• United Bank S.C.

    ሕብረት ባንክ አ.ማ.

  • Slider Two

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

  • Sldier Three

    የምስል ተጓዳኝ መልዕክት

ታሪክን የኋሊት፣ታህሳስ 4፣2009

“የታህሳሱ ግርግር” - የነብርጋዲየር ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት 56 ዓመት ሞላው

የኢትዮጵያ የክቡር ዘበኛ መኮንኖችና ተባባሪዎቻቸው የንጉስ አፄ ኃይለ-ስላሴን መንግስት ለመገልበጥ ሙከራ ካደረጉ ዛሬ 56ኛ ዓመቱን ደፈነ፡፡

የክቡር ዘበኛ ጦር አዛዥ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል መንግስቱ ነዋይና  ወንድማቸው ግርማሜ ነዋይ ዋነኞቹ  የግልበጣው ጠንሳሾች ሆኑ፡፡

ለሌሎች ተባባሪዎቻቸውንም ከጐናቸው አሠለፉ፡፡ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ኃላፊ ኰሎኔል ወርቅነህ ገበየሁና አንዳንድ ወጣት ምሁራን ዋነኛ ተባባሪና ደጋፊዎች ሆኑ፡፡

መፈንቅለ መንግስቱን የጠነሰሱት እነ ብርጋዲየር ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአፄው ስርዓተ ተብድሏል፡፡ ተረግጧል፡፡ ተጨቁኗል፡፡ ከዚህ ለመውጣትም ለውጥ ያሻዋል አሉ፡፡

ከ56 ዓመታት በፊት ንጉስ ነገስቱ አፄ ኃይለሥላሴ ለጉብኝት ወደ ብራዚል ማምራታቸውን  እነ ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ የለውጥና የግልበጣ ውጥናቸውን ስራ ላይ ለማዋል እንደ መልካም አጋጣሚ ቆጠሩት፡፡

ታህሣስ 4/1953 ምሽት ላይ ቁልፍ ቁልፍ የንጉሱን ሹሞችና ባለሟሎችን ወደ ክብርዘበኛ ጽ/ቤት ጠርተው ሰበሰቧቸው፡፡  

ተጠሪዎቹን ሹማምንት አገቷቸው፡፡

ገልባጮቹ ያሠለፏቸው ወታደሮች የገንዘብ ሚኒስቴርን፣ የብሔራዊ ባንኩን እና  ሬዲዮ ጣቢያውን ተቆጣጠሩ፡፡

በጄኔራል መንግስቱ የሚታዘዙት የክቡር ዘበኛ ወታደሮች በከተማዋ የሚገኙ የሌሎች ክፍሎችን የጦር ሠፈሮች ከበቡ፡፡

የግልበጣው ጠንሳሾች አብዛኛውን የአዲስ አበባ ክፍል በእጃቸው እንዳስገቡ በያዟቸው በንጉሱ ልጅ አልጋወራሽ አስፋው ወሰን ድምፅ በብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያው በተሰራጨ መግለጫ የአፄ ኃይል ስላሴ መንግስት መወገዱ ታወጀ፡፡ አዲሱም መንግስት በአልጋ ወራሹ እንደሚመራ አሳወቁ፡፡

 

በዋነኞቹ ገልባጮች በብርጋዲየር ጄኔራል መንግስቱና በወንድማቸው ግርማሜ ነዋይ የተረቀቀውን ባለ 16 ነጥብ ማሳሰቢያም አከሉበት፡፡ የዘመኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለገልባጮቹ ድጋፍ ሰልፍ ወጡ፡፡

የንጉሱም ታማኞች መፈንቅለ መንግስቱን ለማክሸፍ በብልህነት ፈጠኑ፡፡ የጦር ኃይሎች ኢታማዥር ሹም ሜጄር ጄኔራል መርዕድ መንገሻ የሚመሩት የምድር ጦር ሃይል የክብር ዘበኞችን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ተንቀሳቀሰ፡፡

አክሻፊዎች የአየር ኃይሉን ከጐናቸው አሰለፉ፡፡ መፈንቅለ መንግስቱን የሚያወግዙ በራሪ ወረቀቶች ተበተኑ፡፡  የፓትርያርኩ የአቡነ ባስልዩስ የውግዘት ቃልም ስለተበተነ የክብር ዘበኛ ሰራዊት ልቡ አፈገፈገ፡፡

ከየዳር አገሩ ግልበጣውን የሚያከሽፉ የጦር ሰራዊቱ ወታደሮች በብዛት ወደ አዲስ አበባ ስለመጡ የኃይል ሚዛኑ ወደ አፄ ኃይለስላሴ ደጋፊዎች አጋደለ፡፡

እነ- ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ ሙከራቸው ወደ መክሸፉ ማዘንበሉን ሲረዱ በገነተ ልዑል ቤተ መንግስት ካገቷቸው ሹማምንት መካከል የመከላከያ ሚኒስትሩን ራስ አበበ አረጋይን ጨምሮ 15 ባለ ሥልጣኖችን ረሸኑ፡፡

የግልበጣ ሙከራው ተባባሪ የፖሊስ አዛዡ ጄኔራል ፅጌ ዲቡ በተኩስ ልውውጥ ተገደሉ፡፡ ሌላኛው የነ መንግሥቱ ነዋይ አጋር የደህንነት ክፍሉ የበላይ ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ራሳቸውን አጠፉ፡፡ ከዚያ በኋላ ዋነኞቹ የግልበጣው ጠንሳሾች ወደ ሽሽት ገቡ፡፡

ወንድማማቾቹ ብርጋዲየር ጄኔራል መንግስቱ ነዋይና ወንድማቸው ግርማሜ ነዋይ ከሻምበል ባዬ ጥላሁን ጋር ሞጆ ላይ ተከበቡ፡፡ ገርማሜ ሻምበል ባዬን ገድለው ወንድማቸውን አቁስለው ራሳቸውን አጠፉ፡፡

መንግስቱ ተይዘው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ በስቅላት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡ ፍርዱም በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት አደባባይ ተፈፀመባቸው፡፡

አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑ ቢያንስ 300 ሰዎች ያለቁበትና ለአራት ቀናት የቆየው በታሪክም “የታህሳሱ ግርግር” በሚል ቅፅል የሚታወቀው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በመክሸፍ ተደመደመ፡፡

የኔነህ ከበደ

በማኅበረ ሰብ ገጾች ያጋሩ

Submit to FacebookSubmit to Google PlusSubmit to TwitterSubmit to LinkedIn
Sheger 102.1 AudioNow Numbers