣው፡፡

ሌላኛውን የመርከብ አዛዥ፣ ሰው ከሌለበት ምድር ጥሎት ሄደ፡፡

ለተልዕኮው ሲል ጨከነ፡፡

አመፁን አስታገሰው፡፡

ማጄላን፣ ተስፋ ሳይቆርጥ፣ ባደረገው አሰሳ፣ በላቲን አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍ ሲመኘው የነበረውን የባሕር መተላለፊያ ሰርጥ አገኘ፡፡ ታላቅ ግኝት ሆነለት፡፡ አሁን የማጂላን ሰርጥ ተብሎ ይጠራል፡፡

ታዲያ ይሄን ሰርጥ በቀላሉ አላለፉትም፡፡ ከአምስቱ መርከቦች ሁለቱን፣ በወጀብና ማዕበል አደጋ አጥተውበታል፡፡

ሰርጡን እንዳለፉ፣ የተረጋጋውን ባሕር አገኙት፡፡ ማጂላን ሰላማዊ አለው፡፡ አሁን ፓስፊክ ወይም ሰላማዊ ውቅያኖስ የሚሰኘው ውቅያኖስ ነው፡፡

ማጄላን፣ በዚሁ ተልዕኮ ላይ እያለ፣ ፊሊፒንስ ውስጥ ቢገደልም፣ ወደ እስያ መተላለፊያ አዲስ የባሕር መስመር በማግኘቱ፣ የተሳካለት አሳሽ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል፡፡

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers